ህግ እና ፍትህርዕሰ አንቀፅ
በመታየት ላይ ያለ

ርዕሰ አንቀጽ፡ ከህግ አግባብ ውጭ በኦነግ አመራሮች ላይ የተፈጸመው እስር በኢትዮጵያ የፍትህ ስርዓት ላይ አደጋ ነው  

አዲስ አበባ ሐምሌ 26/ 2016 ዓ/ም፦ በቅርቡ ጥቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከተለያዩ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ጋር ያደረጉት ውይይትን የመንግስት ሚዲያዎች ዘግበዋል። በተለመደው ሁኔታ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚመራው ገዥው ፓርቲ እና በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች እና ተወካዮች መካከል የሚደረግ እንደዚህ ያሉ ውይይቶች፤ የጋራ መፍትሄዎችን የሚጠይቁ ውስብስብ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ለመፍታት አስፈላጊ ናቸው።  ነገር ግን በቁልፍ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ላይ የህግ እና ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመባቸው ባለበት ወቅት የተካሄደው ይህ ውይይት ውጤታማ ነው ማለት አይቻልም። 

በውይይቱ ካልተሳተፉት የፓርቲ መሪዎች መካከል በዋናነት የኦሮሞ ነፃናት ግንባር (ኦነግ) አመራሮች ናቸው። አመራሮቹ ለአራት ዓመታት ከህግ አግባብ ውጭ መታሰራቸው በኢትዮጵያ የፍትህ ስርዓት እያሽቆለቆለ መምጣቱን የሚያሳይ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በተደጋጋሚ በሚገኙባቸው የተቃዋሚ መሪዎች ውይይት ላይ ሲያነሱት የሚሰማው ዴሞክራሲና ፍትህን ወደ ኋላ መመለሱን አመላካችም ነው።

በማንኛውም ዴሞክራሲያዊ ማህበረሰብ ውስጥ የህግ የበላይነት ቅድሚያ የሚሰጠው አስፈላጊ ጉዳይ ነው። ፍትህ የተገነባበት እና ፍትሃዊነት የሚሰፍንበት ጠንካራ መሰረትም ነው። የፍትህ አካላት ውሳኔዎች ችላ ከተባሉ የዴሞክራሲ መርሆች ይዳከማል። ይህ ሁኔታ በኢትዮጵያ ያለ ሲሆን የኦነግ ሰባት አመራሮች በተደጋጋሚ እንዲፈቱ በፍርድ ቤት ውሳኔ ቢሰጥም አሁንም በእስር ላይ መቆየታቸው ከፍተኛ የህግ የበላይነት ጥሰት ነው።

ኦነግ፤ በተለያዩ ፍርድ ቤቶች ከፍተኛ የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ አባላቶች እንዲፈቱ የሚሰጡ ተደጋጋሚ ትዕዛዞችን በመጣስ በፀጥታ ኃይሎች ተይዘው እንዲቆዩ መደረጋቸውን እንዲሁም ጥቃት እየደረሰባቸው መሆኑን ለለፉት አራት አመታት በላይ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሲገልጽና መፍትሄ ሲጥይቅ ቆይቷል። ፓርቲው አመራሮቹ በቀድሞው ፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን  በአሁኑ ስያሜው ሸገር ከተማ አስተዳደር በሚገኙ በተለያዩ የማቆያ ማዕከላት ውስጥ ያጋጠሟቸውን አስከፊ ሁኔታዎች በየካቲት 2014 በዝርዝር አስታውቋል። አመራሮቹ ከህግ አግባብ ውጭ ለረጅም ጊዜ መታሰራቸውን በመቃወም የረሃብ አድማ በማድረግ ለጤና እክል ተዳርገዋል። ቤተሰቦቻቸውም እንዳይጠይቋቸው ተከልክለዋል።

በመንግስት ተይዘው ያሉ ግለሰቦች የሚገኙበትን ቦታና ያለበትን ሁኔታ ለመግለጽ ፈቃደኛ አለመሆን በግዳጅ መሰወር በመሆኑ የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ህግን በከባድ ሁኔታ የሚጥስ እና በዓለም አቀፍ የወንጀል ህግ መሠረት ወንጀል ነው

ሚካኤል ቦረን፣ ኬኔሳ አያና፣ ዳዊት አብደታ፣ ለሚ ቤኛ እና ገዳ ገቢሳን ጨምሮ የኦነግ ከፍተኛ አመራሮች በኦሮሚያ ክልል ሞጆ፣ አዋሽ መልካሳ፣ ገላን፣ ሰበታ እና ቡራዩን ጨምሮ በርካታ መደበኛ ባልሆኑ ማቆያ ማዕከላት ውስጥ ታስረው ቆይተዋል። “የተወሰኑ አባሎቻችን ገላን ከተማ በሚገኘው ሶሎሊያ በተባለ የኦሮሚያ ልዩ ሃይል ካምፕ ውስጥ ለብቻቸው ተለይተው ታስረው ይገኛሉ። አብዛኛዎቹ በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሲሆን ቤተሰብ እንዳይጠይቃቸው ተደርጓል” ሲሉ ከሁለት ዓመት በፊት የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ለዚህ ህትመት ገልጸዋል። 

በዚያኑ አመት ግንቦት ወር መንግስታዊው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባወጣው ሪፖርት፤ የፓርቲው መሪዎች እና አባላት “ከሕግ አግባብ ውጪ መታሰራችውን” ባደረገው ክትትል ማረጋገጡን አስታውቋል። ኢሰመኮ ሁሉም እስረኞች በአስቸኳይ እንዲለቀቁ፣ የኦሮሚያ ክልል መንግስት በእስረኞች ላይ ድብደባ የፈጸሙ የጸጥታ አባሎችና ኃላፊዎች ላይ ምርመራ እንዲያደርግና ተጠያቂ እንዲደረጉ ጠይቋል። ተገቢ ባልሆነ አያያዝ በእስረኞች ላይ ለደረሰው ጉዳትም ካሳ እንዲከፈላቸው ኢሰመኮ አሳስቧል፡፡

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የቀድሞ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “የፍርድ ቤትና የዐቃቤ ሕግ ውሳኔዎች በተደጋጋሚ እየተጣሰ እስረኞቹ ከሕግ ውጪ ለተራዘመ እስር መዳረጋቸው ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም ስለሆነ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት አፋጣኝ ማጣራት አካሂዶ ተገቢውን እርምጃ ሊወሰድበት ይገባል” ብለዋል፡፡

በቀጣይ ወር ሰኔ አለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት ሂዩማን ራይትስ ዎች፤ መንግስት በፖለቲካ ሚናቸው ምክንያት በዘፈቀድ ዕስር ላይ የሚገኙት ሰባት የኦነግ ከፍተኛ አመራሮች በአስቸኳይ እንዲለቅ ጥሪ አቅርቧል።  

ሂዩማን ራይትስ ዎች በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ ግለሰቦች የሚገኝበትንና ያለበትን ሁኔታ ለመግለጽ ፈቃደኛ አለመሆን በግዳጅ መሰወር መሆኑና የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ህግን በከባድ ሁኔታ የሚጥስ እና በዓለም አቀፍ የወንጀል ህግ መሠረት ወንጀል መሆኑን አስጠንቅቋል።

ፖሊስ ስራ አስፈፃሚዎቹን ከእስር እንዲፈታ በፍርድ ቤት በተደጋጋሚ የሚሰጠውን ትዕዛዝ ተፈጻሚ አለማድረጉ የህግ ችግር ብቻ ሳይሆን አፋጣኝ መፍትሄ የሚሻውን የፍትህ ስርዓትን አለማክበር ጭምር ነው። 

ይሁን እንጂ፤ የኦነግ አመራሮች የፀጥታ አካላት እስረኞች ሆነው ቀጥለዋል።

የፖለቲከኞቹ ፈተና በ2012 ሐምሌ ወር የጀመረ ሲሆን በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በነፃ እንዲለቀቁ የተላለፈውን ውሳኔ አቃቤ ህግ ይግባኝ በማለቱ ውድቅ መደረጉን ተከትሎ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎትን ጨምሮ በተለያዩ ችሎቶች ጉዳያቸው ተዳኝቷል። 

ይህ እትም በፌዴራል ፍርድ ቤት በተደጋጋሚ በዋሉት ችሎቶች፤ ሁሉም እስረኞች እንዲለቀቁ የተላለፉትን ትዕዛዛት ሲዘግብ ቆይቷል። ፖሊስ ስራ አስፈፃሚዎቹን ከእስር እንዲፈታ በፍርድ ቤት በተደጋጋሚ የሚሰጠውን ትዕዛዝ ተፈጻሚ አለማድረጉ ህግ መጣስ ብቻ ሳይሆን አፋጣኝ መፍትሄ የሚሻና የፍትህ ስርዓትን አለማክበር ጭምር ነው። ይህ ሁኔታ በሰብአዊ መብቶች መከበር እና የፍትህ አካላት ገለልተኝነት ላይ ከፍተኛ ስጋት ይፈጥራል።

በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተከታዮች ያሉት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር፤ ለረጅም አመታት የኢትዮጵያ ውስብስብ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ አንዱ አካል ሆኖ የቆየ የፖለቲካ ድርጅት ነው። ድርጅቱ መንግስትን አደጋ ላይ ለመጣል በአመፅ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ይሳተፋል በሚል ክስ የሚቅርብበት ሲሆን አመራሮች ለተራዘመ የህግ ሂደት ተዳርገዋል። ምንም እንኳ በትጥቅ እንቅስቃሴ ላይ እየተሳተፉ ባይሆንም አመራሮቹ ለእስር ሲዳረጉ የፓርቲው መሪ ዳውድ ኢብሳ ለሁለት ዓመታት ያህል የቁም እስረኛ ሆነው እንዲቆዩ ተደርገዋል። ይህም የሆነው ፓርቲው ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለማድረግ ከትጥቅ ትግል ራሱን ካገለለ በኋላ ነው።

በፍርድ ቤት በተወሰነው ውሳኔ መሰረት የኦነግ አመራሮች ከእስር መፈታት ከፍተኛ የሆነ ኢፍትሃዊነትን ከማስተካከል ባለፈ ኢትዮጵያ ለዲሞክራሲያዊ መርሆዎችና ለህግ የበላይነት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያጠናክር ነው። በተጨማሪም በሕገ መንግሥቱ የተከለለ የፖለቲካ ምህዳር እንዲኖር አስተዋጽኦ ያደርጋል። 

የፓርቲው ስራ አስፈጻሚዎች እንዲፈቱ ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሳኔ በማስረጃዎችና በሕግ መርሆዎች ላይ ተመስርተው ነው። እነዚህን ትዕዛዛት አለማክበር በአጠቃላይ የፍትህ ሂደቶች ላይ ተጽዕኖ ይፈጥራል፤ ይህም ከህግ መርሆዎች ይልቅ ፖለቲካዊ ምክንያቶች እንዳሉ ይጠቁማል። በተጨማሪም የዜጎችን መብት የሚጠብቁ ተቋማዊ ማዕቀፎችን በማዳከም ያለመቀጣት ባህልን ያስፋፋል።

የፌዴራል መንግስቱ ይህን ጉዳይ በአስቸኳይ መፍታት አለበት። ዳኝነት መከበር አለበት፤ ውሳኔም ያለ አድሎና ማራዘም ተፈጻሚ መሆን አለበት። በፍርድ ቤት በተወሰነው ውሳኔ መሰረት የኦነግ አመራሮች ከእስር መፈታት ከፍተኛ የሆነ ኢፍትሃዊነትን ከማስተካከል ባለፈ ኢትዮጵያ ለዲሞክራሲያዊ መርሆዎችና ለህግ የበላይነት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያጠናክር ነው። በተጨማሪም በሕገ መንግሥቱ የተከለለ የፖለቲካ ምህዳር እንዲኖር አስተዋጽኦ ያደርጋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button