ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: በባህርዳር ከተማ ከምሽቱ 3 ሰዓት በኋላ የሰውም ሆነ የመኪና እንቅስቃሴ ተከለከለ፤ ባጃጅ ከምሽቱ 12 በኋላ ማንቀሳቀስ እንደማይቻል ተገልጿል

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22/2016 ዓ.ም፡-የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ጸጥታ ምክር ቤት የተለያዩ የክልከላ ውሳኔዎችን ማሳለፋን አስታወቀ። የአስተዳደሩ ጸጥታ ምክር ቤት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ባወጣው መግለጫ አሁንም በከተማዋ አንዳንድ የጸጥታ ስጋቶች መኖራቸውን ጠቁሞ እነዚህን ስጋቶች ለማስወገድ የክልከላ ውሳኔዎችን ማሳለፉን አስታውቋል፤ አብዛኞቹ ችግሮች የሚፈጸሙት በባጃጅ ተሽከርካሪዎች በመታገዝ መኾኑን አመላክቷል።

የሰው እንቅስቃሴም እስከ ምሽቱ 3 ሰዓት የተፈቀደ ሲኾን ከተፈቀደው ሰዓት በኋላ መንቀሣቀሥ ግን የተከለከለ ነው ብሏል።

ለኅብረተሰቡ ቀጥተኛ አገልግሎት የሚሰጡ የቤት መኪና፣ ታክሲ፣ የመንግሥት መኪና፣ ማንኛውም የጭነት መኪና ተሽከርካሪ እስከ ምሽቱ 3 ሰዓት ድረስ ብቻ ማሽከርከር የተፈቀደ ሲኾን ከተፈቀደው ሰዓት እላፊ ሲያሽከረክሩ መገኘት ግን በሕግ ያስቀጣል ብሏል።

ለባጃጅ ተሸከርካሪዎች ከምሽቱ 12 ሰዓት በኋላ እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ማሽከርከር የተከለከለ መሆኑን አስታውቋል። የባጃጅ ባለ ንብረቶች ለቀን ገቢ ወይም ለተለያዩ የጊዜ ገደብ ለሚያከራዮቸው ግለሰቦች የውል ስምምነት በመያዝ ለፓሊስ እና ትራንስፖርት ጽሕፈት ቤት ማሳወቅ እንዳለባቸው አሳስቧል።

ባለ 2 እግር ሞተር ተሽከርካሪ በከተማው ላልተወሰነ ጊዜ ማሽከርከር የተከለከለ ነው ሲል አስጠንቅቋል።

ይህ ክልከላ የማይመለከታቸው ተሽከርካሪዎች በጸጥታ ሥምሪት ላይ የሚገኙ፣ አንቡላሶች፣ የእሳት አደጋ መኪናዎች ናቸው። ነገር ግን በማንኛውም ሰዓት በአንቡላንስም ኾነ በሌሎች ተሽከርካሪዎች ላይ ፍተሻ ይደረጋል።

ከጸጥታ መዋቅሩ አባላት እና ለጸጥታ ሥራ ተሰማርተው የመንቀሣቀሻ ፈቃድ ከተሰጣቸው ሰዎች ውጭ የጦር መሣሪያ ይዞ መንቀሣቀሥ የተከለከለ መሆኑን ያስታወቀው አስተዳደሩ ማንኛውም የጸጥታ አባል ከስምሪት ውጭ በሚኾንበት ጊዜ ሲቪል ለብሶ የጦር መሣሪያ ይዞ መንቀሣቀሥ ክልክል ነው ብሏል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ክልከላውን ጥሶ የጦር መሣሪያ ይዞ የሚገኝ የጦር መሣሪያውን እንደሚነጠቅ ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button