ማህበራዊ ጉዳይዜና

ዜና፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በጊዜያዊ መጠለያ የነበሩ የሱዳን ስደተኞች ወደ ቋሚ መጠለያ ጣቢያ እየተዛወሩ መኾናቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 16/ 2016 ዓ/ም፦ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ በኩርሙክ ጊዜያዊ መጠለያዎች የነበሩ በቁጥር 22ሺሕ የሚደርሱ ሱዳናውያን ስደተኞች፣ በዚያው ክልል ውስጥ ወደተዘጋጀ የኡራ ቋሚ መጠለያ እየተዛወሩ መኾናቸውን፣ የኢትዮጵያ የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት አስታውቋል።

በአገልግሎት ተቋሙ የአሶሳ ቅንርጫፍ ጽሕፈት ቤት ሓላፊ የሆኑትን አቶ ያሲን አሸናፊ ጠቅሶ የአሜሪካ ድምጽ እንደዘገበው ስደተኞቹ የነበሩበት የኩርሙክ ጊዜያዊ ማቆያ ስፍራ፣ ዓለም አቀፍ መስፈርትን ስለማያሟላ ዐዲሱ የኡራ መጠለያ ጣቢያ መዘጋጀቱ ተጠቁሟል።

“ዓለም አቀፍ ህጉ ስደተኞች ከድንበር ቢያንስ 50ኪ.ሜ ርቀው መስፈር አለባቸው ይላል::” ያሉት ሃላፊው አክለውም በክልሉ የሚገኘው የኩርሙክ መጠለያ ለድንበር የቀረበ በመሆኑ ስደተኞቹን ወደ ሌላ መጠለያ ማዘዋወር ማስፈለጉን ገልጸዋል።

አክለውም እስከ አሁን ድረስ አራት ሺሕ ስደተኞች ወደ ዐዲሱ መጠለያ መግባታቸውን የገለጹ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ 18ሺሕ ስደተኞችም በ10 ቀናት ውስጥ ወደ መጠለያው ይጓጓዛሉ ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአማራ ክልል በምዕራብ ጎንደር ዞን በሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎች ከ6000 በላይ ሱዳናውያን ስደተኞችን ያስጠለለች ሲሆን፤ የሱዳን ጦርነት ከተቀሰቀሰ አንስቶ ከ58ሺህ በላይ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቄዎች ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን የአሜሪካ ድምጽ ዘግቧል።

ከዚህ ቀደም በአማራ ክልል፤ በምዕራብ ጎንደር ዞን በሚገኙ የአውላላ እና ኩመር መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ተጠልለው የነበሩ 800 የሱዳን ስደተኞች በጸጥታ ችግር ምክንያት ወደ አገራቸው ለመመለስ ጉዞ መጀመራቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

በኢትዮጵያ ከ1.1 ሚሊዮን በላይ ስደተኞች ተጠልለው እንደሚገኙ ይታወቃል። አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button