ማህበራዊ ጉዳይዜና
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ “አይናችን እያየ ነው የአፈር ናዳው ያንን ሁሉ ህዝብ የበላው፤ ሁኔታው በጣም አስከፊ ነው” የገዜ ጎፋ ወረዳ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17/ 2016 ዓ/ም፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ ሰኞ ሐምሌ 15/ 2016 ዓ/ም በተከሰተው የመሬት ናዳ የሟቾች ቁጥር እያሻቀበ እንደሚገኝና ሁኔታው እጅግ አስከፊ መሆኑን ተገለጸ:: 

የገዜ ጎፋ ወረዳ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ የዓለም መርህነህ ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረጉት ቆይታ ክስተቱን “በጣም አስከፊ እና ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ ከባድ ነው” ሲሉ ገልፀውታል::

መጀመሪያ የተከሰተውን የአፈር ናዳ አደጋ ሰምተው ከኮሚዩኒኬሽን ባለሙያዎች ጋር ወደ ስፍራው ማምራታቸውን የገለጹት ኃላፊው፤ በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ለማገዝ የተሰበሰቡ በርካታ ሰዎች ላይ ዳግም የአፈር ናዳ መከሰቱን ገልጸዋል። 

“እኛ አጋጣሚ ከሚዲያ እና ኮሚኒኬሽን ባለሙያዎቻችን ጋራ ካሜራ ይዘን ነበር ከአከባቢው ትንሽ ራቅ ከሚል ስፍራ የነበርነው:: ወዲያው ወደ 3፡40 አካባቢ ከባድ ድምጽ ተፈጠረ:: ከባድ የሚለውም ቃል አይገልፀውም፤ አይናችን እያየ ነው አፈሩ ያንን ሁሉ ህዝብ የበላው:: የወረዳው አስተዳዳሪ እና ምክትል አስተዳዳሪ እንዲሁም የወረዳው የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ ከህዝቡ ጋር አብረው የነበሩ ሲሆን አደጋው በተፈጠረ ቅጽበት ቀድሞው አደጋ ወደ ደረሰበት እና ወደ ተናደው ስፍራ በመዝለል ህይወታቸው ሊተርፍ ችሏል::” ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ክስተቱን አስረድተዋል::

አክለውም ከህዝቡ ጋራ አብረው ሲያግዙ የነበሩ አንድ የቀበሌ ሊቀመንበር እንዲሁም የፀጥታ አካል አሰቃቂ በሆነው አደጋ ህይወታቸው ሊያልፍ ችሏል ሲሉ ገልጸዋል::

በትላንትናው አደጋ የሟቾች ቁጥር እየጨመረ እንደሚገኝ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ በወረዳው የኮምኒኬሽን ቢሮ የሚሰሩ አንድ ባለሙያ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል:: “አሃዛዊ መረጃው እኛ ከተናገርነው ውጪ እየጨመረ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው:: እስከ ዛሬ ጠዋት ድረስ የ237 ሰዎች አስከሬን ተገኝቷል” ያሉት ባለሙያው አክለው አሁንም የጠፉ ሰዎች ስላሉ የአስከሬን ማውጣቱ ስራ እንደቀጠለ ነው ሲሉ ገልጸዋል::

የኮሚኒኬሽን ባለሙያው ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገጹት የመንገዱ ምቹ አለመሆን በእርዳታ አሰጣጡ ላይ እክል ፈጥሮ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ግን ክልሉ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ማሽነሪዎች ገብተው የመንገድ ጠረጋ እና የጠጠር ማንጠፍ ስራ እየተከናወነ ነው ሲሉ ተናግረዋል::

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ትላንት ከፌደራል የመጡ ሥስት የቀይ መስቀል መኪኖች እህል እና አልባሳት ወደ ስፍራው አጓጉዘው ነበር ያሉት ባለሙያው አክለውም አጎራቦች ከሆኑ አከባቢዎች እርዳታዎች እየተደረጉ እንደሆነ ገልጸዋል::

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን በደረሰው አደጋ 400 የሚሆኑ ዜጎች መፈናቀላቸውን የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ዛሬ ለመገናኛ ብዙሀን በሰጡት መግለጫ ገልጸዋል:: ኮሚሽነሩ ጉዳት ለደረሰባቸውና ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚያስፈልጋቸውን ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ማስታወቃቸውን መዘገባችን ይታወሳል::

በተከሰተው አደጋ በርካታ አካላት ሃዘናቸውን እየገለጹ የሚገኝ ሲሆን የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ “በደረሰው አስከፊ ጉዳት የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን እገልጻለሁ። አደጋውን ተከትሎ የፌዴራል የአደጋ መከላከል ግብረ-ሀይል በአካባቢው ተሰማርቶ የአደጋውን ጉዳት ለመቀነስ ርብርብ እያደረገ ነው” ሲሉ ገልፀዋል::

በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ በበኩሉ “ከ200 በላይ ሰዎችን ህይወት በቀጠፈው የመሬት መደርመስ አደጋ እጅግ አዝነናል።” ሲል በማህበራዊ ትስስር ገጹ ላይ ባሰፈረው መልዕክት አስታውቋል:: ኤምባሲው አክሎም የአሜሪካ መንግስት በዩኤስ ኤ አይ ዲ በኩል  ካሉ የሰብአዊ እርዳታ አጋሮች ጋር ግንኙነት በማድረግ ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን አስታውቋል::

የተለያዩ የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በስፍራው በመገኘት ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች አጽናኑ ይገኛሉ። በአደጋው የተጎዱ ዜጎችን ለማገዝ በማህበራዊ ሚዲያ ገንዘብ ማሰባሰብ እንቅስቃሴ በስፋት እየተከናወነ የሚገኝ ሲሆን በርካታ ወገኖችም ለችግሩ ልዩ ልዩ ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆናቸው ተገልጿል::አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button