ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: በአማራ ክልል በሱዳናውያን መጠለያ አቅራቢያ በተደረገ ውጊያ ዘጠኝ የፌደራል ፖሊስ አባላት ተገድለዋል፣ ስደተኞች ተጎድተዋል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11/2016 ዓ.ም፡- በአማራ ክልል በሱዳናውያን መጠለያ ካምፕ አቅራቢያ በመንግስት የፀጥታ ሀይሎች እና በታጣቂዎች መካከል በተደረገ ውጊያ የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች መገደላቸው፣ ስደተኞች መጎዳታቸው ተገለጸ።

በአብዛኛው ሱዳናዊ ስደተኞችን ባስጠለለው በኩመር የመጠለያ ጣቢያ አቅራቢያ በሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ላይ በተፈጸመው ጥቃት ቢያንስ ዘጠኝ ፖሊሶች መገደላቸውን እንዲሁም በርካቶች መቁሰላቸውን ሁለት ስደተኞችን እንደነገሩት ቢቢሲ በዘገባው አስታውቋል።

ሱዳን ትሪቢዩን ድረገጽ በበኩሉ በጸጥታ ሀይሎች እና በአከባቢው በሚንቀሳቀሱ ማንነታቸው ያልታወቀ ሲል የገለጻቸው ታጣቂዎች መካከል በተካሄደው ውጊያ በተኩስ ልውውጥ አንድ ህጻን ሱዳናዊን ጨምሮ በርካቶች ቆስለዋል ብሏል።

በአከባቢው በሚገኘው ኩምሩክ መጠለያ ካምፕ ላይ ተጠልለው የሚገኙ ሱዳናውያን ነገሩኝ ብሎ ድረገጹ እንዳስነበበው ከሆን በተካሄደው ውጊያ ዘጠኝ የፌደራል ፖሊስ አባላት መገደላቸውን አስታውቋል። ታጣቂዎቹ የፌደራል ፖሊስ አባላት ላይ ጥቃቱን የፈጸሙት ትላንት ሐምሌ 10 ቀን ንጋት ላይ መሆኑን ጠቁሟል።

በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና ጥቃቱን በከፈቱት ታጣቂዎች መካከል ሲደረግ በነበረው የተኩስ ልውውጥ አንድ የሶስት አመት ሱዳናዊ ህጻንን ጨምሮ በርካታ ስደተኞች ተጎድተዋል ብሏል።

ጥቃቱን ተከትሎ ከአውላላ መጠለያ ካምፕ ወጥተው በጫካ ውስጥ የተጠለሉ ሱዳናውያን ስደተኞችን ሲጠብቁ የነበሩ የፌደራል ፖሊስ አባላት በአከባቢው ባለስልጣናት ትዕዛዝ ጥለዋቸው መሄዳቸውን የሱዳን ስደተኞች አስተባባሪ ኮሜቴ መግለጹን ድረገጹ በዘገባው አስነብቧል።

ኮሚቴው ስደተኞቹ የሚገኙበት አሁናዊ ሁኔታ እጅግ አስቸጋሪ ነው ሲል ማሳሰቡን አስታውቋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ስደተኞቹ በታጣቂዎች ጥቃቶች እንደተፈጸሙባቸው እና በትጥቅ የታገዙ ዘረፋዎች እንዲሁም ለገንዘብ የሚደረጉ እገታዎች ተደጋጋሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ተከትሎ መጠለያ ካምፖቹን ጥለው በአቅራቢያቸው በሚገኘው ጫካ መኖር መጀመራቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

የሐምሌ 10 ቀን 2016 ዓ.ም ጥቃትን ተከትሎ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ወደ አካባቢው መሰማራታቸውን ስደተኞቹ እንደነገሩት ቢቢሲ በዘገባው አስታውቋል።

በአማራ ክልል በምዕራብ ጎንደር ዞን የሚገኙት አውላላ እና ኩመር የተሰኙት የተመድ መጠለያ ጣቢያዎች ከሱዳን፣ ከኤርትራ እና ከደቡብ ሱዳን የሚመጡ ስደተኞችን ይቀበላሉ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ድርጅት በአማራ ክልል የስደተኞች ካምፕ ላይ ተጠልለው የሚገኙ ሱዳናውያንን ስደተኞችን ወደ ሌላ አዲስ ቦታ (የተሻለ የክልሉ አከባቢ) ለማዛወር መወሰኑን መዘገባችን ይታወሳል።

ድርጅቱ ከአጋር ድርጅቶች እና ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመተባበር በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል የሚኖሩ ሱዳናውያን ስደተኞችን ወደ ሌላ ቦታ የሚያዘዋውሩበትን ቦታ መለየቱን በዘገባው ተካቷል።

በወራት ውስጭ እነዚህ ስደተኞች በክልሉ ወደ ተለዩት አዲስ ቦታዎች እንደሚዛወሩ ተጠቁሟል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button