ማህበራዊ ጉዳይዜና
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ ለአጋቾቹ የምንከፍለው ገንዘብ ስለሌለን በየገበያው እና በየመንደሩ እየለመንን ነው የምንገኘው_ የታጋቾች ቤተሰቦች

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13/ 2016 ዓ/ም፦ ከሁለት ሳምንት በፊት በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በገርበ ጉራቻ ከተማ አቅራቢያ በታጣቂዎች ታግተው የሚገኙ ተማሪዎችን ለማስለቀቅ፤ አጋቾቹ የጠየቁትን ገንዘብ ለመክፍል የድጋፍ ደብዳቤ በማጻፍ በልመና ላይ እንደሚገኙ የታጋቾች ቤተሰቦች ገለጹ።

ባለፈው ሰኔ ረቡዕ ሰኔ 25 ቀን 2016ዓ.ም በአማራ ክልል ከሚገኘው የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ተነስተው ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ላይ እያሉ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ገርበ ጉራቻ ከተማ አቅራቢያ በታጣቂዎች ከታገቱ ከ150 በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች መካከል እስከአሁን ያልተለቀቁ መኖራቸውንና በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ እንደሚገኙ የታጋች ቤተሰቦች ለአዲስ ስታንዳርድ ገልፀዋል::

አዲስ ስታንዳርድ ያነጋገራቸው የታጋቾች ቤተሰቦች እንደገለፁት ከሆነ የተጠየቁትን ክፍያ ከፍለው የተለቀቁ ተማሪዎች ቢኖሩም ገንዘቡን መክፈል ያልቻሉ ግን እስከአሁን ድረስ በታጣቂዎች ተይዘው እንደሚገኙ አስታውቀዋል::

ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የታጋች እህት ረቡዕ ሰኔ 25 ቀን 2016 ዓ.ም የታገተች እህታቸው እስከአሁን እንዳልተለቀች ተናግረዋል::

“ያለብር የሚያስለቅቅ ምንም አካል የለም:: እኛ ብር እያሰባሰብን ነው ያለነው:: እህቴን ትላንትም ዛሬ ጠዋትም አውርቻታለሁ:: ታስራ ነው ያለችው:: ከእሷ ጋራ የነበሩ 4የሚሆኑ ሰዎች የተጠየቁትን እስከ አንድ ሚሊየን የሚደርስ ገንዘብ ከፍለው ወጥተዋል:: እኛ የምንከፍለው ስለሌለን ከወረዳው የድጋፍ ደብዳቤ አጽፈን በየገበያው እና በየመንደሩ እየለመንን ነው የምንገኘው” ሲሉ ገልጸዋል።

“ገንዘቡ የሚሞላልን ከሆነ አጋቾቹ የሚያዘጋጁት ሰው አለ:: ለሱ ሄደን እናስረክባለን:: ከዛ ልጅቷን ወደ እኛ ያመጣሉ:: ይህን እንድናደርግ ነው አጋቾቹ መመሪያ የሰጡን::” ሲሉ አክለው ገልፀዋል::

ሌላኛው ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የታጋች ወንድም ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለፁት እህታቸው እስከ አሁን ድረስ ታግታ እንደምትገኝ ገልፀዋል::

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

“እህቴን ከትላንት ወዲያ ነው ለመጨረሻ ጌዜ ያወራሗት:: 700 ሺህ ብር ነው ለማስለቀቂያ እየተጠየቅን ያለነው:: ግን ምንም የምንከፍለው ገንዘብ የለንም:: ሁለት መንግሥት እያስተዳደረን እንዳለ ነው የሚሰማን::” ሲሉ ግራ በተጋባ ስሜት ገልፀዋል::

የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ቢሮ ሐምሌ 3 ቀን 2016 ዓ.ም በሰጠው መግለጫ “ጽንፈኛ እና አሸባሪ ሃይል” ብሎ በጠራቸው ሃይሎች ታግተው ከነበሩት 167 ተማሪዎች መካከል 160 ያህሉ በ”ከባድ ኦፕሬሽን” መለቀቃቸውን ማስታወቁን መዘገባችን ይታወሳል::

ይሁንና አዲስ ስታንዳርድ በወቅቱ ያነጋገራቸው የታጋቾች ቤተሰቦች በበኩላቸው የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ኮሚኒኬሽን የሰጠውን መግለጫ ሐሰት ነው ሲሉ አስተባብለው ነበር::

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አፈናውን የፈጸመው “ሸኔ” በማለት የጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት እንደፈፀመው የገለጸ ሲሆን ታጣቂ ቡድኑ የቀረበበትን ክስ አስተባብሎ “በተማሪዎቹ እገታ ላይ እጄ የለበትም” ሲል መግለጹ ይታወሳል::

ኢሰመጉ  በበኩሉ ሐምሌ 5 ቀን 2016 ዓ.ም በሰጠው መግለጫ የፌደራል እና የሚመለከታቸው የክልል መንግስታት የግዛት ወሰናቸው ባሉባቸው አካባቢዎች የሚፈጸሙ የእገታና አፍኖ የመሰወር ድርጊቶችን እንዲያስቆሙ፣ የእገታና አፍኖ የመሰወር ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎችን በሕግ ተጠያቂ እንዲያደርጉ እና ለዜጎች ተገቢውን ጥበቃ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል::

አዲስ ስታንዳርድ በዚህ ሳምንት ርዕሰ አንቀጹ ገንዘብ ለመቀበል ሲባል የሚፈጸም እገታ ዕየተለመደና እየተስፋፋ በመጠው እገታን ወንጀል ላይ መንግስት ጠንካራ እርመጃ መወሰድ እንዳለበት አስገንዝቧል።

ርዕሰ አንቀጹ የፀጥታ ተቋማት ለገንዘብ ሲባል የሚደረግን እገታ ማስቆም አለመቻላቸው ብሔራዊ ቀውስ መሆኑንና መንግስት የመላው የዜጎችን ደህንነትና መረጋጋት ለማስከበር የገባውን ቃል ለመጠበቅ መስራት እንዳለበትና እርምጃ የመውሰጃ ጊዜው አሁን መሆኑን አበክሮ አስከንዝቧል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button