ዜናህግ እና ፍትህ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ ለፓርላማ የቀረበው ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መገናኛዎችን መጥለፍ የሚፈቅድ ረቂቅ አዋጅ ተቃዋሚዎችን ማሳደጃ እንዳይሆን የምክር ቤቱ አባላት አሳሰቡ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6/2016 ዓ.ም፡- ለፓርላማ የቀረበው “በወንጀል የተገኘ ንብረትን ሕጋዊ ከማስመሰል ወይም ሽብርተኝነትን በገንዘብ ከመርዳት ወንጀል ጋር በተያያዘ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መገናኛዎችን እና ደብዳቤዎች ለመጥለፍ ለመርማሪዎች ፈቃድ የሚሰጥ ረቂቅ አዋጅ” ተቃዋሚዎችን ማሳደጃ እንዳይሆን የህ/ተ/ም አባላት አሳሰቡ።

ትላንት ለህዝብ ተወካዮች ም/ ቤት የቀረበው ረቂቅ አዋጅ መርማሪ አካል “አስቸኳይ ሁኔታ ካጋጠመው” የሚመለከተውን የዐቃቤ ሕግ ተቋም የበላይ ኃላፊ በማስፈቀድ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ የመገናኛ እና የደብዳቤ ልውውጦችን መጥለፍ ያሚያስች ነው።

በረቂቅ አዋጁ መሰረት  በዐቃቤ ሕግ ፍቃድ ያገኘ መርማሪ አካል ጠለፋውን ለማካሄድ የሚጠየቅ የመገናኛ የአገልግሎት አቅራቢ፤ “ጠለፋው በፍርድ ቤት ወይም በዐቃቤ ሕግ የበላይ ኃላፊ የተፈቀደ መሆኑን በማረጋገጥ” ትብብር የማድረግ ግዴታ ተጥሎበታል።

በወንጀል የተገኘ ንብረትን ሕጋዊ ከማስመሰል ተቀጽላ ወንጀሎች ጋር በተያያዘ ይጣል የነበረው ከ5 እስከ 10 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ ተሻሽሎ ከ100 እስከ 500 ሺህ ብር የሚያስቀጣ ሆኗል።

በረቂቅ አዋጁ ላይ ውይይት ያደረጉት የህ/ተ/ም አባላት አዋጆች ተቃዋሚዎችን ማሳደጃ እንዳይሆኑ ተገቢ ድነጋጌዎች እንዲካተቱባቸው ጠይቀዋል።

ከምክር ቤቱ አባላት ጥያቄዎች እና አስተያያቶች ካነሱት መካከል በቅርቡ ለእስር ተዳርገው የተፈቱት የፓርላማው አባል ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ይገኙበታል።

ዶ/ር ደሳለኝ ስጋት እና አስተያየት በሚል ባቀረቡት ሀሳብ ለምክር ቤቱ የሚቀርቡ ወንጀል እና ሽብር ነክ አዋጆች አስፈላጊነታቸው እንደተጠበቀ ሁኖ ተቃዋሚዎችን እና መንግስትን የሚተቹ ተቋማት የነዚህ አይነት ህጎች ሰለባ ሁነው ብዙ ጉዳት እንደደረሰባቸው በማውሳት ጥንቃቄ እንዲደረግባቸው አሳስበዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

አዋጆቹን ገዢው ፓርቲ ተቃዋሚዎችን ለማሳደድ እንዳያውለው ምን ዝግጅት ተደርጓል ሲሉ ማብራሪያ እንዲሰጥበት በመጠየቅ አዋጆቹ የወንጀል ፍሬ የሆኑትን ብቻ ለይቶ ለመከታተል እና ተቃዋሚዎችን ማሳደጃ እንዳይሆን ተገቢ ድንጋጌዎች እንዲካተቱባቸው ሲሉ አሳስበዋል።

በውይይቱ ላይ ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ረቂቅ አዋጅ ላይ ማብራሪያ ያቀረቡት ወ/ሮ መሰረት በወንጀል የተገኘ ንብረት ህጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀልን መከላከልና መቆጣጠር ትኩረት የሚያስፈልገው እና አለም አቀፍ ግዴታን ከመወጣት ጋር ተያይዞ መታየት የሚገባው ነው ብለዋል።

ነባሩ አዋጅ ግልጽነት የጎደለው እና በአተገባበር ሂደት እንደታየው ከሌሎች ህጎች ጋር የማይጣጣም እና ወቅታዊ ለሆኑ ችግሮች በቂ ምላሽ የማይሰጥ ሆኑ በመገኘቱ በአዲስ እና በተሟላ የህግ ማዕቀፍ መተካት ስላስፈለገ ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቷል ሲሉ ገልጸዋል።

ረቂቅ አዋጁ ካካተታቸው ነጥቦች መካከል የወንጀል ጥፋቶች እና ቅጣት፣ ወንጀሎችን ለመከላከልነእና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ድንጋጌዎች፣ ወንጀሎችን ለመለየት የሚያስችል ምርመራ፣ እንዲሁም አለም አቀፍ ትብብር የሚመለከቱ ድንጋጌዎች የሚሉት እንደሚገኙበት ጠቁመዋል።

ሌላ የምክር ቤቱ አባል በበኩላቸው በአካል በአዋጁ አንቀጽ “በቂ ቁጥጥር ከማያደርጉ የፋይናንስ ተቋማት ጋር የንግድ ግንኙነት ከመሰረተ ወይንም የነበረውን የንግድ ግንኙነት ካስቀጠለ” የሚለው ሃሳብ አሻሚ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሃሳቡ ውስብስብ ከመሆኑ ባለፈ ባንኮቹ ትክክለኛ ቁጥጥር ከሚደረግባቸው መሆናቸውንም ሆነ አለመሆናቸውን ማን ነው የሚያረጋግጠው ሲሉ ጠይቀዋል፤ ውጭ ሀገር ያለን ባንክ እንዴት ነው ማረጋገጥ የምንችለው፣ እነዴት በዝርዝር ማስቀመጥ ይችላል ብለዋል።

ሌላ የምክር ቤት አባል በበኩላቸው ሕጉ የሚመራለት ኮሚቴ የዓለም የገንዘብ ድርጅት ያወጣቸውን እና ሀገራት የግድ እንዲቀበሏቸው የተቀመጡ አስገዳጅ ድንጋጌዎችን ኢትዮጵያ ካወጣቻቸውና ተቀብላ ካጸደቀቻቸው ድንጋጌዎች ጋር በማዛመድ ለምክር ቤቱ የተደራጀ ሰነድ እንዲያቀርብም አሳስበዋል።

ረቂቅ አዋጁ ለዝርዝር እይታ ለህግ እና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሁለት ተቃውሞ ተመርቷል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button