ቢዝነስዜናፖለቲካ

ዜና: በበርካታ የአማራ ክልል ከተሞች ከ11 ወራት በኋላ የኢንተርኔት አገልግሎት መጀመሩ ተገለጸ፣ ፍጥነቱ ዘገምተኛ ነው የሚል ቅሬታ ቀርቦበታል

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8/2016 ዓ.ም፡-በአማራ ክልል ለበርካታ ወራት ኢንተርኔት ተቋርጦባቸው የነበሩ ከተሞች አገልግሎት ማግኘት መጀመራቸው ተገለጸ። ከአስረ አንድ ወራት በኋላ በክልሉ በሚገኙ 19 የሚሆኑ ከተሞች ላይ የዳታ ኢንተርኔት አገልግሎት መጀመሩ ተጠቁሟል።

በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂ ሀይሎች እና በመንግስት የፀጥታ ሀይሎች መካከል ውጊያ መጀመሩን ተከትሎ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ማወጁን እና የኢንተርት አገልግሎት መቋረጡን ሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም መጨረሻ መዘገባችን ይታወሳል።

ከትላንት ሐምሌ 7 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በበርካታ የክልሉ ከተሞች የዳታ ኢንተርኔት አገልግሎት መጀመሩን ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ አስታውቀዋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የደሴ ከተማ ነዋሪ ለአዲስ ስታንዳርድ እንዳስታወቁት የዳታ ኢንተርኔት አገልግሎት መጀመሩን ገልፀው ፍጥነቱ ግን አነስተኛ መሆኑን ጠቁመዋል። “ሁሉም እየተጠቀመው ስለሆነ መጨናነቅ አለ: መጣ ሄደት ይላል” ያሉት የአከባቢው ነዋሪ አክለውም በአገልግሎቱ መመለስ የተሰማቸውን ደስታ ተናግረዋል።

ሌላኛው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የባህርዳር ነዋሪም የኢንተርኔት አገልግሎት መመለሱን ገልፀው ፍጥነቱ ግን አነስተኛ መሆኑን ለአዲስ ስታንዳርድ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሞ በ2023 ብቻ ኢንተርኔት በመዝጋቱ አንድ ነጥብ ስድስት ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ገደማ ማጣቱን የመብት እና ዲሞክራሲ ማዕከል (Center for Rights and Democracy (#CARD)) ማስታወቁን መዘገባችን ይታወሳል።

ተቋሙ ያካሄደው ጥናት እንደሚያሳየው ከሰሀራ በታች ካሉ ሀገራት ኢንተርኔት በመዘጋቱ ሳቢያ በቀዳሚነት በርካታ ገቢ ያጣው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ነው።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በ2023 ብቻ በኢትዮጵያ ለ14ሺ 910 ሰአታት የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጧል፤ ከ29 ሚሊየን በላይ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ተጎጂ ሁነዋል ብሏል።

ኢንተርኔት እንዲቋረጥ የተደረገው በግጭቶች እና አለመረጋጋት ምክንያት መሆኑንም ጥናቱ አመላክቷል።

የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (CARD) ዋና ዳይሬክተር አቶ በፍቃዱ ሃይሉ በአማራ ክልል የኢንተርኔት አገልግሎት መመለሱን ለአዲስ ስታንዳርድ አረጋግጠዋል::

የብሮድባንድ ኢንተርኔት ቀድሞም ይሰራ እንደነበር የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ አሁን የተመለሰው የዳታ አገልግሎት መሆኑን ጠቁመዋል። አክለውም የአገልግሎቱ ፍጥነት መቀነሱን በተመለከተ ትክክለኛው መንሰኤ ገና ምርመራ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል::

“የተለያዩ ምክንያቶች የኢንተርኔት ፍጥነቱን ሊገድቡት ይችላሉ፣ ምሣሌ አንዳንድ ማህበራዊ ድረገፆች ላይ ዕቀባዎች ተደርገው ከሆነ ወይም የበይነ መረቡ አቅራቢ ፍጥነቱን ገድቦት ከሆነ ግንኙነቱን አሰልቺ ሊያደርገው ይችላል:” ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም የአገልግሎት ፍጥነት አለመኖሩን በተመለከተ ምርመራ ስለሚያስፈልገው በትክክል በዚህ ምክንያት ነው ለማለት እንደሚያስቸግር ለአዲስ ስታንዳርድ አብራርተዋል።

ከባለፈው አመት ሐምሌ ወር ጀምሮ በበርካታ የአማራ ክልል ከተሞች የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡን መዘገባችን ይታወሳል።

በያዝነው አመት መጀመሪ ከ300 በላይ የሰብዓዊ መብት ተማጋች ድርጅቶች የኢትዮጵያ መንግስት በአማራ ክልል ላይ የጣለውን የኢንተርኔት ( በይነ-መረብ) እገዳ እንዲያነሳ መጠየቃቸውን የተመለከተ ዘገባ ማስነበባችን ይታወሳል።

ከ105 ሀገራት የተወጣጡት  ኪፕኢትኦን  ጥምረት ድርጅቶቹ በግጭት ወቅት ኢንተርኔት መዝጋት የዜጎችን ህይወት አደጋ ላይ የሚጥል እና አስፈላጊ መረጃን እንዳያገኙ ያደርጋል ብለዋል፡፡ በክልሉ ከነሃሴ ውር ጀምሮ የተወሰደው ኢንተርኔት መዝጋት ተግባር የአለም አቀፍ ህግን የጣሰ ድርጊት ነው ሲሉ ባወጡት የጋራ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡ አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button