ዜና
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን፣ ፍትሕና ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ 10 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሰላም ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 2/ 2016 ዓ/ም፦ በአዲሱ 2017 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን፣ ፍትሕና ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ፤ የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከልን ጨምሮ 10 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፤ የሰላም ጥሪ አቀረቡ።

ድርጅቶቹ ትናንት ጳጉሜ 1 ቀን በጋራ ባወጡት የሰላም ጥሪ  መግለጫ በ2016 ብቻ በመላው ኢትዮጵያ ከ1,792 በላይ የግጭት ኩነቶች የተመዘገቡ መሆኑን ገልጸው በነዚህ ግጭቶችም በጥቅሉ ከ6,164 በላይ ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል  ብለዋል።  ይህም ማለት በግጭቶች ሳቢያ ብቻ በየወሩ በአማካይ 560 ሰዎች የተገደሉበት ዓመት እንደነበር አመላክተዋል።

ድርጅቶቹ በመግለቻቸው፤ የነዚህ ግጭቶች ጦስም ከዘፈቀደ ግድያዎች ባሻገር፣ ለሰላማዊ ሰዎች አካል መጉደል፣ በሕፃናትና በሴቶች ላይ ፆታዊ ጥቃትን እንደበቀል እና ጥቃት መሣሪያ መጠቀም፣  ለዜጎች ከቀያቸው መፈናቀል፣ የሕክምናና የትምህርት ተቋማት መውደምና የሕፃናትና ታዳጊዎች ከትምህርት ገበታ መቅረት፣ የመንቀሳቀስ ነፃነታቸውን ማጣት፣ አፈናና የአስገድዶ መሰወር መንሰራፋት  አሳሳቢ ሁነቶች ነበሩ ብለዋል። 

በተለይም በአማራ ክልል እንዲሁም በኦሮሚያ እና ሌሎች ክልሎችም የዘፈቀደ እስሮች፣ በከተማዎች ውስጥ እና አቅራቢያ በሚደረጉ የተኩስ ልውውጦች ሳቢያ የሚፈጠር አለመረጋጋትና መሸበር፣ እንዲሁም እነዚህን ቀውሶች ያስከተሉት የኑሮ ውድነት እና ጫና ተባብሰው ተስተውለዋል ተብሏል።

ግጭቶች በተከሰቱባቸው የአማራ ክልልና በሌሎቹም የኢትዮጵያ ክፍሎች ለ10 ወራት ተፈፃሚ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ተከትሎ፣ የሲቪክ ምኅዳሩ በእጅጉ ሲጠብ፣ ጋዜጠኞችና የመብቶች ተሟጋቾች እንዲሁም የፖለቲካ አመራሮችና የምክር ቤት አባላት ጭምር ለእስር ተዳርገው በኢሰብዓዊ አያያዝ እንዲቆዩ መደረጋቸው ለዴሞከራሲ መጎልበትና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር አሉታዊ እንድምታ አድርሷል ብለዋል። 

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በመግለጫቸው፤  “መጪውን አዲስ ዓመት 2017ን ስንቀበል፣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት፣ ነውጥ አዘል ግጭቶችን በሙሉ በማስቆም፣ እየከፋ የመጣውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች፣ እንዱሁም እየተንሰራፋ የመጣው ስርዓተ አልበኝነት ተከትለውን ወደ ቀጣዩ ዓመት እንዳይሸጋገሩ ፍትሕ እና ተጠያቂነትን በማስፈን እንዲሆን” ሲሉ አሳስበዋል።

ድርጅቶቹ ዘላቂ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ ተብሎ ተስፋ የተሰነቀባቸው ሀገራዊ ምክክሩም ይሁን የሽግግር ፍትሕ ሒደቱ ያለ ዘላቂ ሰላም “እውን እንደማይሆኑ” በመረዳት፤  መንግሥት እና ሁሉም ባለድርሻ አካላት ከዓመታዊ አጀንዳዎቻቸው ሁሉ ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት እንዲሰሩ አበክረው ጠይቀዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ፆታዊ ጥቃቶች  ትኩረት እንዲሰጣቸውን እንዲሁም የሲቪክ ምኅዳሩ እንዲጠበቅ የጠየቁት ድርጅቶቹ፤ በአገሪቱ ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች ጋር የተጀመሩ ንግግሮች እንዲቀጥሉ፣ ግጭቶችን የሚቀሰቅሱ አግላይ አሠራሮች እና ድንገተኛ ውሳኔዎች በአካታችነት፣ ግልጽነት፣ እና ምክክር እንዲተኩ ጥሪ አቅርበዋል።

የትጥቅ ትግል ስልትን የመረጡ ወገኖችም ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ሰላም እና እፎይታ ሲባል ነውጥ ተኮር ከሆኑ ግጭቶች ታቅበው፣ በፍፁም ቅን ልቦና፣ ትዕግስት እና ቁርጠኝነት ለሰላም ውይይቶች እና ድርድሮች በራቸውን እንዲከፍቱ ጠይቀዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button