ትንታኔማህበራዊ ጉዳይ
በመታየት ላይ ያለ

ጥልቅ ትንታኔ፡ “በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ጭምር” በአሽከርካሪዎች ላይ የሚፈጸመው እገታ፣ ዝርፊያና ጥቃት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፤ በስድስት ወር ውስጥ ከ50 በላይ አሽከርካሪዎች በታጣቂዎች ተገድለዋል

በብሩክ አለሙ @Birukalemu21

አዲስ አበባ፣ የካቲት 28/2016 ዓ/ም:– በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች እየተካሄዱ ያሉ ግጭቶች እያስካተሉ ካሉ ዘረፈ ብዙ ጉዳቶች ውስጥ፤ በትራንስፖርት ዘርፍ ላይ በተደጋጋሚ እየደረሰ ያለው ጥቃት አንዱ ሆኗል። በዚህም የተነሳ ከቅርብ አመታት ወዲህ በታጣቂዎች የሚፈጸም የአሽከርካሪዎች እገታ፣ ከመቶ ሺዎች እስከ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ማስከፍል፣ ድብደባ፣ ግድያ እና የንብረት ውድመት ዜና መስማት የተለመደ እየሆነ መጥቷል። በአሁኑ ወቅትም እነዚህ ድርጊቶች ተባብሰው የቀጠሉ በመሆኑ አስጊ ደረጃ ላይ መድረሳቸውን በዘርፉ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። 

በተለይ ባለፉት ሁለት አመታት በኦሮሚያ፣ አማራ እና አፋር በአሽከርካሪዎች ላይ እየደረሰ ባለው ጥቃት በርካታ ሰዎች ሞተዋል፣ ንብርት ወድሟል፤ ይህም ከግለሰቦች አልፎ በአጋሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አስከትሏል እያስከተለም ይገኛል።  

የኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማህበር በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ሸዋ ዞን በተለይም ከወለንጭቴ እስከ አዋሽ ያለዉ መስመር ላይ በተደጋጋሚ በታጣቂዎች የሚደርሰው ጥቃት ከፍተኛ በመሆኑ ስፍራውን “አደገኛ” ሲል ለይቶታል። 

በዚሁ መስመር ላይ በሚገኘው መተሀራ ከተማ አካባቢ ታህሳስ 19 ቀን 2016 ዓ.ም የቁልቢ ቅዱስ ገብርኤልን የንግስ በዓልን ታድመው በመመለስ ላይ በነበሩ ሰዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት ስምንት ሰዎች መገደላቸው ትልቅ ትኩረት ከሳብ ተመሳሳይ መነጋገሪያ እንደነበር ይታወሳል። በጥቃቱ ከተገደሉት በተጨማሪ 10 ሰዎች በታጣቂዎች ታግተው ተወስደዋል። አራት ተሽከርካሪዎችም ተቃጥለዋል።  

ይህን ድርጊት ፈጻሚ ነው በመባል ስሙ የሚነሳው፤ መንግስት “ሸኔ” ሲል በሚጠራው በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (ኦነስ) ታጣቂ ቡድን በቅርቡ ተጠርቷል በተባለው የተሽከርካሪዎች አድማን ተከትሎ በርካታ ተሽከርካሪዎች መቃጠላቸው፣ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ለዘረፋ እና ከፍተኛ እንግልት መዳረጋቸው ተዘግቧል፤ በተንቀሳቃሽ ምስል በማህበራዊ ሚዲያ ተሰራጭቷል።  

ለአዲስ ስታንዳርድ ያነጋገራቸው የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች እና የኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማህበር፤ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች “የታጠቁ አካላት እና የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች በአሽከርካሪዎች ላይ አገታ፣ ዘረፋና ግድያ እየፈጸሙ መሆኑን” ገለጸዋል። 

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ቴዎድሮስ ጥላሁን ከ2004 ዓ/ም ጀምሮ የከባድ መኪና አሽከርካሪ በመሆን እየሰራ ይገኛል። ለ12 አመታት ከጁቡቲ ወደ የኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በማሽከርከር በሚያገኘው ገቢ ራሱን እና ቤተሰቡን በማስተዳድር ቆይቷል። ቴዎድሮስ ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር በስልክ ባደረገው ቆይታ ከቅርብ አመታት ወዲህ በመላ አገሪቱ በአሽከርካሪዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት “እጅግ አሰቃቂ እና የመንግስት ያለህ የሚያስብል” ሲል አሳሳቢነቱን ገልጿል። 

“ታጣቂዎች በዚህ ሰሞን ተሽከርካሪዎችን በማስቆም ለባለንብረቱ በመደወል እስከ 300 ሺህ ብር መቀበል ጀምረዋል” የከባድ ጭነት መኪና አሽከርካሪ ቴዎድሮስ

አሽከርካሪው እንደሚገልጸው በየቦታው የሚደራጁ “ሽፍታዎች” በአሽከርካሪዎች እና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ ነው። ከሶስት ሳምንታት በፊት በአማራ ክልል ወረታ አካባቢ በምትገኘዋ ጎብጎብ ከተማ ሰሊጥ የጫነ አንድ ከባድ ጭነት ተሽከርካሪ መንገድ ዳር ሙሉ ለሙሉ ሲቃጠል ማየቱን ገልጾ “በየቦታው እንዲ አይነት ትዕይንት ማየት የተለመደ ሆኗል” ብሏል።

“በየአካቢው የተደራጁ ወጣቶች መሳሪያ በመታጠቅ ዝርፊያ እና የንብረት ውድመት አለፍ ሲልም ህይወት የማጥፋት ተግባር እየፈጸሙ ነው” የሚለው አሽከርካሪው፤ “ በፍራቻ ይሁን በሌላ ምንክያት ባላውቅም ማህበረሰቡ የታጣቂዎቹ ድርጊት ለማስቆም ሲሞክሮ አላየንም” ሲል ገልጿል።   

በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን፤ ከጋይንት እሰከ ወረታ ያለው መስመር ለአሽከርካሪዎች እግጅ ከባድ ሆኗል የሚለው ቴዎድሮስ በተመሳሳይ ከመተሃራ እስከ ወለንጪቲ እና አዋሽ ያለው መስመር በተደጋጋሚ ከፍተኛ ጥቃቶች የሚፈጸሙበት መሆኑን በመግለጽ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስቧል። 

“አሽከርካሪዎች በተደጋጋሚ እየተፈጸመባቸው ባለው ጥቃት ሳቢያ በስጋት ተሞልተው ነው እየተንቀሳቀሱ ያሉት” ሲል የገለጸው ቴዎድሮስ አመሻሽ 12፡00 ካለፈ መንቀሳቀስ የማይታሰብ ሆኗል ብሏል። 

በአማራ ክልል ኬላ ላይ የታጠቁ አካላት ለአንድ ተሽከርካሪ እስከ አንድ ሺህ ብር በመቀበል ሲያሳልፉ እንደቆዩ የጠቀሰው አሽከርካሪው፤ በዚህ ሰሞን ደግሞ “ተሽከርካሪዎችን በማስቆም ለባለንብረቱ በመደወል እስከ 300 ሺህ ብር መቀበል ጀምረዋል” ሲል ገልጿል።

ከሶስት ሳሞንታት ባፊት በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር አካባቢ በርካታ አሽከርካሪዎች በታጣቂዎች መታገታቸውን በቅርበት እንደሚያውቅ የሚናገረው ቴዎድሮስ በተመሳሳይ ሁኔታ በኦሮሚያ ክልል የሚታገቱ ሾፌሮች ቁጥር በርካታ መሆኑን ተናግሯል።

በኦሮሚያ ክልል በተደጋጋሚ አሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት ከሚፈጸምበት አካባቢ አንዱ መተሓራ ከተማ ነው። አቶ ተስፋዬ ( ለደህነነታቸው ሲባል ስማቸው የተቀየረ) የመተሃራ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ በአካባቢው እየደረሰ ያለውን ጥቃት በተመለከተ ለአዲስ ስታንዳርድ አስረድተዋል። በአካባቢው በርካታ ችግሮች አሉ የሚሉት አቶ ተስፋዬ፤ ሾፌሮችን በማገት ገንዘብ የመቀበል እና ተሽከርካሪዎችን የማቃጠል ድርጊት በየጊዜው እንደሚፈጸም ገልጸዋል።

“ታጣቂዎቹ አሽከርካሪዎችን እና ተሳፋሪዎችን ካገቱ በኋላ ወደ ቤተሰቦቻቸው በመደወል በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እንዲያስገቡ ያዛሉ፤ ያለበለዚያ ታጋቹ እንደሚገድሉት ይነግሯቸዋል። የተባለውን ገንዘብ ያላስገባ የቤተስብ አባል ታጋቹን ያለ ርህራሄ ይገድሉታል” ብለዋል። በቅርቡ በርካታ ሰዎች መታገታቸው ገልጸው ግማሾቹ ገንዘብ ከፍለው የተለቀቁ ሲሆን እስካሁን ያልተለቀቁም መኖራቸውን ጠቁመዋል።

አቶ ተስፋዬ፤ በቅርበት በሚያውቁት አሽከርካሪ በ2015 በታጣቂዎች ታግቶ እጅግ አሰቃቂ ጉዳት ካደረሱበት በኋላ ለቤተሰቡ ደውለው 400 ሺህ ብር ጠይቀው ተከፍሎለት መለቀቁን ገልጸዋል። 

በቅርቡም አንድ የፋንታሌ ወረዳ የካቢኔ ልጅ ለህብረተሰቡ ውሃ ለማድረስ በማሽከርከር ላይ እያለ በታጣቂዎች ከተያዘ በኋላ መገደሉን ገለጸዋል። ታጣቂዎቹ ግለሰቡን የገደሉት እነሱ ያሉትን ተፈጻሚ ባለማደረጉ ነው የሚሉት አቶ ተስፋዬ አስክሬኑን ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ፖስት ተደርጎ መታየቱንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ላይ “ሽፍቶች እና የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች” ዘረፋ፣ እገታና የንብረት ውድመትን ጭምሮ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱባቸው_ የኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ዘውዱ

ከመተሃራ ወጣ ብሎ፤ ኢላላ ከሚባል ቦታ ጀምሮ እስከ አዋሽ መግቢያ ድረስ በተደጋጋሚ ጥቃቶች እንደሚፈጸም የገለጹት አቶ ተስፋዬ ከአንድ አመት በፊት አዋሽ መግቢያ አካባቢ የቆርቆሮ ፋብሪካ ሰራተኞች የሆኑ የቻይና ዜጎች ታግተው ሶስት ሚሊዮን ብር ከፍለው መለቀቃቸውን አስታሰዋል። 

ታህሳስ ወር ላይ ሁለት ተሽከርካሪዎች በታጣዎች መቃጠላቸውንም አክለው የገለጹት የመተሓራ ነዋሪው፤ ይህን ተከትሎ መንግስት መከላከያ ሰራዊት በቦታው ቢያሰማራም ጥቃቶቹ ግን አለመቆማቸውን አስረደተዋል። 

መስመሩ እጅግ አደገኛ ከመሆኑ የተነሳ አሽከርካሪዎቹ ሌሊት የሚያደርጉትን ጉዞ በማቆ ጠዋት ላይ ተጠባብቀው መሄድ መጀመራቸውን የጠቀሱት ነዋሪው ይህም መንገዱ እንዲዘጋጋና እንዲጨናነቅ አድርጓል በማለት ገልጸዋል። 

አቶ ተስፋዬ የጥቃት አድራሾቹን ማነነት በተመለከተ በሰጡት ምላሽ፤ “ማህበረሰቡ ውስጥ ያሉ ስራ አጥ ወጣቶች ናቸው ቀድሞውኑ ጫካ ከነበሩ ታጣቂዎች ጋር በመተባበር እየዘረፉ ያሉት” ብለዋል። ጥር ወር በፈንታሌ ወረዳ ሳራዊ ቀበሌ በጫካ ከመሸጉ ታጣቂዎች ጋር ሲሰሩ የነበሩ 69 ሰዎች እጅ መስጠታቸውን ገልጸዋል።

አቶ ተስፋዬ እንደገለጹት ይህን ድርጊት ሲያቀናብር የነበረው የመንግስት ሰራተኛ ( የአካባቢው ዲኤ ሰራተኛ) ነው። ግለሰቡ በጸጥታ አካላት በቁጥጥር ስር መዋሉን እና ማስተማሪያ እንዲሆን በሚል በሚሰራበት መስሪያ ቤት ስብሰባ ላይ እንዳቀረቡት ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።   

የኢትዮጵያ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ዘውዱ በበኩላቸው በመላ አገሪቱ በሚባል ደረጃ  አሽከርካሪዎች ላይ ከባድ አደጋ እየደረሰ መሆኑን ገልጸው ነገር ግን እጅግ የከፋው በኦሮሚያ ክልል ነው ብለዋል።  

የማህበሩ ስራ አስኪያጅ፤ ከጁቡቲ ወደብ ለኢትዮጵያ ጠቃሚ የሆኑ አቃዎችን በመጫን በመላ አገሪቱ በሚጓዙ የኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ላይ “ሽፍቶች እና የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች” ዘረፋ፣ እገታና የንብረት ውድመትን ጭምሮ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱባቸው መሆኑን ገልጸዋል። 

አቶ ሰለሞን ገለጻ፤ አፋር እና ኦሮሚያ ላይ ያለው ሁኔታ እጅግ የከፋ ነው።  አፋር ላይ አየደረሰ ያለውን ችግር ሲያስረዱ “የታጠቁ ሰዎች አስከርካሪዎችን ያስቆሙና በማስፈራራት ገንዘብ አምጡ ይላሉ፤ ገንዘብ ካልሰጧቸው የተላያዩ እርምጃዎችን ይወስዳሉ” ብለዋል። ኦሮሚያ ላይ የሚደርሰው ጥቃት ተመሳሳይ ነው ሲሉ ያብራሩት አቶ ሰለሞን፤ “ የተደራጁ ታጣቂዎች ሰዎችን አግተው በመውሰድ ለቤተሰብ በመደወል ገንዘብ ይጠይቃሉ። ቤተሰብ የተባለውን ገንዘብ ካላሟላ የሚፈለጉትን እርመጃዎች ይወስዳሉ” በማለት ገለጸዋል። 

“የሾፌሮቹ ደመወዝ 5 ሺህ የማይበልጥ ነው፤ ነገር ግን ታጣቂዎቹ አግተው የሚጠይቁት በመቶ ሺዎች ነው። የተባሉትን ብር ከፍለውም የተገደሉ አሉ” ብለዋል።

“በዚህ አመት ብቻ (በስድስት ወር ውስጥ) ከ53 በላይ አሽከርካሪዎች በታጠቁ አካላት የተገደሉ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 80 በመቶ የሚሆኑት በጁቡቱ መስመር ላይ ( በተለይ ወለንጪቲ እና መተሃራ መካከል)  የተገደሉ ናቸው”_ የኢትዮጵያ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማህበር የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢው አቶ አዲስ አለማየሁ

በኦሮሚያ ክልል ከወለንጪቲ እስከ አዋሽ ባለው መስመር ላይ በተደጋጋሚ “መኪኖች ይቃጠላሉ፣ ሾፌሮች ይታገታሉ ወይም ይገደላሉ” ሲሉ የገለጹት የኢትዮጵያ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን፤ ከሁለት ወር በፊት መተሓራ አካባቢ አራት መኮኖች በታጣቂዎች መቃጠላቸውን እና ሾፌሮች መታገታቸውን አታውሰዋል፣ 

በአሁኑ ወቅት ዝርፊያዎች እና የተለያዩ ጥቃቶች በቀን እየተፈጸሙ መሆኑን ገልጸው፤ ታጣቂዎቹን ለማምለጥ የሚሞክሩ አሽከርካሪዎች አደጋ እያደረሱ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ አቶ ሰለሞን ገለጻ ባላፉት ጥቂት አመታት ውስጥ የበርካታ ሾፌሮች ህይወታቸው አልፏል፣ የቆሰሉ ከስራ የተፈናቀሉም አሉ፤  በርካታ የመንግስት እና የህዝብ ሃብት የሆነ ንብረት ወድሟል።

ጉዳት በማድረስ ላይ ያሉት ታጣቂዎች ማንነት ይታወቃል? ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ ማንነታቸው እንደማይታወቅ ተናግረዋል። ነገር ግን “የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች የድምብ ልብስ የለበሱ ታጣቂዎች ተሽከርካሪዎችን በማስቆ ዝርፊያ እንደሚፈጽሙ” ገልጸዋል።

አንደዚህ ያሉ ጥቃቶች በሁሉም አካባቢዎች መኖራቸውን የጠቆሙት የማህበሩ ስራ አስኪያጅ ስጋቱ ከፍተኛ በመሆኑ ተሽከርካሪዎች እየተደዋወሉ መንገዱ ሰላም መሆኑን መረጃ እየተለዋወጡ እንዲጓዙ አያደረን ነው ብለዋል። እነዚህ ድርጊቶች በአማራ ክልል እንዲሁም በደቡብ አካባቢ እንደሚፈጸሙ አስታወቀዋል። 

ማህበሩ ችግሩን ለሚመለከተው አካል ማሳወቁን ገለጸው መከላከያ ሰራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የኦሮሚያ ፖሊስ እንዲሁም የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር ችግሩን ለመፍታት ትብብር አያደረጉልን ነው ሲሉም አክለዋል። 

የኢትዮጵያ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማህበር የስራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ አዲስ አለማየሁ በበኩላቸው በታጣቂዎች የታገቱ በርካታ አሽከርካሪዎችን ተደራድረው ማስለቀቃቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጽዋል። “ከአንድ ወር በፊት ወለንጪቲ እና መተሃራ መካከል 15 አሽከርካሪዎች ታግተው ነበር። ገንዘብ በእርዳታ አዋጥተን እኔ ከታጣቂዎቹ ጋር በስልክ ተደራድሬ ከፊሎቹን አስለቅቀናል። ያልተከፈለላቸው ደግሞ ተገድለዋል” ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል። 

“በታጣቂዎች ከታገቱት 15ቱ አንዱ የእኔ የቅርብ ጓደኛ ነበር” ያሉት አቶ አዲስ፤ “ታጋቹ ደውሎልኝ 500 ሺህ ብር ከከፈልክ ትለቀቃለህ በለውኛል፤ ሌሎቹ የለንም ብለው እየተገረፉ ነው፤ ባለቤቴ ብሩን ታስገባ በሎኝ 500 ሺህ በባንክ ለታጣቂዎቹ አስገባን” ብልዋል። አክለውም “ብሩን ካስገባን በኋላ ለመንግስት አካላት አሳውቀን መከላከያ ሠራዊት ተከበው ተኩስ ተከፈተ፤ በተኩስ ልውውጡ ብሩ የተከፈለለት ጓደኛዬ እና ሌላ አንድ ሾፌር ተገደሉ፤ የተቀሩት አስራ ሶስቱ ተረፉ” በማለት ገልጸዋል። 

በተጨማሪም “የሚድመው ንብረት ቁጥር ስፍር የለውም” የሚሉት ምክትል ሰብሳቢው፤ “የመንግስት ኃይሎች ካሉበት አንድ ኪሎሜትር ርቀት ላይ በታጣቂዎች ዝርፊያ ይፈጸማል” ሲሉ ገልጸው፤  “ምን ማድረግ እንዳለብን ግራ ገብቶናል” ሲሉ የችግሩን አሳሳቢነት ገልጸዋል።

“በዚህ አመት ብቻ (በስድስት ወር ውስጥ) ከ53 በላይ አሽከርካሪዎች በታጠቁ አካላት መገደላቸውን” የማህበሩ የስራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢው አቶ አዲስ አለማየሁ ገልጸው፤ ከዚህ ውስጥ 80 በመቶ የሚሆኑት በጁቡቱ መስመር ላይ ( በተለይ ወለንጪቲ እና መተሃራ መካከል)  የተገደሉ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

የማህበሩ የስራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ እና የከባድ መኪና አሽከርካሪ የሆኑት አቶ አዲስ፤ “ከኢ-መደበኛ ታጣቂዎች በተጨማሪም የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች በአሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት እና ዘረፋ እየፈጸባቸው ነው” ብለዋል። 

የጸጥታ ኃይሎቹ በሾፌሮች ላይ በሆነ ባልሆነ ምክንያት ድብደባ እንደሚፈጽሙባቸው ገልጸው “ለምሳሌ በአፋር ክልል የመንግስት ታጣቂ ኃይሎች ኬላ ዘርግተው ሾፌሮችን በማስቆም ዝርፊያ እየፈጸሙ ነው፤ ይህ ስም ማጥፋት አይደለም፤ ትክክለኛ መረጃ ያለው እውነት ነው” በማለት ገልጸዋል። 

በክልሉ ወጣቶችም ተደራጅተው ድርጊቱን በመፈጸም ላይ መሆናቸውን አክለው የገለጹት አቶ አዲስ፤ ሆን ብለው እንሰሳትን፣ ያረጁ ሳይሎች፣ ሞተር ሳይሎች እንዲሁም ባጃጆች በማስገጨት ከሚያወጡት ዋጋ ከእጥፍ በላይ እንደሚቀበሉ በመግለጽ አሽከርካሪዎቹ ላይ እየደረሰ ያለው ፈተና በአንድ ጉዳይ ላይ የተወሰነ አለመሆኑን አስረድተዋል። 

“የጸጥታ ኃይሎችም ዘረፋ ፈጻሚዎች ናቸው፤ መተሃራ አካባቢ በሚገኘው ቦታ ላይ ጥበቃ የሚያደርጉ የኦሮሚያ ክልል ፖሊሶች ከአሽከርካሪዎች ገንዘብ ያለአግባብ እንደሚውስዱ አውቃለሁ”_ የማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ ደረጀ ሲሳይ

በኦሮሚያ ክልልም ተመሳሳይ ችግር መኖሩን ጠቆመዋል። “በኦሮሚያ ክልል እገታ፣ ዝርፊያ እንዲሁም ግድያ የሚፈጸመው የመንግስት የጸጥታ ኃይል ልብስ (የመከላከያ ሠራዊት እና የፌዴራል ፖሊስ) በለበሱ አካላት ነው” ያሉት አቶ አዲስ፤ ድርጊቱን የሚፈጽሙት ታጣቂዎች የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላትም፤ ትክክለኛ የጸጥታ አካላት ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠቁመዋል። 

መስከርም ወር በራሳቸው የደረሰውን ክስተት ለአዲስ ስታንዳርድ ሲያስረዱም “እያሽከረከርኩ እያለሁ የመከላከያ ሠራዊት ልብስ የለበሱ ሰዎች አስቁመው ከመኪናው አስወርደው እንድበረከክ አደረጉኝ። ምን አጥፍቼ ነው? እኔ መንደገኛ ብቻ ነኝ ብዬ ጠየኳቸው። እርስዎ ትልቅ ሰው ነዎት ለዛሬ ሂዱ ነገር ግን ክዚህ በኋላ ተመልሰው ቢመጡ ይገደላሉ በማለት አስጠንቅቀው ለቀቅቁኝ” ብለዋል።  

በተመሳሳይ መልኩ በቅርቡ በአማራ ክልል ፍኖተ ሰላም ከተማ አካባቢ በፋኖ ታጣቂዎች መያዛቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ የገለጹት የአሽከርካሪዎች ተወካዩ፤ “ጅጋ ከተማ ለአንድ ሳምንት አቆይተውኝ ጉዳት ሳያደርሱብኝ ለቀውኛል” ብለዋል።

በኦሮሚያ ክልል ከምዕራብ ሸዋ አንስቶ እስከ አሶሳ ቀን በቀን ዝርፊያ አለ የሚሉት አቶ አዲስ፤ ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ ከምትገኘው ከፊቼ ወጣ ብሎ ቱሉ ሚልኪ፣ ጎሃ ጺዮን አካባቢ በየቀኑ ጥቃትና ዝርፊያ ይፈጸማል ብለዋል።  ወለንጪቲ እና መተሃራ መካከል ያለው መስመር ደግሞ “እጅግ አደገኛ” ሆኗል ሲሉ ገልጸው ወልቂጤ እና ቡታጅራም አልፎ አልፎ ይከሰታል” ሲሉ እጅግ አስጊ ያሏቸው ቦታዎች ዝርዝረዋል። 

በተለይ ባለፉት ሁለት አመታት ችግሩ እጅግ መባባሱን እና ዘረፋዎች በሁሉም አይነት ተሽከርካሪዎች ላይ እንደሚፈጸም አስታውቀዋል። ከከባድ መኪና ተሽከርካሪዎች በተጭማሪ፤ እንደ አይሱዙ ያሉ የጭነት ተሽከርካሪዎች እና የህዝብ ማመላለሻ መኪኖች ጥቃቱ ሰለባ ናቸው ብለዋል። 

“መንግስት ያስታጠቃቸውን አካላት ሃይ ሊል ይገባል” ያሉት የአሽከርካሪዎች ተወካዩ፤ “ያለአግባብ ከማኪና አስወርደው የሚደበድቡ፣ ገንዘብ የሚደራደሩ ኃይሎቹን ማስቆም አለበት” ሲሉ ጠይቀዋል። ማህበሩ ይህንን ለመንግስት አካላት በተደጋጋሚ ቢያሳውቅም የመጣ ለውጥ አለመኖሩን አክለው አስረድተዋል። 

አቶ ደረጀ ሲሳይ የማህበሩ ፕሬዝዳንት ሲሆኑ፤ ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር በስልክ ባዳረጉት ቆይታ ባሁኑ ወቅት አገሪቱ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ መሆኗን ገልጸው አሽከርካሪዎች የዚህ ገፈት ቀማሽ ከሆኑት ውስጥ ይገኛሉ ብለዋል። 

ለአሽከርካሪዎች የሚሰጠው ክብር ዝቅ ያለ መሆኑን የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ፤ “መንግስት ያሰማራቸው የጸጥታ ኃይሎች በታጣቂዎች ከሚድርስባቸው ጥቃት አላዳናቸውም” ብለዋል። የጸጥታ ኃይሎች ባሉበት ቅርብ ርቀት ላይ ሳይቀር ቀን በቀን መኪና ይቃጠላል፣ ይዘረፋል፣ ሰዎች ይታገታሉ፣ ጉዳት ይደርስባቸዋል በማለት ገልጸዋል።

“የጸጥታ ኃይሎችም ዘረፋ ፈጻሚዎች ናቸው” ያሉት አቶ ደረጀ “ከመተሃራ ወደ አዲስ አበባ በሚሰደው መንገድ ላይ 20 ኪሎ ሚትር ርቅት ላይ በሚገኘው ቦታ ላይ ጥበቃ የሚያደርጉ የኦሮሚያ ክልል ፖሊሶች ከአሽከርካሪዎች ገንዘብ ያለአግባብ እንደሚውስዱ አውቃለሁ” ሲሉ ፖሊሶች በህገ ውጥ ተግባር ላይ መሰማራታቸውን አስታውቀዋል። 

ከአዲስ አበባ 70 ኪሎ ሜትር ገደማ፤ ቱሉ ቦሎ አካባቢ ተሽከርካሪዎች መቃጠላቸውን አክለው የጠቆሙት የማህበሩ ፕሬዝዳንት፤ አፋር እና አማራ ክልልም ያለው ችግር ተመሳሳይ መሆኑን ተናግረዋል። 

በሶማሌ ክልልም በተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት እና ዝርፊያ የሚፈጸም መሆኑን በክልሉ የሚንቀሳቀሰው የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) ገልጿል። 

ፓርቲው የካቲት 18 ቀን 2016 ዓ/ም ባወጣው መግለጫ በሱማሌ ክልል በሲቪል ተሽከርካሪዎች ላይ “ዒላማ ያልለየ ተኩስ”  እየተፈጸመ መሆኑን ገልጾ በዚህም የንጹሃን ሰዎች ህይወት መጥፋት እና ጉዳት ድርሷል ብሏል። 

ድርጅቱ ማንነታቸውን ባለጠቀሳቸው አካላት በተሽከርካሪዎች ላይ እየተፈጸመ ነው ያለውን “ተኩስ እና በእንስሳትና ሸቀጦች የመውረስ ርምጃ” አውግዟል። ኦብነግ፣ ድርጊቶቹ የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶችን የሚጥሱ እና ኢኮኖሚያዊ መረጋጋትን የሚያጠፉ ናቸው ሲል ገልጿል።  የዘፈቀደ ተኩሱ እና ንብረት የመውረሱ ድርጊት ባስቸኳይ እንዲቆም እና የፌደራሉና የክልሉ መንግሥታት የሕግ የበላይነትን እንዲያከብሩ ፓርቲው ጠይቋል።

የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ያለው ተጽዕኖ

ከባድ ጭነት ተሽከርካሪዎች ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት፤ የህዝብ ማማላለሻ ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ላይ እያስከተለ ያለው ተጽዕኖ ቀላል አለመሆኑን በስማቸው እና ማህበራቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የህዝብ ማማላለሻ አክሲዮን ማህበር የህዝብ ግንኝነት ኃላፊ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል። 

የህዝብ ማማላለሻ ተሽከርካሪዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ከከባድ ጭነት ተሽከርካሪዎች በአንጻራዊነት ያነሰ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፤ የዚህ ምክንያት፤ አገግሎት የሚሰጡበት ሰዓት ልዩንት ያለው መሆኑ እና የህዝብ ማማላለሻ ተሽከርካሪዎች ክልሎችን በማቋረጥ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የተወሰነ በመሆኑ ነው ብለዋል።

በተሽከርካሪዎች ላይ በሚደርሱ ጥቃቶች የተነሳ የተሳፋሪዎችን እንቅስቃሴ ገድቦታል ያሉት የህዝብ ግንኝነት ኃላፊው፤ ታጣዎቹ በሚያወጡት የጉዞ እገዳ አስከርካሪዎቻችን ለአደጋ እንዲጋለጡ እና በስጋት ውስጥ ሆነው እንዲያሽከረክሩ አድርጓል ብለዋል። 

“አገልግሎት በመስጠት ላይ ያለነው ከስጋት ነጻ ሆነን አይደለም፤ በአሁኑ ወቅትም የስጋት መጠንን በመገምገም ነው እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ያለነው” ሲሉ በታጣቂዎች የሚሰነዘረው ጥቃት፤ በህዝብ ማማላለሻ ተሽከርካሪዎች ላይም ተጽዕኖ እያደረስ መሆኑን አመላክተዋል። 

ከጥቂት ሳምንታት በፊት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ከፋና ቴሌቪዥን ጋር አድርገውት በነበረ ቆይታ፤ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የዕገታ ድርጊት ተባብሶ መቀጠሉን አረጋግጠዋል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ሰዎችን በማገት ገንዘብ መጠየቅ እየተለመደ መጥቷል ብለዋል። ድርጊቱ ማህበረሰቡን ለተለያዩ ቀውሶች እየዳረገ መሆኑንም ኮሚሽነር ጄኔራሉ አብራርተዋል፡፡

ከዕገታ ጋር ተያይዞ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ለገንዘብ ወይም ለፖለቲካ ዓላማ ማስፈፀሚያ የሚውሉ መሆናቸውን የገለጹት  ኮሚሽነር ጄኔራሉ፤ ድርጊቱን መንግስት የሚፈፅመው ለማስመሰል በመንግስት የፀጥታ መዋቅር ውስጥ የሚገኙ ግለሰቦችን በመጠቀም የሚፈፀም መሆኑን በተደጋጋሚ በተደረገ ምርመራ መረጋገጡን አስረድተዋል።

ኮሚሽነር ጄኔራሉ፤ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች አሁንም ይህ ድርጊት ተባብሶ መቀጠሉን ጠቁመው፤ በድርጊቱ የተሳተፉ ግለሰቦችን ተከታትሎ ለመያዝ እና በእገታው የተከፈለውን ገንዘብ ለማስመለስ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በአሽከርካሪዎች ላይ የሚደርሰው ዝርፊያ፣ ግድያ እና የንብረት ውድመት በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚያስከትለው ተጽዕኖ

ከጁቡቲ ወደብ እጅግ ጠቃሚ የሆኑ አቃዎችን በመጫን መላ ኢትዮጵያን የሚያካልሉት የከባድ ጭነት ተሽከርካሪዎች ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ትልቁ ድርሻ እንደሚወጡ ይታወቃል። ነገር ግን በተለይ ባለፉት ሶስት እና አራት አመታት በተሽከረካሪዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት እየተበራከተ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ተከትሎ አሽከርካሪዎቹ ከጁቡቲ ወደብ ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ እየተገደበ እንደሚገኝ በዘርፉ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። 

ይህም በኢኮኖሚው ላይ የሚያድርሰው አሉታዊ ተጽዕኖ ቀላል የሚባል አለመሆኑን የኢትዮጵያ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ዘውዱ ገልጸዋል። 

ኢትዮጵያ በውጭ ምንዛሬ እጥረት እየታገለች ባለችበት ወቅት ተሽከርካሪዎቹ ይዘውት የሚመጡት ሀብት እና ንብረት እየወደመ ነው ብለዋል። ይህም የዋጋ ንረትን በማስከተል አገሪቱ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ እንድትወድቅ ያደርጋል፤ እያደረገም ነው ሲሉ ገልጸዋል። በተለይ ኢትዮጵያ የጁቡቲን ወደብ ብቻ የምትጠቀም አገር እንደመሆኗ ኮሪደሩ ላይ እየተከሰቱ ያሉት ችግር ካተቀረፉ በኢኮኖሚ ብቻ ላይ ሳይሆን ፖለቲካዊና በማህበራዊ ህይወት ላይ የሚደርሰው ጫና ከፍተኛ መሆኑን አሳስበዋል። 

ይህን ጫና ለመቀነስ በየደረጃው ያሉ የመንግስት የጽጥታ አካላት አሽከርካሪዎች በሚነቀሳቀሱበት ወቅት አስፈላጊውን ጥበቃ እና ክትትል ሊያደርጉላቸው እንደሚገባ ያሳሰቡት ስራ አስኪያጁ የመንገድ ቁጥጥር አካላትም አደጋ እንዳይደርስ መቆጣጠር እንጂ አላስፈላጊ የሆኑ ገንዘብ መጥየቅ እንዲያቆሙ ጠይቀዋል። 

የኢትዮጵያ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማህበር የስራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ አዲስ አለማየሁ በበኩላቸው የዜጎች የመንቀሳቀስ መብት አደጋ ላይ መውደቁን ጠቅሰው ድርጊቱ ሰዎች ውጥተው ሰርተው መብላት እንዳይችሉ አድርጓል ብለዋል።  ይህም የመንግስት ገቢን በመቀነስ ረገድ ድርሻው ቀላል አለመሁንን እንዲሁም በመላ ማህበረሰቡ ላይ የሚያደርሰው ተጽዕኖ ከባድ መሆኑን አስረድተዋል።

በኦሮሚያ ክልል የፈንታሌ ወረዳ በአሽከርካሪዎች ላይ እያደረሰ ያለውን ጥቃት በተመለከተ፤ የወረዳው ፖሊስ መመሪያ ኃላፊ ኢንስፔክተር ተመስገን እና ምክትላቸው ኢንስፔክተር ሙሉነህ፤  ምላሽ እና ማብራሪያ እንዲሰጡን ላቀረብንላቸው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረታቸው የወረዳውን ፖሊስ አስታየት ማካተት አልቻልንም። 

በተመሳሳይ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት እና የፌዴራል ፖሊስ ህዝብ ግኑኝነት ኃላፊን እንዲሁም የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስቴርን ለማግኘት ያደረኘው ሙከራ አለተሳካም። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button