ዜናፖለቲካ

ዜና፡ ኢትዮጵያ “የሶማሊያ ችግር የቀጠናውን ጸጥታ ማደፍረስ የለበትም” ስትል አሳሰበች

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 24/ 2016 ዓ/ም፦ በቀጣዩ ከድህረ አትሚስ አወቃቀር ኢትዮጵያ ባትሳተፍበት እንኳን፤ “የሶማሊያ ችግር የአከባቢውን ጸጥታ ማደፍረስ የለበትም” ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀ ሥላሴ አሳሰቡ።

አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ይህን የተናገሩት በወቅታዊ ቀጠናዊ ጉዳዮች ዙርያ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ጋዜጣዊ  መግለጫ ነው።

“የኢትዮጵያ ፍላጎት ከሶማሊያ ፌደራላዊ መንግስት ጋር በቅርቡ የተስተዋለውን አለመግባባት በውይይት መፍታት ነው።” ያሉት ሚንስትሩ አክለውም፤ ሶማሊያ እንደሃገር እንድትቆም ኢትዮጵያ ብዙ ዋጋ መክፈሏን ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ በተጨማሪ ኢትዮጵያ በርካታ የሰላም አስከባሪ ሃይል በማዋጣት ከመስዋዕትነት ጀምሮ የተለያዩ ጥረቶች ስታደርግ መቆየቷን ገልጸው፤ የብዙ ሃገሮች ፍላጎትም በአከባቢው ኢትዮጵያን ያመከለ  የጸጥታ መዋቅር እንዲኖር መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪ ኢትዮጵያ ያልተሳተፈችበት በጎ ነገር ሁሉ “ታጥቦ ጭቃ” ይሆናል የሚል አስተሳሰብ በብዙ ሃገራት እንዳለ ገልጸዋል።

በተጨማሪ በሶማሊያ ከድህረ አትሚስ (በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ) በኋላ የሚመጣው ሃይል የኢትዮጵያ እንዲሁም የቀጠናው የጸጥታ ስጋት መሆን እንደሌለበት አክለዋል።

ኢትዮጵያ፤ የሶማሊያ መንግሥት የጸጥታ ሃይሉን ሙሉ በሙሉ መያዝ እስከሚችል ድረስ ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥልም ገልጸዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ሆኖም ግን ከአከባቢያችን “ሰላም ከማይፈልጉ አካላት ጋር የሚደረገው እንቅስቃሴ ዝም ተብሎ የሚታለፍ አይደለም” ሲሉ አበክረዋል።

ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር የተፈጠረው አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተለያዩ ምክክሮች በኬንያ ናይሮቢና በቱርክ አንካራ መካሄዳቸው የተገለጸ ሲሆን እነዚህ ውይይቶችም “ተጨባጭ ውጤት” ማምጣታቸውን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ በኩል አሁንም የንግግር በሮች አለመዘጋታቸውንም አስታውቀዋል።

ይሁን እንጂ፤ “አንዳንድ የሶማሊያ ተወካዮች ልዩነት ማስፋት የአዘቦት ተግባራቸው አድርገውታል።” ያሉት ሚኒስትሩ አክለውም፤ የኢትዮጵያ ሰራዊት የከፈለውን መስዋዕትነት ማጣጣል አግባብ አለመሆኑንም አንስተዋል።

የባሕር በር ጥያቄ “ለኢትዮጵያ የህልውና ጥያቄ” መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ አክለውም ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥል ተናግረዋል።አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button