ህግ እና ፍትህዜና

ዜና፡ በጎንደር የሁለት አመት ህጻን በአጋቾች መገደሏን ተከትሎ ህዝባዊ ቁጣ ተቀሰቀሰ፤ የሁለት ሰዎች ህይወት አለፈ

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 28/ 2016 ዓ/ም፦  በአማራ ክልል፤ በጎንደር ከተማ ኖላዊት ዘገየ የተባለች የሁለት አመት ህፃን ትላንት ነሀሴ 27 ቀን በአጋቾች ተገድላ መገኘቷ ተከትሎ ህዝባዊ ቁጣ ተቀሰቀሰ። ግድያውን ተከትሎ በተካሄደ ሰልፍ ሁለት ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ህፃኗ ነሐሴ 24/2016 ዓ.ም በጎንደር ከተማ ከሚገኘው መኖሪያ ቤት ተወስዳ መታገቷን ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።

አጋቾቹ ለአባቷ ስልክ በመደወል “ልጅቷን አግተናት ከእኛ ጋ ነች፤ የተሰበሰበውን ሰው በትኑ፤ ለፖሊስ ከተናገራችሁ ግን እንገድላታለን” የሚል ማስፈራሪያም፤ ማስጠንቀቂያም ይደርሳቸዋል። 

አጋቾቹ ለማስለቀቂያ የሚሆን በመጀመሪያ አንድ ሚሊየን ብር የህጻኗን ወላጆች የጠየቁ ሲሆን በኋላ ላይ በድርድር ጥያቄያቸውን ወደ 300 ሺህ ብር ዝቅ ማድረጋቸው አዲስ ስታንዳርድ ያነጋገራቸው የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ገልጿል።

በግል ድርጅት ውስጥ በአሽከርካሪነት ተቀጥረው የሚሰሩት አባት እና ፀጉር ቤት ውስጥ የሚሰሩት የህጻን ኖላዊት እናት በልመና ያሰባሰቡትን 200ሺህ ብር ለአጋቾቹ በመክፈል የልጃቸውን መለቀቅ ሲጠብቁ፤ ህፃኗ ተገድላ ጓሮ ተጥላ እንደተገኘች አስረድተዋል።

ስማቸው ለደህንነት ሲባል እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የአይን እማኝ በበኩላቸው ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለጹት፤ የህጻኗን ግድያ ተከትሎ ትናንት ነሀሴ 27/2016ዓ.ም. በጎንደር ከተማ ቁጣ መቀስቀሱን ገልጸዋል።

ቁጣቸውን ለመግለጽ አደባባይ በወጡ ሰዎች ላይ “በመንግሥት የጸጥታ ሃይሎች” በተከፈተ ተኩስ በትንሹ ሁለት ሰዎች መገደላቸውንና ሌሎች ሁለት ሰዎች መቁሰላቸውን የአይን እማኙ ገልጽዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ሌላኛው በጎንደር ከተማ ነዋሪ የሆኑ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ግለሰብ፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በከተማዋ ውስጥ የእገታ እና የተደራጁ ወንጀሎች መበራከታቸውን ተናግረዋል።

“ህዝቡ የሰቀቀን ኑሮን እየገፋ ይገኛል። ከአምስት ቀን በፊትም እናትና ልጅ ቤታቸው ተቀምጠው ባሉበት በእጋቾች የእገታ ሙከረ ከተደረገባቸው በኋላ በጥይት ተገድለዋል። ልጅቷ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪ የነበረች ናት።” ያሉት ነዋሪ አክለውም፤ ከሚፈጸሙት የውንብድና ድርጊቶች ጀርባ የ”መንግሥት መዋቅር” ይኖርበታል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል። 

ከዚህ በተጨማሪ በከተማዋ በ”ፋኖ” ስም የሚንቀሳቀሱ አካላት እንዲሁም ቀድሞ በሌብነት እና ዝርፍያ ተሰማርተው የነበሩ ሰዎች በአከባቢው ያለውን የጸጥታ ሁኔታ እንደ አመቺ በመጠቀም በውንብድና ተግባሩ ላይ ተሳታፊ ሊሆኑ እንደሚችሉ ነዋሪው አክለው ገልጸዋል።

ትናንት ነሀሴ 27/2016 ዓ.ም. በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ ውስጥ በሰው እገታ ወንጀል የተጠረጠሩ 31 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ፖሊስ አስታውቋል

ባለፉት ሳምንታት በከተማው 64 የእገታ ወንጀሎች መፈጸማቸውን የገለጹት የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ ሃላፊ ረዳት ኮሚሽነር አየልኝ ታክሎ፤ የእገታ ወንጀል ከሚፈጸምባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ሴቶችና ህጻናት በግንባር ቀደም ተጠቃሽ መሆናቸውንም ረዳት ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

በተጨማሪም በከተማው የጸጥታ ስራ ህዝብና መንግስት የጣለባቸውን ሃላፊነት በአግባቡ ያልተወጡ የስነ ምግባር ጉድለት የፈጸሙና በወንጀል ድርጊት የተጠረጠሩ 14 የጸጥታ አባላት ከሃላፊነታቸው መነሳታቸውንም ረዳት ኮሚሽነር አየልኝ ታክሎ ትናንት በተካሄደው የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት አስቸኳይ ጉባኤ ላይ ባቀረቡት ሪፖርት ገልጸዋል።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ጸጥታ ምክር ቤት ዛሬ ነሐሴ 28/2016ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፤ በእገታ፣ በግድያና በዘረፋ ወንጀል የተጠረጠሩ 49 ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ገልጿል። በተጨማሪም በከተማዋ ህግ የበላይነትን ለማስፈን የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲል ተናግሯል።

በኢትዮጵያ በተለይም በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ገንዘብን ለማግኘት ሲባል የሚደረጉ የእገታ እና የአፈና ተግባራት እየጨመሩ መጥተዋል።

በጎንደር የተፈጸመው የህጻን ግድያ የተሰማው ባሳለፍነው አመት በባህርዳር ከተማ ጌትነት ባይህ የተባለ የቤት አከራይ፤ የተከራይ ልጅ የሆነችውን የ7 ዓመቷን ህፃን ሔቨንን በአሰቃቂ በሆነ መንገድ አስገድዶ ከደፈረት በኋላ አንቆ ህይወቷ እንዲያልፍ ማድረጉ መሰማቱን ተከትሎ በቅርቡ ከፈተኛ ቁጣ በቀሰቀሰበት ወቅት ነው። 

ግለሰቡ 25 ዓምት እስር የተፈረደበት ሲሆን ፍርዱ በቂና ተመጣጣኝ አይደለም በሚል በርካቶች ቁጣቸውን አያሰሙ ይገኛሉ። 

የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ፤ ግድያውን ተከትሎ በዛሬ ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገሪቱ የሚፈጸሙ የእገታ ተግባራትን አውግዞ፤ “ማንኛውም ዜጋ በህጻናት እና ሴቶች ጥቃት የሚፈጽሙ ሃይሎች በህግ እንዲጠየቁ ብቻ ሳይሆን ፍትሃዊና አስተማሪ እርምጃ እንዲወሰድባቸው በማድረግ ከተበዳዮች ጎን እንዲሰለፍ” ጥሪ አስተላልፏል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዛሬ ነሃሴ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተለይም በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች እገታዎች በአሳሳቢ ሁኔታ መባባሳቸውን አስታውቆ መንግስት ውጤታማ እርምጃዎችን እንዲወስድ ጠይቋል።

እገታዎቹ የተባባሱት ከተራዘሙ የትጥቅ ግጭቶች ጋር ተያይዞ “በተፈጠረው የሕግ ማስከበር እና የመንግሥት መዋቅር መላላት ሳቢያ ነው” ሲል ኮሚሽኑ ገልጿል።

የኢሰመኮ አደረኩት ባለው ክትትልና ምርመራ ውጤት መሰረት ተባብሰው የቀጠሉት እገታዎች የሚፈጸሙት “ለዘረፋ በተደራጁ ቡድኖች እና በአንዳንድ የመንግሥት የጸጥታ አካላት አባሎች” መሆኑን አመላክቷል።

የእገታ ተግባርን ዘላቂ በሆነ መልኩ ለማስቆም ለሰዎች እገታ መነሻና አባባሽ ምክንያት የሆነውን የሰላም መደፍረስና የትጥቅ ግጭትን በዘላቂነት፣ በሰላማዊ መንገድ መፍታት ይገባል ሲልም አሳስቧል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button