ዜናፖለቲካ

ዜና፡ በኮንሶ ዞን ሰገን ወረዳ በተፈጸመ ጥቃት በትንሹ 13 ሰዎች መገደላቸውና በመንግስት ንብረት ላይ ውድመት መድረሱ ተነገረ

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 16/ 2016 ዓ/ም፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮንሶ ዞን ሰገን ወረዳ በተፈጸመ ጥቃት ስምንት የፖሊስ አባላትን ጨምሮ አምስት ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው ተነግሯል።

የሰገን ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ኡርማሌ ኡጋንዴ ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ጥቃቱ “የጽንፈኛ ቡድን አባላት” ሲሉ በጠሯቸው ግለሰቦች ባሳለፍነው ቅዳሜ ነሐሴ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. መፈጸሙን ገልጸዋል።

አስተዳዳሪው አክለውም የሟቾች ቁጥር 14 መድረሱን አስታውቀዋል።

“በሰገን ወረዳ አስተዳደር እና በአካባቢው የመንግስት መዋቅሮች ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ ጥቃት አድራሾቹ በሰላማዊ ሰዎች እና በመንግስት ሰራተኞች ላይ አነጣጥረዋል” ያሉት አስተዳዳሪው አክለውም፤ ተሽከርካሪዎችን፣ ኮምፒውተሮችን እና ሞተር ሳይክሎችን ጨምሮ የተለያዩ ንብረቶችን በመዝረፍ ላይ መሰማራታቸውን ገልጸዋል።

አቶ ኡርማሌ ኡጋንዴ እንዳስታወቁት ጥቃቱን ያደረሱት ሃይሎች በፖሊስ ጣቢያ ላይ ከፍተኛ ጥቃት በመሰንዘር ከጣቢያው ውስጥ የነበሩ መሳሪያዎችን እና ሌሎች ንብረቶችን መውሰዳቸውን ገልጸዋል።

አክለውም “የአከባቢው ሚሊሻዎች እና የፖሊስ ሃይሎች በታጣቂዎቹ የበላይነት ከአካባቢው ለቀው እንዲወጡ በተደረጉበት ወቅት ጽንፈኛ ሃይሎቹ በርካታ ቤቶችን አቃጥለዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

ጥቃቱን ተከትሎ የተወሰኑ ነዋሪዎች ሲፈናቀሉ ሌሎች ሰዎች ደግሞ በአሳዛኝ ሁኔታ ተገድለዋል ያሉት አስተዳዳሪው፤ “የፖሊስ አባላቱ የተገደሉት የመንግስትን ቢሮ በጀግንነት ሲከላከሉ ነው” ሲሉ አብራርተዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በተጨማሪም ጥቃት አድራሾቹ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋርዱላ ዞን ከሚገኘው ድራሼ ወረዳ እና ቡርጂ ዞን ውስጥ ከሚገኘው ቀያት ቀበሌ የተውጣጡ የ”ተደራጁ ግለሰቦች” መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከቅዳሜ ምሽቱ ጥቃት በኋላ የፖሊስ ሃይሎች ወደ ሰገን ከተማ ገብተው የነበረ ቢሆንም በመጨረሻ “ጽንፈኛ ቡድኑ” በያዘው የሃይል የበላይነት ምክንያት አከባቢውን ለቀው ለመውጣት መገደዳቸውን የወረዳው አስተዳዳሪ አክለው ገልጸዋል።

አያይዘውም ታጣቂዎቹ የመንግስት ተቋማት ህንጻዎችን ማቃጠላቸውን እና ፖሊስ ጣቢያ፣ የከተማው አስተዳደር ፅህፈት ቤት፣ የአካባቢውን ሆስፒታል እና የፋይናንስ ጽህፈት ቤቶች ላይ ዘረፋ መፈጸማቸውን ገልጸዋል።

የወረዳው አስተዳዳሪ አክለውም “የጥቃቱ መጠን ከፍተኛ ነው” ያሉ ሲሆን፤ አክለውም በአሁኑ ጊዜ የጠፉ ግለሰቦችን በማፈላለግ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የወረዳው አስተዳዳሪ አያይዘውም ጥቃቱ እስከ ማክሰኞ ምሽት ድረስ መቀጠሉን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የሀገር መከላከያ ሰራዊት እና የፌደራል ፖሊስ አባላት ወደ አካባቢው ገብተው ቡድኑ እንዲሸሽ መደረጉ የተገለጸ ሲሆን፤ ባለፉት አራት ቀናት ውስጥ ያልታወቁ ሰዎች አስከሬን እየተገኘ መሆንኑንም አንስተዋል።

አቶ ኡርማሌ፤ በድራሼ ወረዳ በተለይም በሆንቴ ቀበሌ በክልሉ ልዩ ሃይል ፖሊሶች ላይ በተፈፀመው ወንጀል አብዛኞቹ ጥቃት ፈፃሚዎች በሌሉበት የቅጣት ውሳኔ እንደተላለፈባቸው ገልጸዋል።

አክለውም “ከዚህ ቀደም በፈጸሙት ጥፋት በመንግስት ይፈለጋሉ” ሲሉ አስረድተዋል።

እንደ አቶ ኡርማሌ ገለጻ፣ ጥቃት አድራሾቹ ቀደም ሲል በአካባቢው ጥቃት ሲሰነዝሩ እንደነበርና ይህም ለሰላማዊ ሰዎች፣ ለመንግስት ሰራተኞች እና ለፖሊስ ሃይሎች ህይወት ማለፍ ምክንያት መሆኑ ተጠቁሟል።

የኮንሶ ዞን ኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት በበኩሉ በትናንትናው ዕለት በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በ”ጽንፈኛ ሃይሎች” ጥቃት እስካሁን ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙን አስታውቋል።

መግለጫው አክሎም በቅርቡ በተፈጸመው ጥቃት “አካባቢውን በማተራመስ እና የህዝቡን ሰላም በማደፍረስ ላይ የሚገኙት ፀረ ሰላም ሃይሎች”፤ የወረዳውን አስተዳደር ህንጻ ጨምሮ ግብርና ጽ/ቤት፣ ፖሊስ ጣቢያ፣ የምክር ቤቱ አዳራሽ እና ማዘጋጃ ቤት መውደማቸውን ገልጿል።

በተጨማሪም ሆስፒታሎች ውስጥ የሚገኙ ዲጂታል የህክምና መሳሪያዎች፣ የመንግስት ተሽከርካሪዎች እና 23 የመንግስት ሴክተር መስሪያ ቤት እቃዎች መዘረፋቸው ተገልጿል።

የኮንሶ ዞን በሚያዚያ ወር 2014 ዓ.ም. የ”ጽንፈኛ ቡድኖች” ጥቃት ኢላማም እንደነበረ ይታወሳል።

አዲስ ስታንዳርድ በወቅቱ በኮንሶ ዞን ከሚገኙ 10 ቀበሌዎች መካከል 19,000 የሚደርሱ ሴቶችና ልጃገረዶችን ጨምሮ በአጠቃላይ ወደ 37,000 የሚጠጉ ሰዎች በውስጣዊ የጸጥታ ችግሮች ምክንያት መፈናቀላቸውን መዘገቡ ይታወሳል።

በተፈጸሙ ጥቃቶችም በሰብል፣ በእንስሳት እና በንብረት ላይ ዝርፊያ እና ውድመት የተከሰተ ሲሆን፤ የሰዎች ህይወት ማለፉም ይታወሳል።አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button