ቢዝነስዜና
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: ኢትዮጵያ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ፖሊሲ ተግባራዊ አደረገች፣ የኑሮ ውድነት ሊከሰት እንደሚችል የጠቆመው መንግስት የደመወዝ ጭማሪ አደርጋለሁ ብሏል

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22/2016 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከዛሬ ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ስርዓት ማሻሻያ ማድረጉን አስታወቀ።

ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረገው የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያ ከሚያስከትላቸው አበይት አዳዲስ የፖሊሲ ለውጦች መካከል የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓቱ የውጭ ምንዛሪ ተመን በባንኮችና በደንበኞቻቸው መካከል ወደሚወስንበት የገበያ ሥርዓት ይሸጋገራል ብሏል፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሚና፣ ገበያውን በማረጋጋት ላይ ያተኮረ እንደሚሆን ጠቁሟል።

አሁን በሥራ ካሉና በባንኮች ከተቋቋሙ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች (Forex Bureaus) በተጨማሪ ባንክ ያልሆኑ የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች እንደሚቋቋሙ ያስታወቀው ባንኩ  ለእነዚህ ባንክ ላልሆኑ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎችም በገበያ ዋጋ የውጭ ምንዛሪ ጥሬ ገንዘብ እንዲገዙና እንዲሸጡ የሥራ ፈቃድ እንደሚሰጣቸውም ጠቁሟል።

የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ስርዓት ማሻሻያው በህብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ ጫና እንደሚያሳድር ያመላከተው መንግስት ጫናውን ለማቃለል የተለያዩ እርምጃዎችን ለመውሰድ ማቀዱን አስታውቋል።

ከዘራዘራቸው እርምጃዎች መካከል ለመንግሥት ሠራተኞች የኑሮ ውድነት መደጎሚያ ደሞዝ እንደሚጨምር ያመላከተበት ይገኛል።  መንግስት “ያለውን የገንዘብ ምንጭ በመጠቀምና የመንግሥትን የበጀት ጉድለት በማያባብስ መልኩ ለመንግሥት ሠራተኞች የኑሮ ውደነት መደጎሚያ ደሞዝ ለመጨመር” አስቢያለሁ ብሏል።

በተጨማሪ እወስዳቸዋለሁ ብሎ ከጠቀሳቸው እርምጃዎች መካከል የአንዳንድ መሠረታዊ ሸቀጦችን ዋጋ በጊዜያዊነት ለመደጎም መወሰኑን የጠቆመበት ይገኛል።

ይደጎማሉ ብሎ ከዘረዘራቸው መካከልም ነዳጅን፣ ማዳበሪያን፣ መድኃኒትና የምግብ ዘይትን የመሳሳሉት ይገኙበታል ብሏል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

እንዲሁም፣ በከተማም ሆነ በገጠር ለሚገኙ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ አነስተኛ ገቢ ላላቸው ቤተሰቦች የሚደረገው የሴፍቲኔት እርዳታ በከፍተኛ ደረጃ እንዲያድግ መደረጉን አስታውቋል።

መንግሥት የውጭ ዕዳ ማቅለያ እርዳታ ማግኘቱን የጠቆመው የቢሔራዊ ባንክ መግለጫ ከዓለም የገንዘብ ድርጅት፣ ከዓለም ባንክና ከአበዳሪዎች የሚገኘውን ጨምሮ “የሽግግር ወቅት ወጪዎችንና የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያ የሚያስከትላቸውን ጫናዎች ለመቀነስ የሚረዳ 10.7 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ትልቅ የገንዘብ ድጋፍ ከውጭ አጋሮች ተገኝቷል ብሏል።

መንግስት ከዛሬ ሐምሌ 22 ቀን ጀምሮ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረጉን ተከትሎ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአሜሪካ ዶላር መግዣ እና መሸጫ ዋጋ ላይ የ17 ብር ጭማሪ ማድረጉን አስታውቋል። አንድ የአሜሪካ ዶላር ባለፈው ሳምንት አርብ ሲሸጥ ከነበረበት 58.63 ብር ወደ 76.23 ብር ከፍ ያለ ሲሆን መግዣው ደግሞ በሳምንቱ መጨረሻ ከ57.48 ብር የነበረው የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ ወደ 74.73 ከፍ ብሏል።

ማንግስት ያካሄደውን የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ስርዓት ማሻሻያን ተከትሎ አስተያየታቸውን ካሰፈሩ መካከል በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካን ኤምባሲ ይገኝበታል፤ ኤምባሲው በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጹ “ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ አስቸጋሪ ነው፣ ነገር ግን የኢትዮጵያን የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ለማስተካከል ወሳኝ እርምጃ ነው፤ መንግስትን እናበረታታለን፣ ከሌሎች የልማት አጋሮች ጋር በመሆን የኢትዮጵያን ህዝብ ለመደገፍ እና ወደ ተሻለ ነፃ እና ጠንካራ ኢኮኖሚ እድገት የሚያሸጋግሩ ማሻሻያዎችን እንዲተገብሩ እናበረታታለን” የሚል መልዕክት አጋርቷል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button