ዜናፖለቲካማህበራዊ ጉዳይ

ዜና: በትጥቅ ግጭቶች ምክንያት በንጹሃን ላይ እየደረሰ ያለው የሞት እና የአካል ጉዳት አሳሳቢነት ቀጥሏል - ኢሰመኮ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ /2016 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የ2016 ዓ.ም የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታን የዳሰሰ ባለ 132 ገጽ ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የሥራ ዘመናቸው ማብቃት ጋር በተገጣጠመው በዚህ በ3ተኛው የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክልሎች የትጥቅ ግጭቶች፣ ጥቃቶች ወይም የጸጥታ መደፍረሶች ከሐምሌ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. እስከ ግንቦት ወር 2016 ዓ.ም. መመዝገቡን አስታውቋል።

በዚህ ሳቢያ በታጣቂ ኃይሎች እና በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በተወሰዱ እርምጃዎች በሲቪል ሰዎች ላይ የሚደርስ የሞት እና የአካል ጉዳት አሳሳቢነት ቀጥሏል ብሏል፤ በተለይም በትጥቅ ግጭት ዐውድ ውስጥ በሲቪል ሰዎች ላይ የሚደርሱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እንደቀጠሉ እና እንደተስፋፉ በሪፖርቱ ተመላክቷል።

የትጥቅ ግጭት በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮች፣ በተለይም ሴቶችና ሕፃናት፣ አካል ጉዳተኞችና አረጋውያን ለምግብና ለመሠረታዊ ሰብአዊ ድጋፍ እጥረት፣ ለጤና እና ትምህርት አገልግሎቶች መስተጓጎል ወይም መቋረጥ እንዲሁም ለሌሎች ተጨማሪ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተጋላጭ መሆናቸውም ተገልጿል።

በሪፖርት ዘመኑ በትጥቅ ግጭት፣ በግጭት ውስጥ በቆዩ አካባቢዎች እንዲሁም ግጭት በሌለበት በአንዳንድ ሁኔታዎች ወቅት ጭምር የሚፈጸም ከሕግ ውጪ የሆኑ የሲቪል ሰዎች ግድያ አሳሳቢ ሆኖ መቀጠሉን አትቷል።

በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል በሲቪል ሰዎች ላይ በትጥቅ ግጭቱ እንዲሁም በግጭቱ ዐውድ ውስጥ ከሚደርሱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች በተጨማሪ ሲቪል ሰዎችን ዒላማ ያደረገ እገታ አሳሳቢነት ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑ በሪፖርቱ ተመላክቷል።

ለ10 ወራት ተፈጻሚ ሆኖ በቆየው የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጅ በርካታ ሰዎች መደበኛ እና መደበኛ ባልሆኑ ማቆያ ቦታዎች ውስጥ ለተራዘመ እስር መዳረጋቸውን አስታውቆ ለቀናት ወይንም ለሳምንታት ለቆየ ጊዜ ያሉበት ቦታ ሳይገለጽ/ሳይታወቅ በእስር መቆየተቻውን ጠቁሟል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ከአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጁ አተገባበር ጋር ተያይዞ “ወቅታዊ ሁኔታ” በሚል ምክንያት ሰዎች ለዘፈቀደ እስር እንዲሁም ለአስገድዶ መሰወር የተዳረጉበት በርካታ ክስተቶች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች መመዝገባቸውን ጠቁሟለ።

የመንቀሳቀስ መብትን በተመለከተ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ባለው የጸጥታ ሁኔታ ወይም በሚጣሉ ገደቦች ምክንያት በተለይም በየብስ የሚደረግን እንቅስቃሴ አዳጋች ማድረጉን ገልጿል።

እንዲሁም የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ወይም በታጣቂ ቡድኖች ለተከታታይ ቀናት በሚዘጉ መንገዶች ምክንያት የሚደርሱ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ችግሮች፣ በሸቀጦች ዋጋ እና በገቢ እንዲሁም በጤና እና ትምህርት አገልግሎቶች ተደራሽነት ላይ የሚደርሱ አሉታዊ ተጽዕኖዎች በዘንድሮ በጀት ዓመትም በተለይ በአማራ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ እና በኦሮሚያ ክልሎችም መቀጠላቸው በዝርዝር ተብራርቷል።

በመጪው በጀት ዓመት ትኩረት ከሚሹ አንኳር ጉዳዮች መካከል የትጥቅ ግጭቶች በሰላማዊ ውይይት እንዲፈቱ ማድረግ፣ የሀገራዊ ምክክር እና የሽግግር ፍትሕ ሂደት ተዓማኒ አተገባበር ማረጋገጥ፣ ከፍርድ ቤት ትእዛዝ ውጪ በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎች ሁሉ በአፋጣኝ እንዲለቀቁ ወይም የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ማድረግ የሚሉት ይገኙበታል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button