ዜናፖለቲካ

ዜና: በኢትዮጵያ የአሜሪካን አምባሳደር ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እና ከህወሓት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በተናጠል መወያየታቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 23/2016 ዓ.ም፡- በኢትዮጵያ የአሜሪካን አምባሳደር የሆኑት ኤርቪን ማሲንጋ ትላንት ነሃሴ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሃላፊዎች እና ከህወሓት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በተናጠል መወያየታቸው ተገለጸ።

አምባሳደሩ በትግራይ ያካሄዱትን የሶስት ቀናት ጉብኝት አስመልክቶ ኤምባሲው በጋራው መረጃ አምባሳደሩ በመቀለ ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እና ከህወሓት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ውጤታማ ውይይት አካሂደዋል ብሏል።

አምባሳደሩ ከከፍተኛ ባለስልጣናቱ ጋር በነበራቸው ውይይት “በፕሪቶርያ የተደረሰው የሰላም ስምምነት ለትግራይ እና ለአካባቢው ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት መሰረት መሆኑን” አጽንኦት ሰጥተው መወያየታቸውን ኤምባሴው አመላክቷል።

የአምባሳደሩን ጉብኝት መገባደድ አስመልክቶ ኤምባሲው በማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገጾቹ ባጋራው መረጃ ውጤታማ ውይይት አካሂደዋል ከማለት ባለፈ በፓርቲው አመራሮች ክፍፍል ዙሪያ ስላካሄዱት ውይይት ያወጣው መረጃ የለም።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ በማህበራዊ ትስስር ገጾቻቸው ባጋሩት መረጃ ከአምባሳደር ማሲንጋ ጋራ “ለትግራይ በጣም አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ተወያይተናል” ሲሉ ገልጸዋል።

በክልሉ ዘላቂ ሰላምን የማስፈን ጉዳይ እና የፕሪቶርያው ስምምነት አፈጻጸም፣ በውይይቱ ከተነሱ ጉዳዮች መካከል መኾናቸውንም ጠቁመዋል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ በክልሉም ይኹን በአገር አቀፍ ደረጃ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚያደርገው እንቀስቃሴ ስለሚያስፈልገው ድጋፍ መነጋገራቸውንም ጠቅሰዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በተመሳሳይ ህወሓት በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ባጋራው መረጃ አምባሳደር ማሲንጋ ከፓርቲው ሊቀመንበር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) እና ከምክትላቸው አቶ አማኑኤል አሰፋ ጋር መወያየታቸውን አስታውቋል።

በተጨማሪም አምባሳደሩ “በቅርቡ ፓርቲው ባካሄደው ጉባኤ ከተመረጡ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፣ ከወጣቶች፣ ሙሁራን እና ሴት ከፍተኛ የፓርቲው አመራሮች ጋር ተወያይተዋል” ብሏል።

የውይይታቸው ዋነኛ አጀንዳም የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት እና የትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ እንደነበር ጠቁሟል።

“በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት መሰረት ወራሪ ሀይሎች ከተቆጣጠሯቸው የትግራይ አከባቢዎች አለመውጣታቸውን፣ በወራሪዎች ቁጥጥር ስር በሚገኙ የትግራይ አከባቢዎች የሚኖሩ የክልሉ ነዋሪዎች ነጻ አለመውጣታቸውን፣ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው አለመመለሳቸውን፣ በትግራይ ህዝብ ላይ የዘር ፍጅት የፈጸሙ አካላት ተጠያቂ መሆናቸው አለመረጋገጡ፣ በማንነታቸው ምክንያት በእስር ላይ የሚገኙ የመከላከያ አባላት የሆኑ የትግራይ ክልል ተወላጅ ወታደሮች አሁንም አለመፈታታቸውን፣ የህወሓት ህጋዊ ሰውነት አለመመለሱን፣ በአጠቃላይ በፕሪቶርያው ስምምነት መሰረት ዋናዋና ጉዳዮች ባለመፈጸማቸው በትግራይ ህዝብ ላይ የተፈጸመው የዘር ማጥፋት መልኩን ቀይሮ መቀጠሉን” የተመለከቱ ዝርዝር ማብራሪያዎች ለአምባሳደሩ ተሰጥቷቸዋል ብሏል።

“አምባሳደሩ በበኩላቸው የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ መተግበር የመንግስታቸው እና አለምአቀፉ ማህበረሰብ አቋም መሆኑን ገልጸውልናል” ብሏል።

በኢትዮጵያ የአሜሪካን አምባሳደር የሆኑት ኤርቪን ማሲንጋ በህወሓት አመራሮች መካከል የተፈጠረውን ውዝግብ ለማርገብ ትኩረት ያደረገ የሶስት ቀን ጉብኝት ለማድረግ ነሃሴ 20 ቀን 2016 ዓ.ም መቀለ መግባታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

የአምባሳደሩ ጉብኝት በክልሉ የሚስተዋሉ “የፖለቲካ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት አስፈላጊነትን ለማጉላት” ያለመ ነው ሲል ኤምባሲው መግለጹን በዘገባችን ተካቷል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button