ዜና
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መገናኛዎችን መጥለፍ የሚፈቅድ ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ

አዲስ አበባ ሰኔ 5/ 2016 ዓ/ም፦ በወንጀል የተገኘ ንብረትን ሕጋዊ ከማስመሰል ወይም ሽብርተኝነትን በገንዘብ ከመርዳት ወንጀል ጋር በተያያዘ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መገናኛዎችን እና ደብዳቤዎች ለመጥለፍ ለመርማሪዎች ፈቃድ የሚሰጥ ረቂቅ አዋጅ ለተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ።

ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ረቂቅ አዋጅ መርማሪ አካል “አስቸኳይ ሁኔታ ካጋጠመው” የሚመለከተውን የዐቃቤ ሕግ ተቋም የበላይ ኃላፊ በማስፈቀድ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ የመገናኛ እና የደብዳቤ ልውውጦችን መጥለፍ ይችላል።

አዲሱ ረቂቅ በሥራ ላይ ያለውን በወንጀል የተገኘ ንብረት ሕጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ የሚሽር መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል

መገናኛዎችን እና የደብዳቤ ልውውጦችን መጥለፍ፣ በባንክ ሂሳቦች እና በሌሎች ተመሳሳይ ሂሳቦች ላይ ክትትል ማድረግ፣ የኮምፒውተር ሥርዓቶችን፣ መረቦችን ሰርቨሮችን መለየትና በሽፋን ስር የሚደረግ ምርመራ ከወንጀሎቹ ጋር በተያያዘ ተግባራዊ ከሚደረጉ በአዋጁ የተጠቀሰ  የምርመራ ዘዴዎች መካከል ናቸው።

በረቂቅ አዋጁ መሰረት  በዐቃቤ ሕግ ፍቃድ ያገኘ መርማሪ አካል ጠለፋውን ለማካሄድ የሚጠየቅ የመገናኛ የአገልግሎት አቅራቢ፤ “ጠለፋው በፍርድ ቤት ወይም በዐቃቤ ሕግ የበላይ ኃላፊ የተፈቀደ መሆኑን በማረጋገጥ” ትብብር የማድረግ ግዴታ ተጥሎበታል።

በሥራ ላይ ያለው አዋጅ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በዐቃቤ ሕግ ይሁንታ ብቻ የምርመራ ዘዴዎችን ማከናወን ለመርማሪ አካል አይፈቅድም።

በወንጀል የተገኘ ንብረትን ሕጋዊ ከማስመሰል ተቀጽላ ወንጀሎች ጋር በተያያዘ ይጣል የነበረው ከ5 እስከ 10 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ ተሻሽሎ ከ100 እስከ 500 ሺህ ብር የሚያስቀጣ ሆኗል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በዚሁ ወንጀል ጥፋተኛ የሚባል ግለሰብ ላይ ይጣል የነበረው የእስር ቅጣት ግን ከዚህ በፊት በነበረበት ከ10 እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንዲቀጥል ተደርጓል።

ሽብርተኝነት በገንዘብ መርዳት ወንጀልም ተመሳሳይ የገንዘብ እና የእስራት መቀጮ የሚጣልበት ሆኖ ተሻሽሏል። የእስራት ቅጣቱ ግን ምንም ዓይነት ማሻሻያ ሳይደረግበት ከሦስት እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ እስራት ሆኖ ቀጥሏል።

ረቂቅ አዋጁ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ወደ ሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር ዕይታ ከተመራ በኋላ ለምክር ቤቱ ቀርቦ ተግባራዊ እንዲሆን ይጸድቃል።አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button