ማህበራዊ ጉዳይዜና

ዜና፡ ከቀናት እንቅስቃሴ መቋረጥ በኋላ ባህርዳር ከተማ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ ተመለሰች

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 13/ 2016 ዓ/ም፦ የአማራ ክልል መዲና ባህርዳር ከቀናት የንግድ ሱቆች መዘጋት እና የትራንስፖርት እንቅስቃሴ መቋረጥ በኋላ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴዋ መመለሷን ነዋሪዎች ገለጹ። 

ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ የከተማው ነዋሪ ትላንት ምሽት በከተማዋ የተኩስ ድምጽ መሰማቱን ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጿል። ነገር ግን ዛሬ ትራንስፖርት አገልግሎቶች በመጀመሩን እና ሱቆች በመከፈታቸው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ዳግም ጀምረዋል ሲል ተናግሯል። 

“ዛሬ ጠዋት ላይ የተወሰኑ ሱቆች ብቻ የተከፈቱ ሲሆን ባለሶስት እጅር ተሽከርካሪዎች በብቸኝነት እየንቀሳቀሱ ያሉ ተሽከርካሪዎች ናቸው። ይሁን እንጂ ከሰዓት በኋላ መደበኛ የትራንስፖርት አገልግሎቶችና እንቅስቃሴዎች ቀጥለዋል” ሲሉ ነዋሪው ተናግሯል።

በከተማዋ የአድማ ጥሪ መደረጉን ተከትሎ በተፈጠረ የጸጥታ ስጋት ከአርብ ጀምሮ በርካታ እንቅስቃሴዎች መቋረጣቸውን ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል። 

ባሳለፍነው ሳምንት በከተማዋ ተከታታይ የቦንብ ፍንዳታዎች መፈጸማቸውን ነዋሪዎች አስረድተዋል። በቀበሌ 4፣ በቀበሌ 14 እንዲሁም አባይ ማዶን ጨምሮ በከተማዋ ልዩ ልዩ ስፍራዎች የቦንብ ጥቃቶች መፈጸማቸውን አረጋግጠዋል

የአማራ ክልል ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ  ባወጣው መግለጫ ለድርጊቶቹ የ”ጎጃም ፋኖ” ያለውን አካል ተጠያቂ አድርጓል።

መንግሥት እና ሕዝብ ክልሉ ያጋጠመውን የሰላም እጦት እና ግጭት በሰላም እና በድርድር ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ባሉበት ሁኔታ እራሱን የ”ጎጃም ፋኖ” በሚል የሚጠራው ታጣቂ ቡድን ያስተላለፈውን የአድማ ጥሪ ተከትሎ በክልሉ ትራንስፖርትን ጨምሮ የሥራ እንቅስቃሴ መቆሙን ገልጿል። በባሕር ዳር ከተማ ከሰሞኑን ተከታታይ ፍንዳታዎች መከሰታቸውንም ገልጿል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን  ህዝቡ “የጸጥታ ሃይሉ ቁመና በአስተማማኝ ሁኔታ ላይ ስለሚገኝ” የቀደመውን ሰላማዊ እንቅስቃሴ እና መስተጋብር እንዲቀጥል አሳስቧል።

በየካቲት ወር በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በከባድ መሳሪያ የታገዘ  ግጭት መካሄዱን አዲስ ስታንዳርድ መዘገቡ ይታወሳል። በተለይ ዳያስፖራ በሚባል ሰፈር የከባድ መሳሪያ ተኩስ ልውውጥ ተካሄዶ ነበር።  

ይህን ተከትሎም በከተማዋ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እና የባንክ አገልግሎት ተቋርጦ እንደነበር ነዋሪዎች ተናግረዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button