ማህበራዊ ጉዳይዜና
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ ኢትዮጵያ በረሃብ ተጠቂ ከሆኑ ሀገራት ተርታ ተካተተች፤ 13 ሚሊዮን ዜጎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ይሻሉ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ12/ 2016 ዓ/ም፦ የተባበሩት መንግስታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት እና የአለም የምግብ ፕሮግራም (FAO-WFP) አዲስ ባወጡት ሪፖርት፤ ኢትዮጵያ ከተወሰኑ የአፍሪካ አገራት ጋር፤ በዓለም ላይ በረሃብ ተጠቂ ከሆኑ ሀገራት ተርታ ተካተተች።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በግጭት፣ በድርቅ፣ በከፍተኛ የኑሮ ውድነት እና በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት በተከሰተ ከፍተኛ የምግብ ችግር ውስጥ እንደምትገኝ ሪፖርቱ ገልጿል።

በኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ጦርነት እና ድርቅ ባስከተለው ረሃብ ከሐምሌ 2016 እስከ መስከረም 2017፤ 13 ሚሊዮን ሰዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ሪፖርቱ አመላክቷል።

ከእነዚህም መካከል ወደ አራት ሚሊዮን የሚጠጉት በዋናነት በሶማሌ፣ በትግራይ እና በኦሮሚያ ክልሎች የሚገኙ ተፈናቃዮች መሆናቸው ተገልጿል::

ሪፖርቱ አክሎም ከአምስት አመት በታች የሆኑ ህጻናት እና ነፍሰ ጡር በሆኑ እንዲሁም ጡት በሚያጠቡ ሴቶች ላይ ከፍተኛ የሆነ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት መከሰቱን አመልክቷል።

የዓለም አቀፉ የምግብ ተቋም በሪፖርቱ ችግሩ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የምግብ እጥረቱ እንዳይባባስ ለመከላከል ተጨማሪ እርዳታ እንደሚያስፈልግ በአጽንኦት ገልጿል።

ከየካቲት እስከ ግንቦት 2016ዓ.ም መካከል ባለው የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ የሆኑ ክልሎች የተሻለ የምግብ አቅርቦት ሊኖራቸው ቢችልም፣ በመኸር ሰብሎች ላይ የተመሰረቱ አካባቢዎች ግን ከሰኔ እስከ መስከረም ባለው ጊዜ ውስጥ የምግብ አቅርቦት እየቀነሰ እንደሚሄድ ይጠበቃል ተብሏል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ሪፖርቱ በዚህ ወቅት ውስጥ ተጨማሪ እርዳታ ካልተደረገ በተለይ ሰሜናዊ የአገሪቱ አከባቢዎች ውስጥ የበለጠ ከባድ ሁኔታዎች ሊከሰቱ ይችላሉ ሲል አስጠንቅቋል።

የአየር ሁኔታ ትንበያዎች፤ ከሰኔ እስከ መስከረም ድረስ ከመደበኛ እስከ ከፍተኛ ዝናብ እንደሚኖሩ ቢጠቁሙም በኋላ ግን በዓመቱ ውስጥ ሊኖሩ የሚችሉ የላኒና ክስተቶች ከአማካይ በታች የሆነ ዝናብ ሊያስከትሉ ይችላሉ የተባለ ሲሆን  ይህም የእንስሳትን ምርት ሊጎዳ እንደሚችል ተገልጿል።

መሠረታዊ የምግብ ሸቀጦች በአጠቃላይ በገበያ ላይ የሚገኙ ቢሆንም፣ የዋጋ ንረቱ ግን የቤተሰብን የምግብ አቅርቦት መገደብ መቀጠሉንም ሪፖርቱ አመልክቷል። የምግብ የዋጋ ግሽበት 22.7 በመቶ የደረሰ ሲሆን አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት በሰኔ 2016 ዓ/ም 19.9 በመቶ ደርሷል:: ይህም ምግብ በመግዛት ላይ የተመሰረቱ አባወራዎችን የመግዛት አቅም እንደሚቀንስ ነው የተነገረው።

ይህ የምግብ እና የእርሻ ድርጅት እና የአለም የምግብ ፕሮግራም ሪፖርት፤ ከዚህ ቀደም ፊውስ ኔት  የሰራውን ግምገማ ተከትሎ የወጣ ነው።

በታህሳስ 2015፣ ፊውስ ኔት አንዳንድ የትግራይ እና የሰሜን ምስራቅ አማራ ክፍሎች ከሰኔ እስከ መስከረም 2016 ዓ/ም የምግብ ዋስትና እጦት እንደሚገጥማቸው እና አብዛኛዎቹ አካባቢዎች በቀውስ ውስጥ ሊሆኑ ይችላሉ ሲል ተንብዮ ነበር።

ተቋሙ በ2024 አጋማሽ ድረስ በአምስት የኢትዮጵያ ክልሎች፤ አራት ሚሊዮን ሰዎች ለከፍተኛ የረሃብ አደጋ እንደሚጋለጡ የገለጸ ሲሆን ክልሎችም የጉዳዩን ክብደት ሪፖርት ማድረጋቸው ይታወሳል::

ለአብነትም በታህሳስ 2015፣ የትግራይ ባለስልጣናት በአንድ ወር ውስጥ 25 ህፃናትን ጨምሮ ወደ 400 የሚጠጉ ሰዎች በአራት ወረዳዎች በረሃብ ምክንያት መሞታቸውን አስታውቀዋል።

በህዳር 2015 ዓ.ም የአማራ ክልል ባለስልጣናት በበኩላቸው  በዋግ ኽምራ እና ሰሜን ጎንደር ዞኖች በረሃብ ምክንያት ከ20 በላይ ሰዎች መሞታቸውን እና ከ85,000 በላይ ከብቶች መሞታቸውን መግለፃቸው ይታወሳል::አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button