ፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: “ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ወደ ሶስተኛው ምዕራፍ መሸጋገሩን በይፋ አበስራለሁ” – የምክክር ኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21/2016 ዓ.ም፡-የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በክልል ደረጃ የሚደረገዉ የምክክር ምዕራፍ በአዲስ አበባ ከተማ ዛሬ ግንቦት 21 ቀን 2016 ዓ.ም ማስጀመሩን አስታወቀ።

አጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍ ላይም በአዲስ አበባ ከሚገኙ 119 ወረዳዎች የተውጣጡ የማህበረሰብ ተወካዮች በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን መረጃ ያሳያል። ከመዲናዋ የተወከሉ መሆናቸው የተገለጹ ተሳታፊዎች ቃለ መሃላ መፈጸማቸው ተገልጿል።

የመድረኩን የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፤ ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ወደ ሶስተኛው ምዕራፍ መሸጋገሩን በይፋ አብስረዋል።

ከበርካታ አካላት የገለልተኝነት እና አካታችነት ጥያቄዎች ቢነሱበትም ኮሚሽነሩ “በዛሬው እለት የተጀመረው የምክክር ምዕራፍ በቀጣይ ለሚከናወነው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ስኬታማነት ቁልፍ ሚና የሚኖረው መሆኑን” ገልጸዋል።

በአዲስ መንገድ በምከክር ችግሮችን መፍታት የግድ ስለመሆኑ ያነሱት ዋና ኮሚሽነሩ፤ ስር የሰደዱ ሀገራዊ ችግሮችን በስክነት በመመካከር መፍታት አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው ብለዋል።

በምክክርና በሃሳብ ልእልና ችግሮችን መፍታት መቻል ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ ሀገራዊ መፍትሄ መሆኑን ጠቅሰው ተወካዮችም ለዚሁ ስኬት አሻራችሁን የምታሳርፉበት ልዩ ታሪካዊ አጋጣሚ ነው ብለዋል።

ኮሚሽኑ እዚህ ምዕራፍ ላይ ደርሻለሁ ቢልም ከሀገሪቱ ዋና ዋና የፖለቲካ ፓርቲዎች ከፍተኛ ትችት እና ተቃውሞ ተሰንዝሮበታል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ አስራ አንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ያቀፈው የተቃዋሚ ፓርቲዎች ካውከስ ኮሚሽኑ “አካታች” የሆነ አገራዊ ውይይትን ለማሳለጥ አላማ አንግቦ ቢመሰረትም አላሳካም ሲል ተችቷል።

ኮውከሱ ለአዲስ ስታንዳርድ በላከው መግለጫ ኮሚሽኑ በህዝቦች መካከል ፍትህን፣ ሀገራዊ አንድነት፣ መግባባትን እና እርቅን ለማስፈን በሚል አላማ ቢቋቋምም በገዥው ፓርቲ “ፖለቲካ ፍጆታ” እየሰራ ነው ሲል ኮንኗል።

ኮሚሽኑ በመዲናዋ ይካሄዳል ያለው ምክክሩ ለሰማንት (ከግንቦት 21-27 ቀን 2016 ዓ.ም) እንደሚቆይ አስታውቋል።

ኮሚሽኑ ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባስጀመረው የምክክር ምዕራፍ መድረክ ላይ ከ200 ሺ በላይ የአጀንዳ ልየታና የምክክር ተሳታፊዎች፣ 11 ሞደሬተሮች፣ 121 ተባባሪ አካላት እና 45 በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች እየተሳተፉ ይገኛሉ ብሏል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button