ዜናፖለቲካ

ዜና፡ በጉራጌ ዞኖች ከ55 ባላይ ሰዎች መገደላቸውን ጎጎት ገለጸ፤ የወሰን ማስከበር ስራና ግጭት አፋጣኝ እልባት እንዲያገኝ ጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 30/ 2016 ዓ/ም፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞኖች በተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች እና ድንበር ዘለል ጥቃቶች ከ55 በላይ ንፁኃን ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውንና በርካቶች መፈናቀላቸውን ለጉራጌ አንድነት እና ፍትሕ ፓርቲ (ጎጎት) አስታወቀ። 

ጎጎት ዛሬ በወጣው መግለጫ፤ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከተመሰረተ ጀምሮ በጉራጌ አካባቢ ተከታታይነት ግጭት፣ ግድያ፣ አስር፣ ድብደባ፣ እገታና ዘረፋ እየተፈጸመ መሆኑን ገልጿል።

በኢንሴኖ ዙሪያ ከመጋቢት 21 እስከ ነሐሴ 26, 2016 ዓ.ም ህጻናትና ጨምሮ 32 ወንዶችና 12 ሴቶች በጠቅላላው 44 ሰዎች ተገድለዋል ያለው ፓርቲው ከ6000 በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን እንዲሁም ከ36 ሰዎች በእስር ላይ እንደሚገኙ አስታውቋል።

አሁን ላይ ከ5 በላይ ቋሚ የፀጥታ ኃይል ስምሪትም የሚፈልጉ የግጭት ስጋት ያንዣበባቸው አካባቢዎች ተፈጥረዋል ብሏል።

ጎጎት በመግለጫው፤ ቆስየ ሌላው በጉራጌ አካባቢ የፀጥታ መደፍረስ የተፈጠረበትና ለአመታት መፍትሄ ሳይሰጠው የቆየና አካባቢ መሆኑን ገልጾ በአካባቢው “ሙሉ ለሙሉ መንግስታዊ መዋቅር ፈርሶ በጎበዝ አለቆች እጅ የገባ ነው” ብሏል። 

ፓርቲው “ቆስየ በህግና በታሪክ የጉራጌ ዞን አካል ቢሆንም ላለፉት 5 አመታት ከዞኑ ቁጥጥር ውጪ በሌሎች አካላት ቁጥጥር ስር ይገኛል። በርስታቸው ባዳ ተደርገው ከአካባቢው እንዲሰደዱ ተደርገው ሌሎች እንዲሰፍሩበት ተደርጓል” ሲል ገልጿል። 

የአካባቢው ነዋሪ ለከፋ ሰብአዊ መብት ጥሰት ተጋልጧል ያለው ጎጎት ነባር የገበያ ቀኖች ሳይቀር መቋረጣቸውንና ግብር የሚሰበስበውም ከዞኑ ውጭ ባለ አካል ነው ብሏል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በሶዶ ወረዳዎች ያለው ሁኔታም ከምስራቁ ዞን የፀጥታ ኃይል አቅም በላይ ሆኖ ህዝቡ የመከላከያ ሰራዊት የእለት ተእለት ጥበቃ የሚፈልግ ሆኗል ተብሏል።

የኃይማኖት አባቶችና ገዳማትን ሳይቀር ኢላማ ያደረገ እገታ እና ዘረፋ መስፋፋቱንና እልባት አለማግኘቱን ያስታወቀው ፓርቲው በአካባቢው በከፍተኛ ትጥቅ እና ቅንጅት የታገዘ ጥቃት እየተከናወነ ይገኛል ብሏል።

መግለጫው “ሰዎች ከቤታቸው ታግተው ይወሰዳሉ፣ ይደበደባሉ፣ ይገደላሉ። ብዙ ጊዜደግሞ ለማስለቀቂያ ተብሎ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ ይጠየቃሉ። በዚህ መልኩ እስካሁን በሚሊዮኖቸ የሚቆጠር ገንዘብ ከህዝብ ተሰብስቦ ለአጋቾች ተሰጥቷል። በመንገደኞች ላይም ድንገተኛ ጥቃቶች በመክፈት እገታዎች ሲፈፀሙ ተስተውሏል” ብሏል። 

ሁለቱ የሶዶ ወረዳዎች ከጥቅምት 2015 ዓ.ም እስከ ነሐሴ 28 2016 ዓ.ም 10 ሰዎች በታጣቂዎች ተገለዋል፣ ከ23 በላይ የሚበልጡ ሰዎች ድብደባ ተፈጽሞባቻ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል ሲል የገለጸው ጎጎት፤  ከ16 በላይ የታገቱ ገበሬዎች፣ የሃማኖት አባቶችና ነዋሪዎች ለማስለቀቂያ ከ2900000 ብር በላይ ከፍለዋል ብሏል።

በወልቂጤ ከተማ ከወሰን ማስከበር ጋር የተከሰተው አለመግባባት ምንም ዓይነት ዕልባት ባለማግኘቱ አካባቢው እንደ ቀደሙት ጊዜያት ሁሉ ወደ ግጭት ሊያመራ ይችላል የሚል ስጋት ማየሉም በመግለጫው ተመላክቷል።

የቀቤና የልዩ ወረዳው ምስረታ፤ በልዩ ወረዳው ያሉትን ብዙሃን ጉራጌዎች መብት የጨፈለቀ መሆኑ ተቀባይነት የሌለው ነው ሲል ያስገነዘበው ጎጎት፤ ልዩ ወረዳው ውስጥ የሚገኙ ጉራጌዎች “ስልታዊ በሆነ መልኩ ከመሬታቸው እየተፈናቀሉ፣ በማንናቸውም መንግስታዊና ህዝባዊ መድረኮች እንዳይሳተፉ አፈና እየፈፀመባቸው፤ ነዋሪዎች መታወቂያ፣ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ፣ ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር የመሳሰሉ አገልግሎቶች እንዳያገኙ እየተደረጉ ይገኛል” ሲል ከሷል። 

በጉራጌ ዞኖች ያሉት የፀጥታ ችግሮች በአብዛኛው ድንበር ዘለል ጥቃቶች ናቸው ያለው ፓርቲው “የሸኔ እና የፋኖ” እንቅስቃሴ መኖሩን ገልጾ በህዝቡ ላይ በ5 ግንባሮች ጥቃት እየተፈፀመ ነው ብሏል። መነሻቸው ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሆኑ ሌሎች “ፅንፈኛ ኃይሎች” መኖራቸው መዘንጋት የለበትም ሲል አሳስቧል።

ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከተመሰረተ ጀምሮ አካባቢው ተከታታይነት ባለው ግጭት እየታመሰ ይገኛል ያለው ፖርቲው በምስራቅ መስቃን እና ማረቆ የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው የ11/9 ቀበሌዎች ጉዳይ በህዝበ ውሳኔ መፍትሄ እንዲያገኝ በማድረግ ህዝቡ በመረጠው ወረዳ እንዲተዳደር እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል።

ፓርቲው በመግለጫው በቆስየ አካባቢ የተፈጠረው “ወረራ” በአስቸኳይ እንዲቆም፣ መንግስት በወራሪዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድና የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ፣ እንዲሁም በአካባቢው የጉራጌ ዞን መንግስታዊ ተቋማት መደበኛ ስራቸውን እንዲጀምሩም ጥይቋል።

በሶዶ ወረዳዎች ማለትም በሪፌንሶ፣ አማውቴ፣ ጢያ፣ በዱግዳ ቀላ እና ሌሎች አካባቢዎች ላይ የሚፈፀመው ዝርፊያ፣ እገታ እና አግቶ ገንዘብ መቀበል ለማስቆም ተጨማሪ የመከላከያ ሰራዊት ስምሪት እንዲደረግ አክሎ ጥሪ አቅርቧል።

ህግ ይከበር፣ ህዝብ ከጥቃት ይጠበቅ በሚል መንግስት ኃላፊነቱን እንዲወጣ በመቀስቀስ የዜግነት ግዴታቸውን በመወጣታቸው ምክንያት የታሰሩ የጉራጌ የፖለቲካ እስረኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱም ፓርቲው ጠይቋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button