ህግ እና ፍትህዜና
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ በአርሲ ዞን በተፈጸመ ጥቃት አንድ ካህንን ጨምሮ ስድስት ሰዎች መገደላቸው ተነገረ

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 11/ 2016 ዓ/ም፦ በኦሮሚያ ክልል በአርሲ ዞን አሰኮ ወረዳ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ በተፈጸመ አሰቃቂ ጥቃት የአካባቢውን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ ካህን ጨምሮ 6 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው ተነግሯል።

ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአሰኮ ወረዳ ነዋሪ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደተናገሩት፤ ጥቃቱ ነሐሴ 7 ቀን 2016 ዓ.ም.  በወረዳው ጢጆ ቀበሌ ውስጥ የተፈጸመ ሲሆን በጥቃቱ ከተገደሉት በተጨማሪ ሌሎች 3 ሰዎች መቁሰላቸውን ገልጸዋል።

በአካባቢው የቤተክርስቲያን አገልጋይ አባል የሆኑት ነዋሪ አክለውም የጥቃቱ ፈጻሚ “ሸኔ” ተብሎ የሚጠራው የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት መሆኑን ገልጸዋል።

ከሟቾቹ መካከልም በጠለልቱ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የነበሩት ቄስ በላይነህ ማሞን ጨምሮ ገዛኸኝ መንግስቱ፣ ገበየሁ ፀጋዬ፣ መብራቱ ፍቅሬ፣ አበበ ፍቅሬ እና አድማሱ ታደሰ የተባሉ ግለሰቦች እንደሚገኙበት ምንጩ ለአዲስ ስታንዳርድ አክለዋል።

በጥቃቱ አቶ በላይነህ ዘርጋው፣ ደምሶ አበራ እና መብራቱ ልክየለው የተባሉ ሌሎች ግለሰቦች  መቁሰላቸውም ተጠቁሟል።

ጥቃቱን ተከትሎ የመኖሪያ ቤቶች መውደማቸውንና ከብቶች እና በጎችን ጨምሮ ከፍተኛ የንብረት ዘረፋ መፈጸሙንም የአካባቢው የሃይማኖት አባቶች ገልፀዋል።

ለደህንነት ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ሌላዋ የጢጆ ነዋሪ በበኩላቸው፣ በአካባቢው እየተከሰቱ በሚገኙ የጸጥታ ችግሮች የተነሳ ከፍተኛ ስጋት መፈጠሩን ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ነዋሪው አክለውም ግማሹ ቀበሌ በ”ሸኔ” ቁጥጥር ስር ሲገኝ ሌላኛው ግማሽ ቀበሌ ደግሞ በመንግስት ኃይሎች ቁጥጥር ስር እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ጥቃቱን ተከትሎ በርካታ ተፈናቃዮች በቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ተጠልለው የሚገኙ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ሁኔታው ​​​​አስቸጋሪ እንደሆነም ገልጸዋል። በተጨማሪም “ህፃናት እና አረጋውያን በምግብ እና በመድሃኒት እጦት እየተሰቃዩ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

በአከባቢው የክልሉ ፖሊስ ሃይል ቢገኝም፤ ያለው የጸጥታ ችግር አሁንም አሳሳቢ መሆኑን ገልጸዋል።

ነዋሪው አክለውም የአካባቢው ነዋሪዎች ምንም አይነት የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳትፎ የሌላቸው አርሶ አደሮች መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዞኑ የተፈጸመው ይህ ጥቃት የመጀመሪያ አይደለም። ከቅርብ አመታት ወዲህ በአከባቢው የሚፈፀሙ ጥቃቶች ተባብሰው ቀጥለዋል።

በህዳር ወር በአርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ 36 ሰዎች ባልታወቁ ታጣቂዎች መገደላቸውን አዲስ ስታንዳርድ መዘገቡ ይታወሳል

ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ነዋሪ በበኩላቸው፤  በአከባቢው በሚፈጸሙ ጥቃቶች ዋነኛ ሰለባዎቹ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች መሆናቸውን ገልጸው፤ ጥቃቱ በማንነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን አስረድተዋል። ከሟቾቹ መካከልም ህጻናትና አረጋውያን ሴቶች እንደሚገኙበት ነዋሪው ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ በበኩሉ ወንጀሉን የፈፀመው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ነው ሲል ከሷል።

ይሁን እንጂ የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ቃል አቀባይ ክሱን አጥብቆ ያስተባበለ ሲሆን፣ በሺርካ ወረዳ በተፈፀመው ጥቃት የመንግሥት ሃይሎች ሰላማዊ ሰዎችን መግደል እና ቤቶችን ማቃጠልን ጨምሮ ሰፊ አሰቃቂ ድርጊቶች ላይ ከተሳተፉ በኋላ፤ “የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ነው የፈጸመው ይላሉ።” ሲል አበክሯል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button