ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: በዩኒቨርስቲ ተማሪዎቹ እገታ እጄ የለበትም ሲል የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት አስተባበለ፣ ለእገታው ተጠያቂ መሆን ያለበት መንግስት ነው ብሏል

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5/2016 ዓ.ም፡-ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ ሲጓዙ በታጣቂዎች በታገቱ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ላይ ምንም አይነት አስተዋጽኦ የለኝም ሲል የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ባወጣው መግለጫ አስተባበለ።

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ገርበ ጉራቻ ከተማ በተፈፀመው የተማሪዎች እገታ ላይ “የመንግሥት ደህንነት አካላት” እና “የበታች የፓርቲ ካድሬዎች” እጅ አለበት ብሎ እንደሚያምን አስታውቋል።

የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ቢሮ ሃላፊው ሀይሉ አዱኛ ለመንግስትመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ እገታው የተፈጸመው በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ሸኔ ብለው የጠሩት) ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የኦሮምያ ክልል መንግስት የሰጠውን መግለጫ ተከትሎ ቡድኑ ትላንት ሐምሌ 4 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ነው ያስተባበለው።

የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ትላንት ሐምሌ 4 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ “ለገንዘብ ተብሎ የሚደረጉ አፈናዎች በቅርቡ ወደ ጉልህ ማህበራዊ: ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ተቀይረዋል::” ሲል በመግለጽ በጉዳዩም ላይ ውስብስብ የኢኮኖሚ መስተጋብር አለ ብሎ እንደሚያምን አመላክቷል።

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ገርበ ጉራቻ ከተማ አቅራቢያ ታፍነው የተወሰዱ ከ160 በላይ ተማሪዎች መለቀቃቸውን የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ቢሮ ቢያስታውቅም፣ የታጋች ተማሪዎች ቤተሰቦች ልጆቻቸው እንዳልተፈቱ በመግለጽ የመንግስት ሀሰተኛ መረጃ እያሰራጨ ነው ሲሉ ኮንነዋል፤ አሁንም እንደታገቱ ነው በማለት ስጋታቸውን መግለጻቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

አዲስ ስታንዳርድ ያነጋገራቸው የታጋቾች ቤተሰቦች የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ኮሚኒኬሽን የሰጠውን መግለጫ ሐሰት ነው ሲሉ ማስተባበላቸው በዘገባው ተካቷል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በቅርቡ መንግስት በሰጠው መግለጫ የተሰማቸውን ቅሬታ በመግለጽ “እስከ ዛሬ አንድም ተማሪ በመንግስት ታጣቂዎች አልተፈታም፤ አጋቾቹ በየቀኑ ከልጆቻችን ጋር ያገናኙናል፤ የተመለከቱት የመንግስት ሃይል አለመኖሩንም ነግረውናል” ሲሉ ገልፀዋል።

የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት በመግለጫው የመንግሥት መዋቅር መዳከሙን እንደ ጥሩ አጋጣሚ የሚጠቀሙ አካላትም ለገንዘብ ሲሉ እገታውን ይፈፅማሉ በማለት ጠቁሟል።

ስራ አጥ የሆኑ እና በሥርዓቱ ተስፋ የቆረጡ ሰዎችም እገታው ላይ ተሳታፊ ሊሆኑ ይችላሉ ሲል መግለጫው አካቷል።

ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ ሲጓዙ በታጣቂዎች ታፍነው ከነበሩ ተማሪ ቤተሰቦች ለማስለቀቂያ ከፍተኛ ገንዘብ መጠየቃቸው ለጭንቀት እንደዳረጋቸው መግለጻቸውን የተመለከተ ዘገባ መቅረቡ ይታወሳል።

አንድ የሶስተኛ አመት የደባርቅ ዩኒቨርስቲ ተማሪ እሀቷ እንደታገተችባት ለአዲስ ስታንዳርድ ያስታወቀች የታጋች ቤተሰብ ለማስለቀቂያ ግማሽ ሚሊዮን ብር ቤተሰቡ እንዲከፍል መጠየቁን ገልጻለች። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button