ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: ህወሓት በ50 አመታት ታሪኬ አጋጥሞኝ የማያውቅ ፈተና ውስጥ ነኝ አለ፣ በቀጣይ ሳምንታት የፓርቲ ጉባኤየን ለማካሄድ ወስኛለሁ ብሏል

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10/2016 ዓ.ም፡- የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ለ11 ቀናት ሳካሂደው የነበረው የፓርቲው ከፍተኛ አመራር ስብሰባ እና ግምገማ አጠናቅቂያለሁ ሲል ዛሬ ሐምሌ 9 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።

ሳካሂደው የሰነበትኩት በፓርቲው አመራራ ላይ ያተኮረ የ11 ቀናት ስብሰባ እና ግምገማ “ፓርቲውን ከመበታተን ሊታደግ የሚችል ጉባኤ እንዲካሄድ ምቹ ሁኔታዎችን የፈጠረ ነው” ብሏል።

በያዝነው ሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም ባሉት ቀጣይ ጥቂት ሳምንታት የፓርቲ ጉባኤ ይካሄዳል ሲል የገለጸው የህወሓት መግለጫ “ብሔራዊ ህልውናችንን ማረጋገጥ ቀዳሚ ተልኳችን ነው” ሲል አስታውቋል።

በፓርቲው የተሰየመው የ14ኛ ጉባኤ አዘጋጅ ኮሚቴ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር በተያዘው ሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም ጉባኤው አንዲካሄድ በቅርብ ቀናት ውስጥ ይፋ እንዲያደርግ ሲል አሳስቧል። ጉባኤው “እንዳይካሄድ ሊያደርግ የሚችል ምንም አይነት ምክንያት የለም” ሲል መወሰኑን አስታውቋል።

ጉባኤው እንዳይካሄድ ለማደናቀፍ የሚጥሩትን በሁሉም መንገድ እንታገላለን ብሏል።

አሁን “በፓርቲው የማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ ያጋጠመው ችግር ድርጅቱ ከተመሰረተ ጀምሮ ባሉት 50 አመታት አጋጥሞኝ አያውቅም” ያለው ህወሓት ዋነኛ የለየኋቸው ችግሮቼ “ቡድንተኝነት፣ ፀረ ዲሞክራሲያዊነት፣ ጎጠኝነት እና ሙስና ወደ ላቀ ደረጃ አድጎ ፓርቲውን አላፈናፍን ከማለት ባለፈ የመፈራረስ አደጋ ደቅነውብኝ ነበር” ብሏል።

እዚህ ያደረሰኝ ዋነኛ ምክንያት “በፓርቲው ውስጥ ከህዝባዊ መስመር የወጣ በጥቅም አመለካከትና ተግባር የተሰባሰበ ቡድን ስለተፈጠረ” ነው ሲል ገልጿል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የፓርቲው ከፍተኛ አመራር ሁሉም በሚባል መልኩ ተስማምቶበታል ያለውን ባለ 11 ነጥብ የአቋም መግለጫ ይፋ አድርጓል።

በመግለጫው ከተጠቀሱት መካከል የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት አንዱ ሲሆን “የፕሪቶርያውን የሰላም ስምምነት የትግላችን ውጤት በመሆኑ የሰላማዊ መንገድ ትግላችን ሰነድ አድርገን እንቀሳቀሳለን” ሲል አስታውቋል።

የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት አፈጻጸም ጥሩ በሚባል ጅማሮ ላይ ቢሆንም በተያዘለት ግዜ ተፈጻሚ አለመሆኑ የጠቆመው የህወሓት መግለጫ “የተፈናቀለ ህዝባችን ሙሉ በሙሉ ወደ ቀየው የመመለሱ ስራ እና የትግራይ ሉዐላዊ የግዛት ወሰን በስምምነቱ መሰረት አለመተግበር ያልተሻገርናቸው ችግሮች ናቸው” ብሏል። የዚህም ዋነኛ ምክንያት በአንድነት ላይ የተመሰረተ እና የተደራጀ አመራር ያልተሳተፈበት በመሆኑ ነው ሲል ገልጿል።  

በዚስብሰባው እና ግምገማ መድረኩ ላይ መገኘት ከነበረባቸው 1111 ከፍተኛ ኣመራሮች ውስጥ 1032 (93 በመቶ) የሚሆኑ በየደረጃው ያሉ አመራሮች መሳተፋቸውን አስታውቋል።

ፓርቲያችን ህወሓት በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ዕውቅና አግኝቶ የተደራደረ፣ የስምምነቱን ውል የፈረመ ፓርቲ ነው ያለው መግለጫው የፓርቲው ህጋዊ እውቅናው በፖለቲካዊ ድርድር እና ውሳኔ እንዲመለስለት ለማስቻል ለአደራዳሪዎቹ እና ለፌደራል መንግስቱ ጥሪውን አቅርቧል፤ ለተፈጻሚነቱ ሰላማዊ እና ዲፕሎማሲያዊ መንገዶችን ለመጠቀም ቃል ገብቻለሁ ብሏል።

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button