ዜናፖለቲካ

ዜና፡ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ በአማራ ክልል የአካባቢያዊ የስልጣን ሽኩቻ ማስፈጸሚያነት እና ለቂም በቀል መወጣጫነት እየዋለ ነው ሲል አብን ተቸ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 12/2016 .ም፡ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ከታወጀበት መንፈስ እና ከሰላም አላማ ውጭ ለመጠቃቃት እየዋለ ነው ሲል ባወጣው መግለጫ ተችቷል። በተለይ በአማራ ክልል ውስጥ የአካባቢያዊ የስልጣ ሽኩቻን ማስፈጸሚያነት እና ለቂም በቀል መወጫነት ውሏል ሲል ገልጿል።

በአዲስ አበባ እና ኦሮምያ ክልል ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ አማራ ጠል የሆኑ አክራሪ ሲል የገለጻቸው በጸጥታና በህግ ተቋማት የሚሰሩ ሰወች አዋጁን ተገን አድርገው በንጹሀን ላይ ሰፊ ጥቃት እየፈጽሙ ነው ያለው አብን ሰወችን በማስፈራራት ገንዘብ መቀበል እና መሠል ችግሮች በስፋት መስተዋላቸውን ጠቁሟል።

ሀገሪቱ ባስቸኳይ ጊዜ ዋጅ የህግ ሥርዐት እና አስተዳደር ሥር ትገኛለች ብሏል። በአማራ ክልል የተከሰተውን የጸጥታ ችግር ተከትሎ የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መጠነ ሰፊ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች እና የሲቪሊያን እስር የተስተዋለበት መሆኑን ያስታወቀው አብን የሰብአዊ መብት አያያዝ መርሆችን የጣሱ ድርጊቶች እየተፈጸሙ ስለመሆኑ በርካታ ጥቅማዎችን መቀበሉን አመላክቷል።

ከእስር በተጨማሪ በጸጥታ አካላት አማካይነት አካላዊ ድብደባዎች፣ በቁጥጥር ውስጥ በዋሉ ግለሰቦች ላይ ግብታዊ እርምጃ መውሰድ፣ ውድ ንብረቶችን መቀማት፣ ማንገላታትና የመከልከል ድርጊቶች መፈጸማቸውን አስታውቋል።

አብን በመግለጫው በአፋጣኝ ተግባራዊ እንዲደርጉ በመፍትሔነት ካቀረባቸው ሀሳቦች መካከልም የሚጠቀስ የወንጀል ተሳትፎ ሳይኖራቸው በብሔራቸው ተመርጠው የታሰሩ፣ በግል ቂም፣ በፖለቲካ ልዩነት እና ለጥቅም ማስፈጸሚያነት ሲባል በየቦታው የታሰሩ ዜጎች ጉዳይ ተመርምሮ በፍጥነት መለቅቅ አለባቸው የሚለው ይገኝበታል።

በተጨማሪም በጦርነት ውስጥ ለሚገኙት የአማራ ክልል አካባቢዎች አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደረግ ጠይቋል፤ የተፈፀሙት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኛ አካል እንዲመረመሩ አሳስቧል።

መንግስት ከወታደራዊ አማራጭ በመውጣት ለዘላቂ ሰላም መደላድል የሚፈጥሩ የውይይት፣ የንግግር እና በምክክር ላይ የተመሰረተ የሰላምና የአካታች የሲቪክ አስተዳደር ምስረታ ጥረት መደረግ አለበት ሲል ጠይቋል። አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button