ህግ እና ፍትህዜናፖለቲካ

ዜና፡ በደራ ወረዳ በተፈጠረ ግጭት የሶስት ሰዎች ህይወት አለፈ፤ በምዕራብ ወለጋ ተጨማሪ ሶሰት ሰዎች "በመንግስት ሃይሎች" ተገደሉ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13/2016 ዓ/ም፦ በኦሮሚያ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት ቢያንስ ሶስት ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ:: ረቡዕ ሐምሌ 10፣ 2016 በጅሩ ዳድ መንደር የደረሰውን ጥቃት “የፋኖ ታጣቂዎች” እንደፈፀሙት አንድ የአከባቢው ነዋሪ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል::

የጥቃቱ ሰለባዎችም የ15 ዓመት ታዳጊ ሙሉጌታ ፣ የ17 ዓመት ወጣት አባቡ ተሰማ እና የ30 ዓመት ወጣት ጆቦ አበራ የሚባሉ ነዋሪዎች መሆናቸው ተገልጿል። ሙሉጌታ እና አባቡ ቀደም ሲል በእረኛነት ተቀጥረው ይሰሩ ነበር።

ጥቃቱን ተከትሎ በተፈጠረ የፀጥታ ስጋት በርካታ ሰዎች መፈናቀላቸውን የአይን እማኙ ጨምሮ ገልጿል:: በርካቶች አጎራባች በሆኑ በወረ ጋብሮ፣ በማንቄታ ዋሪዮ እና በሂንዳቡ አቦቴ ወረዳ በሚገኙ መንደሮች ተሰደዋል ብሏል።

በተለይም በጅሩ ዳድ መንደር ከአርባ በላይ አባወራዎች ከዳካ አካባቢ በፀጥታ ስጋት የተነሳ ተፈናቅለው ወደ ተጠቀሱት አካባቢዎች ሄደዋል ሲል ምንጩ ገልጿል::

የደራ ወረዳ በፋኖ ሚሊሻዎች እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት  እንዲሁም በተለያዩ የታጠቁ ሃይሎች እና የመንግስት ሃይሎች መካከል በሚደረጉ ውጊያዎች የጦርነት አውድማ ሆኖ ቆይቷል። እነዚህም ግጭቶች የሰላማዊ ሰዎችን ህይወት ማጥፋታቸውን ቀጥለዋል።

ባለፈው ወር አዲስ ስታንዳርድ በደራ ወረዳ በተፈጸመ ጥቃት በትንሹ አራት ንፁሀን ዜጎች መገደላቸውን መዘገቡ ይታወሳል::

በታህሳስ 2015 የደራ ወረዳ ለሁለት ቀናት የፈጀ ጥቃት ገጥሞት የነበረ ሲሆን በዚህም የአስራ ስምንት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ሌሎች 6 ሰዎች ቆስለዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ለደህንነት ሲባል ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ በደራ ወረዳ ጉንዶ መስቀል ከተማ ነዋሪ የሆኑ መምህር ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለፁት “በተደጋጋሚ ጥቃት በሚደርስባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች በአከባቢው ሰፍሮ የሚገኘውን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከጥቃት እንዲጠብቃቸው ሲጠይቁ ቆይተዋል::”

ነገር ግን ወታደራዊ አመራሮቹ ጣልቃ የመግባት ፍቃድ እንደሌላቸው ለነዋሪዎች ማሳወቃቸውን አክለው ገልፀዋል::

በደራ ወረዳ እየታየ ያለው ሁከትና ግጭት በትምህርት ሂደት ላይም ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ እንደሚገኝ ተናግረዋል::  እንደ መምህሩ ገለጻ በወረዳው ከሚገኙት 93 የትምህርት ማዕከላት ውስጥ ተማሪዎችን መቀበል የቻሉት አራቱ ብቻ መሆናቸውን አስረድተዋል::

በተያዘ ዜና በምዕራብ ኦሮሚያ በታጣቂ ሃይሎች እና በመንግስት ሃይሎች መካከል በተፈጠረ ግጭት የሰዎች ህይወት መጥፋቱ ተገልጿል::

በምዕራብ ወለጋ ዞን ቤጊ ወረዳ የካርማ ጉንፊ መንደር ነዋሪ ከሰሞኑ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለፁት ሐምሌ 8 ቀን 2016ዓ.ም ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ላይ የመንግስት ሃይሎች ረመዳን ጅባን እና ቶፊቅ ዳማራን የተሰኙ ግለሰቦችን ላሎ ወደተሰኘ ወታደራዊ ካምፕ የወሰዱ ሲሆን በዚያኑ ቀን ከምሽቱ 3:00 ሰዓት አካባቢ አስከሬናቸው በቤጊ-ቆንዳላ መንገድ መገኘቱ ተገልጿል::

ረመዳን ጂባ  እና ቶፊክ ዳማራ የ25 እና የ24 ዓመት ወጣት ሲሆኑ “ሸኔ” ን ትደግፋላችሁ በሚል ተጠርጥረው በመንግስት ሃይሎች መገደላቸው ተገልጿል::

እንደ ነዋሪው ገለፃ ከሆነ ሁለቱም ተጎጂዎች ሰላማዊ ሰዎች ሲሆኑ ረመዳን ጂባ በቅርቡ ትዳር የመሠረተ እና ኑሮውንም በእርሻ ስራ የሚመራ ነበር::

ማክሰኛ ዕለታ ሐምሌ 9፣ 2016ዓ.ም በምዕራብ ወለጋ ዞን በቆንዳላ ወረዳ በተፈፀመ ሌላ ግድያ የሰላማዊ ሰዎች ህይወት ማለፉን ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ነዋሪ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።

ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ላይ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በዋንጃ መንደር ነዋሪ የሆነ ታዋካል መሀመድ የተባለ የ30 ዓመት ወጣት መግደላቸውን ነዋሪው ተናግሯል።

“ታዋካል በጎረቤት ቤት ቡና እየጠጣ ሳለ የመንግስት ሃይሎች መጥተው በግዳጅ ወደ ውጭ አውጥተው የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊትን ትደግፋለህ በማለት ተኩሰው ገደሉት” ሲሉ ሁኔታውን አስረድተዋል::

በምዕራብ ወለጋ ዞን የፀጥታ ችግር መባባሱንም ነዋሪው በአፅንኦት ገልጸዋል::

“የመንግስት ሃይሎች መረጃ እና ማስረጃ ሳያቀርቡ ሸኔን ትደግፋላችሁ በሚል ግለሰቦች ላይ ዒላማ ያደረጉ ግዳያዎችን መፈፀማቸውን ተከትሎ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ፍርሃት ነግሷል” ሲሉ አክለዋል::

በምዕራብ ኦሮሚያ የሚኖሩ ነዋሪዎች በመንግስት ሃይሎች እና በታጣቂ ሃይሎች መካከል በሚከሰቱ ግጭቶች ሳቢያ የጸጥታ ችግር እያጋጠማቸው እንደሆነ አዲስ ስታንዳርድ በቅርብ መዘገቡ ይታወሳል::

ይህም በአከባቢው የሰላማዊ ዜጎች መፈናቀልን፣ የጤና እና የትምህርት ተደራሽነትን መገደብ እንዲሁም ከባድ የፍርሃት ድባብ በነዋሪው ላይ አስከትሏል::

ነገር ግን የኦሮሚያ ክልል ቃል አቀባይ ሃይሉ አዱኛ  የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ሆን ብለው በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት አያደርጉም ሲሉ በቅርቡ ከቪኦኤ ጋር ባደረጉት ቆይታ መናገራቸው ይታወሳል::

ቃል አቀባዩ አክለውም “ሸኔ” በአሸባሪነት የተፈረጀ ሲሆን ለ”ሸኔ” የሚደረግ ማንኛውም አይነት ድጋፍ ተጠያቂነትን ያስከትላል ብለዋል::

ለታጣቂ ቡድኑም መረጃ፣ የሎጀስቲክስ ድጋፍ ወይም ማንኛውም አይነት ድጋፍ ሲያደርጉ የተገኙ ግለሰቦች ተይዘው ለድርጊታቸው ተጠያቂ እንደሚሆኑም አስረድተዋል።አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button