ዜናፖለቲካ

ዜና: በዶ/ር ደብረጺዮን የሚመራው ህወሓት አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 16 ከፍተኛ አመራሮቹን “ከፓርቲው አባልነት አባርሪያለሁ፣ ውክልናቸውንም አንስቻለሁ” ሲል ገለጸ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 7/2017 ዓ.ም፡- በደብረጺዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ምክትል ሊቀመንበሩ የነበሩትን አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 16 ነባር አባላቱን እና ከፍተኛ አመራሮቹን ማገዱን አስታወቀ።

በዶ/ር ደብረጺዮን የሚመራው ህወሓት መስከረም 5 ቀን 2017 ዓ.ም አካሄድኩት ባለው የማዕከላዊ ኮሜቴ ስብሰባ ሶስት ውሳኔዎችን አሳልፏል።

ከውሳኔዎቹም መካከል 16ቱ ከፍተኛ አመራሮቹ ህወሓትን ወክለው ምንም አይነት የፖለቲካዊ ውስኔ መፈጸም አይችሉም የሚለው እግድ ይገኝበታል።

“በፓርቲው ውክልና ያገኙትን የጊዜያዊ አስተዳደሩን ስልጣን በመጠቀም እና ህገወጥ የሆነ በርካታ ገንዘብ በመበተን በፓርቲው ውስጥ ሁነው ፓርቲውን ለማፍረስ እና የክልሉን ህዝብ አንድነት ለመበታተን እየሰሩ ነው” ሲል ኮንኗል።

“ፓርቲውን ወክለው በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ የያዙትን ስልጣን ለማስተካከል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር እና በመግባባት ውሳኔ እንዲያገኝ ይደረጋል” ሲል አስታውቋል።

ከፓርቲው አባልነት የተባረሩ እና የነበራቸው የፓርቲው ውክልና ከተነሳባቸው ነባር አባላቱ እና አመራሮቹ መካከል የቀድሞ የመቀለ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት የነበሩት ፕሮፌሰር ክንደያ ገ/ሂወት፣ የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ሃላፊው ረዳኢ ሓለፎም፣ ዶ/ር ሓጎስ ጎደፋይ፣ አቶ በየነ ምክሩ ይገኙበታል።

ሌላኛው ውሳኔ የተላለፈበት ጉዳይ “ከፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ውጭ ነጻ ባልወጡ የትግራይ ግዛቶች ላይ ጊዜያዊ አስተዳደር በማቋቋም ሪፈረንደም ለማካሄድ እንቅስቃሴ እየተካሄደ ነው” ሲል በመግለጽ “እንቅስቃሴው መቆም ይገባዋል” የሚለው ይገኝበታል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር እና የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 17 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፣ የድርጅቱ ቁጥጥር ኮሚሽን፣ አብዛኞቹ የደቡብ እና የደቡብ ምሥራቅ ትግራይ ወረዳዎች እንዲሁም የመቀለ ከተማ ክፍለ ከተሞች በሓወልቲ አደራሽ በተካሄደው ጉባኤ ሳይገኙ መቅረታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

በከፍተኛ አመራሮቹ ክፍፍል መካከል በተደረገው በ14ኛው የህወሓት ጉባኤ ያልተገኙ እና በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ያሉ “የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እና ስራ አስፈጻሚዎች ድርጅቱን እንደማይወክሉ” የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል ማስታወቃቸውም በዘገባው ተካቷል።

በሌላ በኩል በሐወልቲ ሰማእታት አደራሽ በተካሄደው የህወሓት ጉባኤ “የሚተላለፉ ውሳኔዎች ተቀባይነት የላቸውም” ሲል በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ቡድን ባወጣው መግለጫ ማስታወቁን መዘገባችንም ይታወሳል።

በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ውስጥ ያሉ ሁለቱም ቡድኖች በክልሉ የሚታየውን ፖለቲካ ሁኔታ ወደ ቀውስ የሚከት እና በህዝቡ ዘንድ መከፋፈልን ከሚፈጥሩ ማናቸውም እንቅስቃሴዎች እንዲታቀቡ ሲሉ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት እና የሰላምና ጸጥታ ሴክሬተሪያት ሃላፊ ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ ማስጠንቀቃቸውን መዘገባችን ይታወሳል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button