ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ አብን የህወሓት ታጣቂዎች በራያ ወረዳወችና በአላማጣ “የንጹሃን ግድያና ዝርፊያ መፈጸማቸውን" ገለጸ፤ ህወሓት "በሰብአዊ መብት ጥሰት" ተጠያቂ እንዲሆን ጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19/ 2016 ዓ/ም፦ አማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) “የህወሓት ታጣቂዎች በራያ ወረዳወችና በአላማጣ ከተማና ዙሪያውን የሚገኙ አካባቢዎችን በንፁሃን የአማራ ተወላጆች ላይ ግድያ ፈጽመዋል፣ በብዙ አስር ሽህ የሚቆጠሩ ወገኖችን እፈናቅለዋል” ሲል ከሰሰ። 

አብን ዛሬ ግንቦት 19 / 2016 በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ባወጣው መግለጫ፤ “ታጣቂዎቹ ከፍተኛ መጠን ያለው የህዝብ ሃብትና ንብረት እንደዘረፉና እንዳወደሙ፣ በገጠር ቀበሌወች የአርሶ አደሩን እህል ጭነው እንዳጓጓዙ ተረጋግጧል” ብሏል።

“ህወሓት ሰፊ ወታደራዊ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቶ ከቀናት በፊት በአፋር አካባቢዎች እና ባሳለፍነው ሳምንንተ መጨረሻ በአለማጣ ከተማ ላይ የወረራ ጥቃት በመክፈት ነዋሪዎችን እየገደለ፣ ንብረታቸውን እየዘረፈ እና እያፈናቀለ ይገኛል” ሲል አብን በመግለጫው ገልጿል።   

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ኃይሎች በአላማጣ ከተማ አቅራቢያ ከሚገኙ “ገርጃሌ” እና “በቅሎ ማነቂያ” ከተባሉ መንደሮች ለቀው መውጣታቸውን አስታውቀዋል።

አቶ ጌታቸው አርብ ዕለት በማህበራዊ ሚዲያ ኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት እንዳስታወቁት የትግራይ ሀይሎች ከመንደሮቹ ለቀው እንዲወጡ የተደረገው ከፌደራል መንግስቱ እና ከአማራ ክልል መንግስት ጋር የተደረሰውን መግባባት በማክበር ነው።

በተጨማሪም ከአከባቢው ተፈናቅለው የነበሩ የትግራይ ተወላጆችን ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ለማስቻል ሁኔታዎችን ለማመቻችት መሆኑን ገልጸዋል።

አማራ ብሄራዊ ንቅናቄ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ “ታጣቂዎቻቸው መውጣታቸውን ያሳወቁት በአለማጣ ከተማ ህዝብ ላይ ጥቃት መክፈታቸውን ለማወጅ ነበር” ሲል ገልጿል። 

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

“መንግስት ጥቃቱን ለማስቆም ምንም አይነት ተጨባጭ ርምጃ አልወሰደም” ያለው ድርጅቱ፤ “በራያ አካባቢወች በህዝብ ላይ እየደረሰ ላለው ግድያ፣ መጠነ ሰፊ መፈናቀል፣ ውድመትና ዘረፋ መንግስት በዝምታ ያየው በመሆኑ፣ በህወሓት አመራሮች የሚደረግ የ”መንግስት ፈቅዶልን” ፕሮፓጋንዳ ዙሪያ ምንም ባለማለቱ ለሚጠፋው ሁሉ ተጠያቂ ይሆናል” ብሏል።

በተጨማሪም “የክልሉ መንግስት በችግሩ ዙሪያ ላለው የግልፅነት ጉድለትና በማህበረሰቡ ላይ ለሚደረሰው ያልተቋረጠ ጥቃት ሃላፊነት የሚወስደ መሆኑ መዘንጋት የለበትም” ሲል ገልጿል።

“በአማራ ህዝብ ስም እታገላለሁ የሚሉ በርካታ ሀይሎች በዚህ ቀጠና ያለው የአማራ ህዝብ ለተደጋጋሚ ጥቃት ሲዳረግ እንዳይነገር መፈለጋቸው በህወሓት ተፅእኖ ስር እንደወደቁ ማረጋገጫ ነው” ሲልም አክሏል። 

አብን በመግለጫው አለማቀፉ የዲፕሎማቲክ ማህብረሰብ “በህወሓት አማካኝነች በህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ሁለንተናዊ ሰብዓዊ ቀውስ እልባት እንዲያገኝ እና ህወሀት ለፈፀመው የሰብአዊ መብት ጥሰት ተጠያቂ እንዲሆን ኃላፊነቱን እንዲወጣ” ጠይቋል። 

“የፌዴራል መንግስት የህወሓት ታጣቂዎችን በወረራ ከያዟቸው አካባቢዎች ባስቸኳይ ለቀው እንዲወጡ እንዲያደርግ እና በተደጋጋሚ ወረራ እየተፈጸመበት ለከፍተኛ ችግር ለተጋለጠው ህዝብ አፋጣኝ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያደርግም” ጥሪ አቅርቧል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button