ማህበራዊ ጉዳይዕለታዊፍሬዜናዜና

ዕለታዊ ዜና፡ በአማራ ክልል ተጠልለው የነበሩ ሱዳናውያን ስደተኞች ወደ አገራቸው ለመመለስ የአግር ጉዞ መጀመራቸው ተነገረ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 7/ 2016 ዓ/ም፦ በአማራ ክልል፤ በምዕራብ_ጎንደር ዞን በሚገኙ የአውላላ እና ኩመር መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ተጠልለው የነበሩ 800 የሱዳን ስደተኞች በጸጥታ ችግር ምክንያት ወደ አገራቸው ለመመለስ ጉዞ መጀመራቸው ተነገረ።

ስደተኞቹ ከዚህ ቀደም ለሶስት ወራት ያህል በጸጥታ ችግር እና በአገልግሎት እጥረት ምክንያት ከመጠለያ ጣቢያዎቹ ወጥተው ኑሯቸውን በጎዳና ዳር አድርገው እንደነበር የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ለአሜሪካ ድምጽ ገልጸዋል።

ኮሚሽነሩ  ባለፈው ሳምንት ዐርብ  800 የሚሆኑ ስደተኞቹ በእግር ወደ አገራቸው ሱዳን ለመመለስ እና አልፎም አጎራባች ወደሆኑ አገራት ለመሄድ ጉዞ መጀመራቸው ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ (UNHCR) በሱዳን ካለው ቀውስ የተነሳ እንዲህ አይነቱን ጉዞ እንደማይደግፈው ገልፆ ስደተኞቹ ወደ አዲሱ አፍጥጥ የመጠለያ ጣቢያ እንዲገቡ እንደሚያበረታታ መግለጹን የአሜሪካ ድምጽ ዘግቧል

በሐምሌ 13/2016 ዓ/ም በአውላላ የሥደተኞች መጠለያ ጣቢያ አከባቢ ሰፍረው በነበሩ ስደተኞች ላይ በተፈፀመ ጥቃት የሁለት ሱዳናውያን ስደተኞች ህይወት ማለፉንና 10 ስደተኞች መቁሰላቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

በተጨማሪም ሐምሌ 11/2016 ዓ.ም በአማራ ክልል በሱዳናውያን መጠለያ ካምፕ አቅራቢያ በመንግስት የፀጥታ ሀይሎች እና በታጣቂዎች መካከል በተደረገ ውጊያ ዘጠኝ የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች መገደላቸውንና ስደተኞች መጎዳታቸውን ዘግበናል።

በአከባቢው በተፈጠረው ከፍተኛ የፀጥታ ስጋት ምክንያት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ድርጅት በአማራ ክልል የስደተኞች ካምፕ ላይ ተጠልለው የሚገኙ ሱዳናውያንን ስደተኞችን ወደ ሌላ ቦታ ለማዛወር እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ኢትዮጵያ ከ1.1 ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን እንዳስጠለለች የሚታወቀ ሲሆን በአቅርቦት ውስንነት ምክንያት እንደ ኩመር እና አውላላ ባሉ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ለስደተኞች የሚሰጠው አገልግሎት ላይ ተግዳሮት ማጋጠሙ ይታወሳል።

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button