ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: ከአላማጣ ወደ መቀለ የሚወስደው መንገድ የመዘጋት እና የተሽከርካሪዎች እንቀስቃሴ መስተጓጎል ክስተት መፈጠሩን ነዋሪዎችና የአካባቢው አስተዳደር ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12/2016 ዓ.ም፡- አዲስ አበባን ከትግራይ የሚያገናኘው ዋናው መንገድ በራያ አላማጣ ከተማ ባላፉት ሶስት ቀናት በሰዓታት ልዪነት የመዘጋትና የመከፈት እንዲሁም የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ መስተጓጎል መፈጠሩን ነዋሪዎችና የደቡብ ትግራይ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጹ።

አዲስ ስታንዳርድ ያነጋገራቸው የአላማጣ ከተማ እና ጥሙጋ አከባቢ ነዋሪዎች፤ ካሳለፍነው ሳምንት መገባደጃ ጀምሮ ወጣቶች ዋናውን መንገድ  ዲንጋይ በመደርደር ለመዝጋት ሙከራ ሲያደርጉ እንደነበር ጠቁመው በአከባቢው የሰፈረው የፌደራል ፖሊስ እና የመከላከያ ሀይል እያስከፈቱት መኪኖች እንዲጓጓዙ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውቀዋል።

ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የቆቦ ከተማ ነዋሪ ለአዲስ ስታንዳርድ እንዳስታወቁት፤ ሰኔ 9 ቀን 2016 ዓ.ም ወደ መቀሌ እቃ ጭነው ሲጓዙ የነበሩ በርካታ መኪኖች መንገድ ተዘግቶባቸው ወደ ቆቦ ከተማ ሲመለሱ ማየታቸውን ገልጸዋል። ትላንት ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም ጠዋት ላይ ከአርባ ምንጭ ሙዝ ጭኖ የመጣ መኪና ሙዙ እንዳይበላሽ በአፋር ጭፍራ በኩል ሲንቀሳቀስ ማየታቸውን ጠቁመዋል።

ከአማራ ክልል ወልድያ እና ቆቦ ከተሞች ተነስተው ወደ አላማጣ ተሳፋሪ የሚያመላልሱ ሚኒባሶች ሰኔ 9 እና 10 ቀን 2016 ዓ.ም እስከ አላማጣ መግቢያ ድረስ ጭነው ይሄዱ እንደነበር አስታውሰው ነገር ግን ወደ አላማጣ ከተማ እንዳይገቡ ይደረጉ እንደነበር አስታውቀዋል። መግቢያው ላይ ተሳፋሪዎቹን በማውረድ ይመለሱ ነበር ብለዋል።

መንገዱ ትላንት ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም ከዘጠኝ ሰአት አከባቢ ጀምሮ ክፍት መሆኑን ነዋሪው አክለው አረጋግጠዋል።

የደቡብ ትግራይ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብቱ ኪሮስ ከአዲስ ስታንዳርድ በሁኔታው ዙሪያ ተጠይቀው በሰጡት ማብራሪያ በአላማጣ ከተማ መግቢያ ላይ ባለፉት ሶስት ቀናት መንገድ “የመዝጋት ሙከራ” መደረጉን ተናገረዋል። ነገር ግን መንገዱ “ሙሉ በሙሉ እንደተዘጋ ተደርጎ የሚቀርቡ መረጃዎች ስህተት ናቸው” ሲሉ ገልጸዋል።

አስተዳዳሪው “የፕሪቶርያው ስምምነት መፈጸምን የማይፈልጉ ተስፋፊ ሀይሎች” ሲሉ የጠሯቸው አካላት፤ የከተማዋን አንዳንድ ወጣቶችን በማደራጀት እና በገንዘብ በመደለል ሁከት ለመፍጠር ጥረት እያደረጉ ነው ሲሉ ከሰዋል።  አስተዳዳሪው የከሰሷቸው አካላት፤ “በትግራይ ጦርነት ወቅት የትግራይን ግዛት በመቆጣጠር አስተዳደር መስርተው የነበሩ ናቸው” ብለዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የመከላከያ ሰራዊት እና ፌደራል ፖሊስ በወጣቶቹ የተዘጉ መንገዶችን ሲያስከፍቱ እንደነበር ጠቁመው ነገር ግን አንዳንድ “የስነምግባር ጉድለት ያለባቸው የፌደራል ፖሊስ አባላት ተግባሩን ከሚፈጽሙ ወጣቶች ጋር ትብብር እንደሚያደርጉ መረጃው አለን” ሲሉ ገልጸዋል።

የፌደራል ፖሊስ በአከባቢው የነበሩ አብዛኞቹን አባላት በማንሳት በሌሎች አባላቱ መተካቱን አመላክተዋል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በአዲስ አበባ ከፌደራል መንግስቱ ጋር በነበረው ውይይት የነበረው አስተዳደር “እንዲፈርስ ከስምምነት ላይ ተደርሷል” ያሉት ሀብቱ ኪሮስ፤ የቀደመው አስተዳደር አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ ፈርሷል ሲሉ ገልጸዋል።

“የቀደመው አስተዳደር በመፍረሱ ተደናግጠው ነዋሪዎች አከባቢውን ጥለው ወጥተዋል” ያሉት አስተዳዳሪው “ወጥተው የነበሩ የአላማጣም ይሁን የኮረም ነዋሪዎች በቀናት ውስጥ ተመልሰዋል” ሲሉ ገልጸዋል።

በሰኔ ወር መጀመሪያ ቀናት የአላማጣ ከተማ ነዋሪዎች የመብራት ኃይል ሰራተኛ “በህወሃት ታጣቂዎች” ተገድሏል መባሉን ተከትሎ ባደረጉት ሰልፍ የአንድ ሰው ህይወት ማለፉን መዘገባችን ይታወሳል።

ሰልፉ በተካሄደበት ቀን አንድ ሰው ላይ ጉዳት ሲደርስ በቀጣዩ ቀን ሁለት ተጨማሪ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል። ክስተቱን ተከትሎም በከተማዋ ውጥረት ነግሷል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button