አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 1/ 2016 ዓ/ም፦ ከአዲስ አበባ በስተሰሜን በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው ገርበ ጉራቻ አካባቢ በታጣቂዎች ታግተው ከሚገኙ የደባርቅ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች መካከል ባለፉት ቀናት 16ቱ ገንዘብ ከፍለው መለቀቃቸው ተገለጸ።
ከ167 በላይ የሚሆኑት ተማሪዎቹ በታጣቂዎች የታገቱት ሰኔ 26/2016 ዓ.ም. በሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች ከአማራ ክልል ተነስተው ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ላይ እያሉ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ገርበ ጉራቻ አካባቢ ነው።
እገታው መሰማቱን ተከትሎ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ወሰድኩት ባለው እርምጃ 160 ተማሪዎችን ማስለቀቁን ቢናገርም፤ መንግስት የታገቱ ተማሪዎች ተለቀዋል እያለ “ሀሰተኛ መረጃ እያሰራጨብነው” ሲሉ የታጋች ቤተሰቦች ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።
ከታገቱ አንድ ወር ከሆናቸው ተማሪዎች መካከል ባለፈው ሳምንት 16 የሚሆኑ ተማሪዎች ከ100 ሺህ እስከ 500 ሺህ ብር የማስለቀቂያ ገንዘብ ከፍለው መለቀቃቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በታጋቾቹ ላይ ግርፋት፣ ድብደባ እንዲሁም ጾታዊ ጥቃት መፈጸሙን የተማሪዎቹን እገታ ከቤተሰብ ጋር ሆነው በቅርበት እየተከታተሉ ያሉ ምንጮች ለዜና አውታሩ ገልጸዋል።
የተለቀቁት ተማሪዎች ከባሕር ዳር በጎደሉ ወንበሮች የተሳፈሩ 15 የሚሆኑ (ተማሪ ያልሆኑ) መንገደኞች አብረዋቸው እንደታገቱ [አሁንም በእገታ ላይ እንደሚገኙ] ተናግረዋል።
ቢቢሲ ያናገራቸው አንድ የታጋች ተማሪ ቤተሰብ “ታጣቂዎቹ በተማሪዎቹ ፊት ሁለት ሰዎችን መግደላቸውን እያለቀሱ ነግረውናል” ብለዋል።
ይህንም የተለቀቁ ተማሪዎች ያረጋገጡ ሲሆን፤ ከተማሪዎቹ ውጭ የነበሩ ሁለት መንገደኞች በታጣቂዎቹ መገደላቸውን ተናግረዋል ተብሏል።
ተገድለዋል የተባሉት ሰዎች ሁለቱም ወንዶች ሲሆኑ፤ አንዱ ‘ገንዘብ እያለው የለኝም ብሎ ዋሽቷል’ የተባለ ወጣት እና አንድ ጎልማሳ የሆኑ ሰው መሆናቸውንም ገልጸዋል።
“ልጆቹ በጣም ከስተዋል፤ ጠቁረዋል” ያሉ ተማሪዎችን በአካል አዲስ አበባ ላይ ያገኟቸው አንድ ምንጭ፤ “በቆሎ በሽንኩርት እና ቃሪያ ተለውሶ” የሚዘጋጅ (በአካባቢው የተለመደ) ምግብ ሲመገቡ እንደነበር ጠቅሰዋል።
ከ30 በላይ ይሆናሉ የተባሉት ታጣቂዎቹ ‘ፀጉራቸውን የተሰሩ፣ የሲቪል ልብስ የለበሱ እና የተማሩ’ መሆናቸውን ተማሪዎቹ አመልክተዋል።
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አፈናውን የፈጸመው “ሸኔ” በማለት የጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መሆኑን የገለጸ ሲሆን ታጣቂ ቡድኑ የቀረበበትን ክስ አስተባብሎ “በተማሪዎቹ እገታ ላይ እጄ የለበትም” ሲል መግለጹ ይታወሳል።
ይሁን እንጂ በተማሪዎቹ እገታ ላይ “የመንግሥት ደህንነት አካላት” እና “የበታች የፓርቲ ካድሬዎች” እጅ አለበት ብሎ እንደሚያምን አስታውቋል።
ባሳለፍነው ወር አዲስ ስታንዳርድ ያነመጋገራቸው የታጋች ቤተሰቦች ለአጋቾቹ የምንከፍለው ገንዘብ ስለሌለን በየገበያው እና በየመንደሩ እየለመንን ነው የምንገኘው ሲሉ መግለጻቸው ይታወሳል። አጋቾቹ የጠየቁትን ገንዘብ ለመክፍል የድጋፍ ደብዳቤ በማጻፍ በልመና ላይ እንደሚገኙ የታጋች ቤተሰቦቹ ተናግረዋል። አስ