ማህበራዊ ጉዳይዜና

ዜና፡ በሶስተኛ ወገን ቅጥር ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲሰሩ የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ሊሰናበቱ መሆኑን ተናገሩ

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 23/ 2016 ዓ/ም፦ በመላ አገሪቱ በሚገኙ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች በሎቢ እና ፋይል ኦፕሬተር የስራ መደቦች ሲሰሩ የነበሩ በሺህዎች የሚቆጠሩ የኮሜርሻል ኖሚኒስ ሠራተኞች ሊሰናበቱ መሆኑን ለአዲስ ስታንዳርድ ተናገሩ።

ሠራተኞቹ ከነሐሴ 25 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ የሥራ ውላቸው እንደሚቋረጥ ከኮሜርሻል ኖሚኒስ ኃ/ የተ/ ግ/ ማ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እንደሰጣቸው ገልጸዋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ በኮሜርሻል ኖሚኒስ ተቀጥረው ለንግድ ባንክ የሚሰሩ ሰራተኛ፤ “ለአራት ዓመታት ያህል በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሎቢ የስራ ዘርፍ አገልግያለሁ፤ ከወር በፊት የስራ ውላችን እንደሚቋረጥ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ደርሶናል። የሚሆነውን እየተጠባበቅን እንገኛለን።” ብለዋል።

ለባንኩ ሠራተኞችን በሚያቀርበው (አዉትሶርስ) ኮሜርሻል ኖሚኒስ ድርጅት የተቀጠሩት ሠራተኞች ባንኩ “ፋይል ኦፕሬተሮችና ሎቢዎች አያስፈልገንም በራሴ ሰራተኞች አሰራለሁ፤” በሚል ምክንያት በስራ መደቡ የሚሰሩ ሰራተኞች ውላቸው ሊቋረጥ መሆኑን ሠራተኛው ገልጸዋል።

አያይዘውም “ባንኩ ቀጥታ በወር ዘጠኝ ሺህ ብር ቢከፍለንም እጃችን ላይ ተቆርጦ የሚደርሰን አራት ሺህ ብር ነው።” ያሉት የባንኩ ሠራተኛ አክለውም የባንኩ አብዛኛው ስራ ግን እነሱ ላይ መውደቁን ገልጸዋል።

ለአዲስ ስታንዳርድ ቃላቸውን የሰጡ ሌላኛዋ ሰራተኛ ይህን አረጋግጠዋል።

“ታርጌት ይሰጠናል፤ በርካታ የስራ ሃላፊነቶች እኛ ላይ ነው የወደቀው ነገር ግን እጃችን ላይ የሚደርሰን ደመወዝ እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም:: አሁን ደግሞ ጭራሽ ይህንንም ስራችንን ልናጣ ነው።” ሲሉ ሁኔታውን አስረድተዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

አክለውም “በርካታ ዛቻዎች እና የመብት ጥሰቶች” ሲፈጸሙባቸው እንደቆዩ ገልጸው፤ “አሁን ላይ እንደ እቃ ተጠቅመው እንደጣሉን ነው የምንቆጥረው” ሲሉ ሠራተኛዋ ገልጸዋል።

የኮሜርሻል ኖሚኒስ የሠራተኛ ማኅበር ምክትል ሰብሳቢ አቶ ባዘዘው አጥላ፤ ተቋሙ “ከስራቸው የሚሰናበቱ ሰራተኞች ቁጥር 2500 ነው ቢልም ቁጥራቸው በመላ ሃገሪቱ እስከ 7000 ሊደርሱ እንደሚችሉ” ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።

አክለውም በተቋሙ እስከ አስር ዓመት የሰሩ ሰራተኞች እንዳሉ ገልጸው፤ “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እና የሞራል ካሣ ሰራተኞችን አውጥቶ መጣል እጅግ አሳዛኝ ክስተት ነው” ሲሉ ቅሬታ አቅርበዋል።

በተጨማሪ ለሰራተኞቹ የስራ ማፈላለጊያ እና የሞራል ካሣን በተመለከተ ማህበሩ እየጠየቀ መሆኑን የተናገሩት የሠራተኛ ማህበሩ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ባዘዘው አጥላ፤ አክለውም ተቋሙ ከ5ዓመት በላይ ለሆናቸው ሰራተኞች ብቻ ካሣ እከፍላለሁ ማለቱን ገልጸዋል።

በጉዳዩ ላይ መግባባት የማይደረስ ከሆነና ለሁሉም ሰራተኞች ጥያቄ አግባብነት ያለው መልስ ካልተሰጠ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ እንደሚገደዱ ገልጸዋል።

የኮሜርሻል ኖሚኒስ የሠራተኛ ማኅበር ፕሬዝዳንት አቶ ባህሩ መለሰ በበኩላቸው የሰራተኞችን መሰናበት ያረጋገጡ ሲሆን ከሁለቱ የስራ መደቦች ላይ ከሚሰሩ ሰራተኞች በተጨማሪ ወደፊት በሌሎች ዘርፎች የሚሰሩ ሰራተኞች ላይ ስጋት እንዳለ ተናግረዋል።

“ሰራተኛው እንኳን ከስራው ተፈናቅሎ ይቅርና እንደዚሁም ራሱን ማስተዳደር አልቻለም።” ያሉት ፕሬዝዳንቱ አክለውም ጉዳዩ አሳሳቢ በመሆኑ የመንግስት አካል እና የሚመለከተው ሁሉ ርብርብ እንዲያደርግ አሳስበዋል።

አዲስ ስታንዳርድ ስለ ጉዳዩ ከኮሜርሻል ኖሚኒስ አስተያየት ለማግኘት ባደረገው ጥረት ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ ድርጅቱ ባለመሆኑ ማካተት አልተቻለም።

ነገር ግን በሠራተኞቹ ቅሬታ ላይ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጠው ምላሽ “የባንኩ ሁለት የሥራ መደቦች በመታጠፋቸው፣ በቦታው ተመድበው ሲሠሩ የነበሩ 2ሺሕ 500 ሠራተኞች የሥራ ውላቸው ይቋረጣል፤” ብሏል፡፡ እነዚኽን ሠራተኞች ወደ ሌሎች ደንበኞች ለማዛወር እየሠራ መኾኑንም አስታወቋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button