ዜናፖለቲካ

ዜና፡ በህወሓት ውስጥ ካለው የስልጣን ሽኩቻ ህዝቡ ገለልተኛ ሆኖ እንዲቀጥል በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ሶስት ፓርቲዎች አሳሰቡ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25/ 2015 ዓ/ም፦ በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) አመራሮች መካከል እየተካሄደ ካለው የስልጣን ሽኩቻ ህዝቡ አንድነቱን እንዲጠብቅ እና ገለልተኛ ሆኖ እንዲቀጥል በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ ሶስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች በጋራ በሰጡት መግለጫ አሳሰቡ።

ብሔራዊ ባይቶ ዓባይ ትግራይ፣ ሣልሳይ ወያነ ትግራይ እና ውድብ ናፅነት ትግራይ ትላንት በጋራ ባወጡት መግለጫ እንዳስታወቁት ሁሉም የትግራይ ተወላጆች ከህወሀት የእርስ በርስ ሽኩቻ ገለልተኛ በመሆን እና አንድነትን በመጠበቅ ክልላዊ ጥቅምን እንዲያስቀድሙ ጥሪ አቅርበዋል::

ፓርቲዎቹ ይህን ያሉት በቅርቡ የትግራይ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በክልሉ ለተንሰራፋው ሙስና፣ የመልካም አስተዳደር ችግር እና የጸጥታ እጦት የህወሃትን የፖለቲካ አመራር ተጠያቂ ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው።

አቶ ጌታቸው፤ በጊዜያዊ አስተዳደሩ፣ በጸጥታ ሃይሎች እና በፍትህ አካላት መካከል ትብብር ባለመኖሩ በክልሉ አስተዳደር ችግር መፈጠሩን በግልፅ የተናገሩ ሲሆን አክለውም “በህወሓት አመራር ውስጥ የተፈጠረው የውስጥ መከፋፈል ቀውሱን የበለጠ አባብሶታል።” ሲሉገልጸዋል። 

ፓርቲዎቹ በጋራ መግለጫቸው፤ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን በቅርቡ ባደረጉት ንግግር ህወሃት በምርጫ ቦርድ ዳግም ካልተመዘገበ ዳግም ጦርነት የመቀስቀስ እድል እንዳለ መግለጻቸውን በመጥቀስ “የፌደራሉ መንግሥት የአንድን ፓርቲ ጉባኤ ጉዳይ፣ ከክልሉ ሕዝብ አጠቃላይ ደኅንነት ጋር ማያያዙ ተቀባይነት የለውም፤” ሲሉ ተቃውመዋል።

ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትግራይ ውስጥ የተፈጠረውን ችግር ከሚያባብሱ ንግግሮች እንዲታቀቡ ያሳሰቡ ሲሆን የፌደራል መንግስቱ እና ህወሓት ሰላማዊ ህዝብን ኢላማ ሳያደርጉ ጉዳዮቻቸውን እንዲፈቱ ጠይቀዋል።አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button