ማህበራዊ ጉዳይዜና
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በኬንያ 'እገታ፣ ዘረፋ፣ ማዕድን የማውጣትና ማዘዋወር' ተግባራት እየፈጸመ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 16/ 2016 ዓ/ም፦ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በኬንያና ድንበር አካባቢ “ዜጎችን የማገት፤ ንብረት የመዝረፍ የማውደምና ህገወጥ ማዕድን የማውጣትና ማዘዋወር” ተግባራት እየፈጸመ መሆኑን እና ከሶማሊያው “አልሸባብ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው” የኢትዮጵያ እና የኬኒያ የመረጃ ተቋማት አስታወቁ። 

በዳይሬክተር ጄነራል ኑረዲን መሐመድ ሀጂ የተመራው የኬኒያ የመረጃ አገልግሎት የልዑካን ቡድን ለስራ ጉብኝት አዲስ አበባ የሚገኝ ሲሆን በትላንትናው ዕለት ከብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ተወያይተዋል።

ተቋማቱ በውውይታቸው እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን በኢትዮጵያ እና በኬንያ ድንበር እና በኬኒያ ውስጥ “ዜጎችን የማገት፤ ንብረት የመዝረፍ የማውደምና እንዲሁም የሰዎችን እንቅስቃሴ የማስተጓጎል” ስራዎች እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

ቡድኑ በሶማሊያ ከሚንቀሳቀሰው “የአልሸባብ የሽብር ቡድን ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያለው መሆኑን” የገለጸው የብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፤ በቅርቡ ሁለት የኮሪያ ዜጎችን በማገት ለአልሸባብ አሳልፎ መስጠቱን አክሎ አስታውቋል።

በተጨማሪም ቡድኑ “የኮንትሮባንድ ንግድ፤ ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር፤ ህገወጥ የማዕድን ማውጣትና ማዘዋወር” ስራዎች ላይ መሰማራቱንና ይህንንም ለማስቆም የኢትዮጵያ እና የኬኒያ የመረጃ ተቋማት አፋጣኝ እርምጃ ለመውሰድ አቅጣጫ ማስቀመጣቸው ተጠቁሟል፡

“ሁለቱ የሽብር ቡድኖች” በአካባቢው እና በቀጣናው የደቀኑትን የሽብር ስጋት በጋራ ለመከላከልና ለመቀልበስ ይረዳ ዘንድ የተቀናጀ ኦፐሬሽን አጠናክረው ለመቀጠል መወሰናቸውን  የአገልግሎት መስሪያ ቤቱ መረጃ አመልክቷል፡፡

የሁለቱ ሀገራት አቻ የመረጃ ተቋማት የሳይበር ጥቃትን በጋራ ለመከላከል እንዲሁም የሀገራት አሁናዊ ስጋት እየሆነ ያለውን የስነ ልቦና ጦርነትንም ለመከላከል እና መልሶ ለማጥቃት በሚደረግ ጥረት በጋራ ለመስራት መስማማታቸው ተመልክቷል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በሱዳን ያለው ጦርነት እና አለመረጋጋትም በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታና ሱዳን ወደ ቀድሞ ሰላማዊ እንቅስቃሴዋ እንድትመለስ በጋራ እንደሚሰሩም ገልጸዋል ተብሏል።

ተቋማቱ ከዚህ በፊት በመረጃ ልውውጥ እና በሌሎች የፀጥታና ደኅንነት ጉዳዮች ዙሪያ በትብብር ለመስራት የጋር መግባቢያ ሰነድ ተፈራርመው ወደ ስራ መግባታቸውን እና በትብብራቸው መሰረትም የተቋማቱ የስራ ሀላፊዎቸና ባለሙያዎች በተደጋጋሚ እየተገናኙ ሲገመግሙ መቆየታቸውን የብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መረጃ አመላክቷል፡፡አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button