ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: ከኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ጋር ግንኙነት አላችሁ በሚል በሻሸመኔ ከ15 በላይ ተማሪዎች ለወራት ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በእስር ላይ እንደሚገኙ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18/2016 ዓ.ም፡- ከኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ጋር ግንኙነት አላችሁ በሚል ከ15 በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች በኦሮምያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን በሻሸመኔ ከተማ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ለሁለት ወራት ያህል ክስ ሳይመሰረትባቸው እና ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በእስር ላይ እንደሚገኙ ተገለጸ።

ምንጮች ለአዲስ ስታንዳርድ አስታወቁት በእስር ላይ ከሚገኙት ተማሪዎች አብዘሃኛዎቹ ከኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን የመጡ ናቸው።

ከታሰሩ ተማሪዎች መካከል በሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ሻሸመኔ ካምፓስ የአካውንቲንግ ትምህርት በመከታተል ላይ የነበረ አንዱ ጓደኛው እንደሚገኝ የተናገረው ኩኒ ዲዳ (ስሙ ለደህንነት ሲባል ተቀይሯል) ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለጸው፤ በአሁኑ ጊዜ በሻሸመኔ ፖሊስ ጣቢያ በተለምዶ 81 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ መታሰራቸውን ጠቁሟል።

ከተያዙት ተማሪዎች መካከልም በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን በሻሸመኔ ከተማ በሚገኘው ፓራዳይዝ ኮሌጅ እና በመሳሰሉት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመማር ላይ የሚገኙ ሌሎች ተማሪዎች እንደሚገኙበት ምንጩ አክሎ ገልጿል።

በተጨማሪም በሻሸመኔ በኩል ወደ ቦረና ዞን ሲጓዝ የነበረ አንድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ከታሰሩት መካከል እንደሚገኝ ምንጩ ገልጿል።

“የታሰሩት አብዛኞቹ ተማሪዎች በሻሸመኔ ከተማ ነዋሪ ናቸው” ሲል የገለጸው ምንጩ አክሎም ተማሪዎቹ በተለያዩ ጊዜያት ተይዘው የነበሩ መሆናቸውንና አንዳንዶቹ ለሁለት ወራት ያህል መታሰራቸውን አስታውቋል።

ከታሰሩት ተማሪዎች መካከል ያዕቆብ ጎዳና፣ ጉራቻ አባ ጉዶ፣ ኩል ኬናሳ፣ ቱሉ ናማ ዱሪ፣ ሃልቃኖ ጅርማ፣ ዋቆ ድንጌ፣ ቃኑ ጅርሞ፣ አባዮ ጋልማ ሃላቄ፣ ላሚ ባቻ እና አባዱባ ኩሊ ጂሎ ይገኙበታል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የሻሸመኔ ከተማ ፖሊስ ተማሪዎቹን እንዲታሰሩ ያደረገው የቦረና ዞን ፖሊስ መምሪያ ከኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት (“ሸኔ”) ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ጥቆማ በማድረሱ መሰረት ነው ሲሉ ምንጮች ለአዲስ ስታንዳርድ ባደረሱት መረጃ አስታውቀዋል።

አክለውም በቅርቡ በኬንያ ድንበር ላይ በሚገኘው በቦረና ዞን ቢሎ ወረዳ በተከሰተው ግጭት ፖሊስ ለኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት መረጃ አቅርባችሗል ሲል ተማሪዎቹን እንደከሰሳቸው ጠቁሟል።

ከተማሪዎቹ መካከል አንዳቸውም ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡ እና ቤተሰቦቻቸው ከታሰሩበት ጊዜ ጀምሮ ከእነሱ ጋር መገናኘት አለመቻላቸውንም ለአዲስ ስታንዳርድ መረጃውን ያደረሱ አስታውቀዋል።

ከታሳሪዎቹ ተማሪዎች መካከል ላሚ ባጫ የተባለ ወንድሙ እንደሚገኝበት የነገረን ፊራኦል ባቻ “ወንድሜ ላሚ በሻሻማኔ የሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ካምፓስ የሁለተኛ ዓመት የኮምፒውተር ሳይንስ ተማሪ ነበር” ሲል ገልጿል፤ አክሎም ወንድሙ ቢታሰርም እስከአሁን ፍርድ ቤት አለመቅረቡን አስታውቋል።

ፊራኦል በመቀጠልም ላሚ ከመታሰሩ በፊት “ፖሊስ በማስፈራራት በቲክ ቶክ ላይ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ካላቆመ ለእስር እንደሚዳርግ አስጠንቅቆት ነበር” ሲሉ ጠቁሟል።

“የቲክቶክ አካውንት እንኳን የሌለው የላሚ ጓደኛም አብሮ ተይዟል” ሲሉ ሁኔታውን አስረድተዋል።

በሻሸመኔ የሚገኘው የአካባቢው ፖሊስ ከቦረና ዞን ለመጡ ወላጆቹ ምርመራ እየተደረገ መሆኑንና ማስረጃ እየተሰበሰበ መሆኑን እንደነገሯቸው ፊራኦል ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጿል።

“ነገር ግን ካለፈው አርብ ጀምሮ በፖሊስ የቀረበ ምንም አይነት ማስረጃ የለም” ያሉት ፊራኦል አክለውም ጉዳዩን ለማጣራት ኃላፊነት ያለው ኮሚቴ እስካለፈው ሳምንት ድረስ አለመሰብሰቡን ተናግረዋል::

ካሊቻ ጅርማ የተባለ ሌላኛው የታሳሪ ሃልቃኖ ጅርማ ወንድም እንደተናገሩት ወንድማቸው በሰኔ ወር 2016 ዓ.ም ታስሮ እንደነበርና በአሁኑ ሰአት በሻሸመኔ ፖሊስ ጣቢያ እንደሚገኝ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።

አክለውም ሃልቃኖ በሻሸመኔ በሚገኘው የሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በሰርቬይንግ የጥናት መስክ ትምህርቱን ሲከታተል እንደነበር ገልጸዋል።

“የታሰረበትን ምክንያት ምንም አናውቅም፣ ፖሊስ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ብቻ ይገልፃል፤ ነገር ግን እስከ ትናንት ድረስ ፍርድ ቤት አልቀረበም ነበር” ሲሉ ካሊቻ ተናግረዋል።

አዲስ ስታንዳርድ ከሻሸመኔ ከተማ እና ከምዕራብ አርሲ ዞን ባለስልጣናት አስተያየት ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።

በኦሮሚያ ክልል ለስድስት ዓመታት የዘለቀውን በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት እና በመንግስት ሃይሎች መካከል የሚደረገውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ በክልሉ በዘፈቀደ እየታሰሩ የሚገኙ ሰዎች እየጨመሩ መጥተዋል።

በቅርቡ የወጣው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሪፖርት በኢትዮጵያ በ2015 ዓ.ም. በተለይም በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ያለውን አሳሳቢ የሰብአዊ መብት ሁኔታ አጉልቶ አሳይቷል። የዘፈቀደ እስር፣ የዜጎች ግድያ፣ ማሰቃየት፣ በግዳጅ መሰወር እና በሲቪል ንብረት ላይ ጥቃት መሰንዘር ከሰብዓዊ መብት ጥሰቶቹ መካከል ይገኙበታል። ሪፖርቱ በኦሮሚያ ክልል በመንግስት ታጣቂዎች እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መካከል በተፈጠረው ግጭት 366 ንፁሀን ዜጎች መሞታቸውን የገለፀ ሲሆን ከተገደሉት መካከል 46ቱ ሴቶች ናቸው ተብሏል:: አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button