ማህበራዊ ጉዳይዜና
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ በባሕር ዳር ከተማ በተፈጠረ ከፍተኛ የጸጥታ ስጋት ምክንያት እንቅስቃሴዎች መቆማቸው ተነገረ

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 10/ 2016 ዓ/ም፦ በአማራ ክልል መዲና ባሕር ዳር ዛሬ ከሰዓት በኋላ በተጠራ የስራ ማቆም አድማ ጥሪ በተፈጠረ የጸጥታ ስጋት እንቅስቃሴዎች መቋረጣቸውን ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጹ።

ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ነዋሪ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለጹት፤ ዛሬ ከሰዓት በኋላ “ውጊያ” ሊከፈት ይችላል በሚል ስጋት የንግድ ማዕከላት ሱቆቻቸውን በጊዜ መዝጋታቸውን ገልጸዋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ሌላኛዋ የባሕርዳር ነዋሪ በበኩላቸው ሰሞኑን በከተማዋ ተከታታይ የቦንብ ፍንዳታዎች መፈጸማቸውን አስረድተዋል። አክለውም በቀበሌ 4፣ በቀበሌ 14 እንዲሁም አባይ ማዶን ጨምሮ በከተማዋ ልዩ ልዩ ስፍራዎች የቦንብ ጥቃቶች መፈጸማቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ በሰጡት ቃል አረጋግጠዋል።

የአማራ ክልል ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ በበኩሉ በወቅታዊ የፀጥታ ጉዳይ ለብዙኅን መገናኛ ተቋማት መግለጫ ሰጥቷል።

“ሰሞኑን በክልላችን አንዳንድ አካባቢዎች እየተካሄደ ያለው የአመፅ ጥሪ እና የጦርነት ነጋሪት ጉሰማ በእጅጉ የሚያሳዝን ነው።” ያለው መግለጫው አክሎም መንግሥት እና ሕዝብ ክልሉ ያጋጠመውን የሰላም እጦት እና ግጭት በሰላም እና በድርድር ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ባሉበት ሁኔታ እራሱን የ”ጎጃም ፋኖ” በሚል የሚጠራው ታጣቂ ቡድን ያስተላለፈውን የአድማ ጥሪ ተከትሎ በክልሉ ትራንስፖርትን ጨምሮ የሥራ እንቅስቃሴ መቆሙ በእጅጉ እንዳሳዘነው ገልጿል።

“ሕዝቡ ሽብር ለመፍጠር የሚጥረውን ሃይል ከመንግሥት መዋቅር ጋራ በመቀናጀት መመከት ሲገባው በተቃራኒው ለጥፋት ሃይሉ ተንበርካኪ በመሆን የተፈጸመው ድርጊት ያሳዝናል።” ያለው መግለጫው፤ በባሕር ዳር ከተማ ከሰሞኑን ተከታታይ ፍንዳታዎች መከሰታቸውን ገልጿል።

ከዚህ ድርጊት ጋር በተያያዘም “ገንዘብ ተከፍሏቸው ፈንጅ የሚያፈነዱ ሁለት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን” የፀጥታ ቢሮው መግለጫ ያመለክታል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አሥተባባሪ እና የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው በበኩላቸው በወቅታዊ የፀጥታ ጉዳይ ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፤ “የፀጥታ መዋቅሩ በአስተማማኝ ቁመና ላይ ስለሚገኝ ባሕር ዳር ላይ የሚፈጠር ነገር አይኖርም” ሲሉ ተናግረዋል።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባስተላለፈው መልዕክት፤ በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ “የተፈጠረ የጸጥታ ችግር አለመኖሩን” አስታውቋል። በተጨማሪም ህዝቡ “የጸጥታ ሃይሉ ቁመና በአስተማማኝ ሁኔታ ላይ ስለሚገኝ” የቀደመውን ሰላማዊ እንቅስቃሴ እና መስተጋብር እንዲቀጥል አሳስቧል።

በአማራ ክልል ከአመት በፊት በመንግሥት ሃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የጀመረው ውጊያ ተባብሶ ቀጥሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ( ዶ/ር) በቅርቡ ተግባራዊ በሆነው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ላይ ባደረጉት ማብራሪያ ከተወሰኑ የፋኖ ታጣቂዎች ጋር የሰላም ንግግር መጀመሩን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ በአማራ ክልል በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ አንድ ዓመት የሆነውን ግጭት በንግግር ለማስቆም በሚል ዓላማ የተቋቋመው የሰላም ካውንስል “ውጤት ማምጣት አልቻልኩም” ሲል ማስታወቁን መዘገባችን ይታወሳል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button