ህግ እና ፍትህማህበራዊ ጉዳይዜናዜና ትንታኔ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና ትንታኔ፡ ሴቶችና ህፃናትን በተመለከተ በሥራ ላይ ያለው የወንጀለኛ መቅጫ ህግ መሻሻል አለበት_ የህግ ባለሙያዎች

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 14/ 2016 ዓ/ም፦ በአማራ ክልል ባሕር ዳር ከተማ ተደፍራ የተገደለችው የሰባት ዓመቷ ህፃን ሔቨን አወት አሰቃቂ የግድያ ወንጀልና የፍርድ ሂደቱ በርካቶችን እያቆጣ ይገኛል።

ድርጊቱ የተከሰተው ሐምሌ 25 ቀን 2015 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ ዳግማዊ ሚኒልክ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 14 ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ሲሆን አቶ ጌትነት ባይህ የተባለው የቤት አከራይ፤ የተከራይ ልጅ የሆነችውን የ7 ዓመቷን ህፃን ሔቨንን አሰቃቂ በሆነ መንገድ አስገድዶ ከደፈረት በኋላ አንቆ ህይወቷ እንዲያልፍ በማድረግ ወንጀል ተጥርጥሮ በቁጥጥር ስር በመዋል ክስ እንዲመሰረትበት ሆኗል። 

አቶ ጌትነት ባይህ ምርመራ ተደርጎበት በምርመራው እና ባሉት የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎች መነሻነት ፍትሕን ለማረጋገጥ በሚያስችል ሁኔታ የሀገሪቱ አግባብ የኾነውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ ተጠቅሶ ከፍተኛ ቅጣት በተደራራቢ ወንጀል ሁለት ክስ ማቅረብ ተችሏል ሲል የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። 

ክሶችም የግፍ ግድያ የወንጀል ሕጉ 539 እና በመድፈር መግደልን 620 (3) ያጣቀሰ ነበር ያለው ቢሮው ይህም የሞት ፍርድ ወይም የዕድሜ ልክ እስራት ድረስ የሚያስቀጣ ነው ሲል አክሏል፡፡

ነገር ግን ግራ ቀኝ ክርክሩን ሰምቶ የቀረበው ማስረጃ የግፍ ግድያን ሳይኾን (539) በመደፈር መሞቷን የሚያረጋግጥ መኾኑን በማረጋገጥ ተጠርጣሪው በ25 ዓመት ፅኑ እስራት ሊቀጣ ውሳኔ አርፎበታል ብሏል፡፡

ይህንን ተከትሎ ወንጀለኛው ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ በማቅርቡ የሄቨን ወላጅ እናት ባሳለፍነው ሳምንት ጉዳዩን ወደ ሚዲያ ይዘው በመምጣታቸው በህዝቡ ጉዳዩን እንዲሰማ አስችሏል።

ይህን ተከትሎ የተፈጸመው ወንጀል እና የተሰጠው ፍርድ ተመጣጣኝ አይደለም፣ የሞት ፍርድ ይገባዋል በሚል በርካቶች ቁጣቸውን በመግለጽ ላይ ይገኛሉ። ከዚህ በተጨማሪም “ፍትሕ ለህፃን ሔቨን” የሚል የማሕበራዊ ሚዲያ ዘመቻ የተከፈተ ሲሆን፤ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተሳተፉበት የፊርማ ማሰባሰብ እንቅስቃሴ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ባሕርዳር ከተማ ከፍተኛ ብጥብጥ እና ግጭት በመኖሩ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የነበረው የአሁኑ ፍርደኛ ወጥቶ ነበር የገለጸው የክልሉ ፍትህ ቢሮ ከተማው ተረጋግቶ በቁጥጥር እስኪውልም በነጻነት ይንቀሳቀስ ነበር ነበር ብሏል፡፡ 

በአሁኑ ወቅት ፍርደኛው የፍርደኛ ይግባኝ አቅርቦ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉዳዩን በመመርመር ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ ጉዳዩም ለውሳኔ ለሚቀጥለው ዓመት ተቀጥሮ ተሰጥቷል፡፡ ፍትሕ ቢሮው ጉዳዩን በአግባቡ እየተከታተለው በመግለጽ ምናልባት ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሚሰጠው ውሳኔ በአሉታዊ ቢኾን ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ በዐቃቢ ሕግ በኩል የሚቀርብ መሆኑን አሳውቋል። 

የአማራ ክልል ዳኞች ማሕበር በበኩሉ ባወጣው መግለጫ “ወንጀል እና ወንጀለኛ የሚዳኝበት ሕግና ስርዓት እያለ እና ጉዳዩም በዳኝነት አካሉ በይግባኝ እየታየ ባለበት ሁኔታ፤ ከዳኝነት ነጻነት እና ከሕግ የበላይነት መርህ ባፈነገጠ መልኩ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴሩን ጨምሮ በማህበራዊ ሚዲያው ቅጣት አንሷል፣ ተከሳሹ ይግባኝ ሊጠይቅበት አይገባም እና መሰል ነገሮችን በማናፈስ ዳኞች ህግና ማስረጃን ብቻ መሰረት አድርገዉ በነፃነት እንዳይሰሩ ያልተገባ ጫናን የሚፈጥር ተግባር እየተፈፀመ ይገኛል” ሲል ኮንኗል።

መግለጫው አክሎም “ማህበራዊ ሚዲያው ላይ ተከሳሹ ይግባኝ ማቅረብ የለበትም የሚለው ዘመቻ የአገሪቷን በሕግ የመዳኘት መብትን (Due process of law) አደጋ ላይ የሚጥል እና በይግባኝ የሚመለከተዉ ፍርድ ቤት ላይ ያልተገባ ጫና በማሳደር የዜጎችን ፍትህ የማግኘት መብት የሚጥስ ተግባር በመሆኑ የፍ/ቤቶችን የመወሰን ነጻነት በሚጋፋ መልኩ የሚደረገው የሚዲያ ዘመቻ እንዲቆም እናሳስባለን።” ሲል ገልጿል።

የሴቶች አና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር በበኩሉ በተፈፀመው ወንጀል ዙሪያ የተሰጠውን ውሳኔ አስመልክቶ ይግባኝ ለመጠየቅ የሚኬድበት አካሄድ አግባብ አለመኾኑንም ገልጿል።

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር በበኩሉ የተፈጸመውን ኢ-ሰብአዊ ድርጊት እንደሚያወግዝ ገልፆ፤ “ ከተፈፀመው ዘግናኝ ድርጊትና የማኅበረሰቡን ሞራልና ክብር ዝቅ ያደረገ ወንጀል በፈፀመው ወንጀለኛ ላይ የተሰጠው ፍርድ አስተማሪነት የሚያንሰው መሆኑን አሥተዳደሩ በፅኑ ያምናል” ሲል ገልጿል።

በፍርድ ሂደቱ ዙሪያ አስተያየታቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ የሰጡት ጠበቃ እና የህግ አማካሪው አቶ ወንድሙ ኢብሳ፤ በኢትዮጵያ በሴቶች እና ህፃናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በተመለከተ ከፍተኛ የህግ ክፍተት እንዳለ ገልጸዋል።

“ከተፈጥሮ ከሃገሪቱ ህግ እና ከሰብአዊነት ያፈነገጡ የወንጀል ድርጊቶች ሲፈጸሙ በመደበኛው ህግ ብቻ መዳኘት ለውጥ ሊያመጣ አልቻለም” ሲሉ ተናግረዋል። 

የህግ ባለሙያው አክለውም በሴቶች እና ህፃናት ላይ ለሚፈፀሙ አሰቃቂ የወንጀል ተግባራት ተመጣጣኝ የሆነ ፍርድ እንዲሰጥ የሚያስችል ህግ መውጣት እንዳለበት ገልጸዋል። ለዚህም ሴቶችና ህፃናትን በተመለከተ በሥራ ላይ ያለው የወንጀለኛ መቅጫ ህግ መሻሻል እንደሚገባው አጽንኦት ሰጥተዋል።

ይግባኝ መጠየቅን በተመለከተም “ይግባኝ መጠየቅ ህጉ ቢፈቅድም፤ ከሰብአዊነት ያፈነገጡ መሰል ድርጊቶች ሲገጥሙ የሚዳኙበት የህግ አሰራሮች መፈጠር ይኖርባቸዋል” ሲሉ ገልጸዋል።

ሌላኛው የህግ ባለሙያ ተጠምቀ ዮሐንስ፤ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል እየጨመረ በመሆኑ መንግሥት ህጉን በማሻሻል ከተቻለ ሌሎች ሃገራት ላይ ያለውን ልምድ በመተግበር ከፍተኛ የሆነ ቅጣት ማስቀመጥ አለበት ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።

ባለሙያው ወንጀሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ስለመጣ ህብረተሰቡን በማንቃት ብቻ የወንጀል ድርጊቱን መከላከል ባለመቻሉ የወንጀል ህጉን በማሻሻል ተመጣጣኝ የሆነ አስተማሪ ቅጣት መጀመር አለበት የሚል እምነት አለኝ ብለዋል።

አስገድዶ ለመድፈር ከትንሹ ጀምሮ አሁን እስከተወሰነው እስከ 25 ዓመት ድረስ በህጉ በተቀመጠው አግባብ እና የቅጣት አወሳሰን መመሪያ አለ ያሉት ባለሙያው ወንጀሉ ሴንሴቲቭ ከመሆኑ አንፃር እኛ ሃገር ለመሰል ወንጀሎች የተቀመጠው ቅጣት አግባብነትን በተመለከተ ህብረተሰቡ ከፈተኛ ቁጣ እያሰማ ይገኛል ብለዋል።

የሞት ቅጣት በወንጀል ህጋችን በግልጽ ተቀምጦ ይገኛል ያሉት ተጠምቀ ነገር ግን አፈፃፀምን በተመለከተ የህግ ክፍተት እንዳለ ጠቅሰዋል።   

“የሞት ቅጣትን በተመለከተ ሳዑዲ አረቢያ እና ቻይናን የመሳሰሉ ሃገራት ላይ ያለ የተፈጻሚነት ልምድ አለ።  በተጨማሪም ብልትን ማኮላሸት የመሰሉ ቅጣቶች አሉ  ልምዱን ጥቅም እና ጉዳቱን አመዛዝኖ ወደ እኛ አገር ማምጣት ያስፈልጋል ነው” በለዋል። 

የሞት ቅጣትን የምስራቅ ሃገራት እንጂ ምዕራባውያን የማይደግፉት በመሆኑ ተፈጻሚ ማድረግ ከእነርሱ ጋር ያለው ግንኙነት የሚሻክርበትና የሰብዓዊ ድጋፎች የማቋረጥ ሁኔታን የሚፈጥር በመሆኑ አብዘሃኛው ሃገራት ለዛ ነው ህጎቻቸው ላይ ቢኖርም ተፈፃሚ የማያደርጉት ብለዋል። 

“አባት ልጆቹን የሚደፍርበት ጉዳዮችን እየሰማን ነው ያነወን” ያሉት ተጠምቀ “እንደኔ ቢያንስ የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች ላይ የሞት ፍርድ የሚሰጥበት ሁኔታ ቢፈጠር የተሻለ ነው ብዬ አስባለሁ” ሲሉ ገልጸዋል። በተለይ አስከፊ የሆነውን የህፃናት እና ሴቶች ጥቃት ለመከላከል ማህበረሰቡና የሲቪል ተቋማት መንግሥት ላይ ጫና ማሳደር ይጠበቅባቸዋል በለዋል።አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button