ማህበራዊ ጉዳይዜና
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ የኤርትራ ክስ የኢትዮጵያን አየር መንገድ ስም የማጥፋት ሥራ በመሆኑ ክሱ ተቀባይነት የለውም_  አቶ መስፍን ጣሰው

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23/ 2016 ዓ/ም፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ ከኤርትራ ሲቪል አቬሽን ባለሥልጣን የቀረበበትን ክስ “የአየር መንገዱን ስም የማጥፋት ሥራ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም” ሲል ውድቅ አደረገ።

በኤርትራ የትራንስፖርት እና ኮሚዩኒኬሽን ሚኒስቴር የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ሐምሌ 17 ባወጣው መግለጫ፡ “በኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ ስልታዊና በተቀናጀ መንገድ የተጓዦች ሻንጣዎች ላይ ስርቆት መፈጸምና መዘግየት፣ ዘረፋና የበረራዎች ሰዓት መዘግየት እንዲሁም ካሳ አለመስጠት” እየተፈጸመ ነው ሲል ከሷል

በተጨማሪም የበረራ ትኬት ዋጋ ላይ ተገቢ ያልሆነ ጭማሪ የሚደረግ መሆኑን ጠቅሷል።  በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ችግሮቹ እንዲቀረፉ በተደጋጋሚ ጥሪ ቢደረግም ፌሬ ማፍራት ባለመቻሉ ወደ አስመራ የሚደረገውን በረራ ማገዱን መግለጫው ገልጿል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸምን አስመልክተው ትናንት በሰጡት መግለጫ፣ የኤርትራ ሲቪል አቬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከመስከረም 30 ጀምሮ እንዳይበር የሚል ደብዳቤ መላኩን አስረጋግጠው፤ ደብዳቤው ይህንን አጥፍታችኋል የሚል ምንም ዓይነት ማብራሪያ አልነበረውም ብለዋል።

ነገር ግን በቀጣይ ቀን በማህበራዊ ሚዲያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትክክለኛ ያልሆነ አሠራር በመከተሉ፣ የሚጠይቀው የትኬት ዋጋ በመወደዱ፣ የመንገደኞች ሻንጣ የሚጠፋ፣ የሚሰበርና የሚሰረቅ በመሆኑ አግደነዋል እና ጉዟችሁን አስተካክሉ የሚል መግለጫ አውጥቷል ሲሉ ገልጸዋል።

አቶ መስፍን ጣሰው በረራ አቪየሽኑ መቋረጡ ሳያንስ የኢትዮጵያን አየር መንገድ “ስም የማጥፋት ሥራ የሠራ በመሆኑ ክሱ በፍጹም ተቀባይነት የለውም” ብለዋል። 

አክለውም ከዚህ በፊት የኤርትራ ሲቪል አቬሽን ከ737 አውሮፕላን ውጪ ከፍ ያለ የመንገደኞች ማመላለሻ እንዳንጠቀም እግድ ጥሎብን ነበር ሲሉ ገልጸው በተጨማሪም በሳምንት ከ10 በረራ ውጪ እንዳናደርግ ተደርጎ ነበር።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

መጋቢት ወር ውስጥ የኤርትራ ሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣን ለኢትዮጵያ አየር መንገድ የመንገደኞች ሻንጣ የሚያጉላላ በመሆኑ ለደንበኞቹ ካሳ እንድንከፍል በጻፈልን ደብዳቤ መሠረት ወዲያውኑ የማስተካከያ ርምጃ ወስደናል ብለዋል።

በወሰድነው ርምጃም መንገደኞች ከሻንጣቸው ጋር እኩል እንዲሄዱ እና በየአውሮፕላኑ ያለውን የተሳፋሪ ቁጥር በመቀነስ ችግሩ ተፈትቷል። ይህ እንደመወንጀያ መደረጉ ተገቢነት የለውም ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስህተቶችን ለማረም ዝግጁ በመሆኑ በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል ጤናማ ግንኙነት፣ ንግድና ቱሪዝም እንዲኖር የሚጥር ተቋም በመሆኑ በረራው እንዳይቋረጥ የኤርትራ የሚመለከታቸው ባለሥልጣናትን ለማነጋገር ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ አየር መንገድ በህይወት ያሉ “ለላብራቶሪ አገልግሎት የሚውሉ እንደ ጦጣ ያሉ እንሰሳትን ወደ አሜሪካ ያጓጉዛል” በሚል ከእንስሳት ተቆርቋሪ ተቋም ለሚነሳበት ቅሬታ የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው “ይህ ዓለም አቀፍ አሰራር ስለሆነ፤ ህጋዊ ፈቃድ የተሰጠው ከአሜሪካም ከሌላም ሀገር ህጋዊ ፈቃድ የተሰጠው ድርጅት እስከመጣ ድረስ ያንን የዓለም አቀፍ ህጉን ተከትለን እናጓጉዛለን” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል። 

አየር መንገዱ “ወታደሮችን ያጓጉዛል” በሚል ለሚነሳትበት ሌላኛው ቅሬታ፤ አቶ መስፍን ጣሰው” ወታደሮች በአውሮፕላኖች የሚሄዱበት አሰራር አለ፤ በዚህ ረገድ አየር መንገዱ ዓለሞ አቀፍ አሰራሮችን ጠብቆ ነው የሚሰራው” ብለዋል።

አየር መንገዱ ሁለት አውሮፕላኖችን መድቦ ለየተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ብቻ ያጓጉዛል። በተለይ አንደኛው አውሮፕላን ለዚሁ ግልጋሎት ብቻ የተመደበ ነው ሲሆን ሁለተኛው ተጨማሪ ሲያስፈልግ አገልግሎት ይሰጣል ሲሉ ተናግረዋል። 

“ሰላም አስከባሪ ወታደሮችን ከሀገር አገር አጓጉዘናል፣ የአፍሪካ ጸጥታ አስከባሪ ወታደሮችን ስናጓጉዝ ነው የኖርነው፤ እናጓጉዛለን፤ ያ ማለት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጦርነት ላይ ተሳተፈ ማለት አይደለም። በዚህም አየር መንገዱ ገቢ እያገኘበት ነው” ብለዋል።

“ወታደሩ ምን ያደርጋል የሚለው የእኛ ኃላፊነት አይደለም” ያሉት አቶ ጣሰው፤ ከዚህ በፊት “ወታደሮች ስለምታጓጉዙ አውሮፕላኖችን ፋይናንስ አናደርግላችሁም ተብለን እናውቃለን እኛ አሰራራችንን አስረድተን፤ አሰራራችን ከዓለም አቀፉ አሰራር ጋር አብሮ የሚሄድ መሆኑን ካረጋገጡ በኋላ አውሮፕላኖቻችንን እንድናመጣ አድርገውናል” በማለት አስረድተዋል። አስ 

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button