ዜናፖለቲካ

ዜና: ህወሓት የፕሪቶርያውን የሰላም ስምምነት እንደማልደግፍ ተደርጎ ስም ማጥፋት እየተካሄደብኝ ነው ሲል ገለጸ  

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1/2016 ዓ.ም፡- “የፕሪቶርያውን የሰላም ስምምነት እንደማልደግፍ ተደርጎ በመነገር ላይ ያለው ሀሳብ ሀሰት ነው፣ ስም ማጥፋት ነው” ሲሉ ህወሓት ገለጸ።

በህወሓት እና በፌደራል መንግስቱ መካከል በፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት በተፈረመበት ወቅት ህወሓትን በመወከል ተደራዳሪ የነበሩት እና በደብረጺዮን ገ/ሚካኤል በሚመራው የህወሓት ቡድን ውስጥ ስራ አስፈጻሚ የሆኑት ፍስሃ ሃፍተፅዮን (ዶ/ር) ለክልሉ መገናኛ ብዙሃን ትላንት ነሃሴ 30 ቀን 2016 ዓ.ም ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ስራ አስፈጻሚው በጋዜጣዊ መግለጫቸው በዋናነት ያጠነጠኑት በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት አፈጻጸም እና በህወሓት ውስጥ ስለተፈጠረው ክፍፍል ዙሪያ ማብራሪያ አቅርበዋል።

ህወሓት “የፕሪቶርያው ስምምነት እንዲተገበር፣ በተለይም የትግራይ ግዛታዊ አንድነት እንዲከበር፣ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ማድረግ፣ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ማድረግን በተመለከተ ጽኑ እምነትና አቋም አለው” ሲሉ መግለጻቸውን ከትግራይ ቴሌቪዥን ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

ፓርቲያቸው የስም ማጥፋት የተደረገበት በማን መሆኑን ግን የገለጹት ነገር የለም።

የፕሪቶርያው ስምምነት በተፈረመበት ወቅት “ትግራይን ወክለው በተሳተፉ ተወካዮች መካከል ከፍተኛ ልዩነት” እንደነበረ ያወሱት ስራ አስፈጻሚው “በወቅቱ ሁሉም ተስማምቶ ስምምነቱ መፈረሙ አንድ ጸጋ ሲሆን ቀሪ ጉድለቶችን ደግሞ በሂደት እንሞላቸዋለን የሚል እምነት ነበረን” ብለዋል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አንድ አመት ከአምት ወራት ቢያስቆጥርም በማቋቋሚያ ሰነዱ መሰረት የጊዜያዊ አስተዳደሩ የቆይታ እድሜ ቢያንስ ስድስት ወራት ቢበዛ አንድ አመት እንደሚሆን መቀመጡ ሊታወስ ይገባል ብለዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

 “በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ማቋቋምን በተመለከተ በፕሪቶርያው ስምምነት የመጀመሪያ ሰነዶች ውስጥ አልነበረም፣ በኋላ ላይ በሂደት ነው የተካተተው፣ በወቅቱ ለምን ብለን ሞግተናል” ሲሉ ገልጸዋል። “የጊዜያዊ አስተዳደሩ እድሜም ከስድስት ወር እስከ አንድ አመት ጊዜ ብቻ” መሆኑን አውስተዋል።

ዶ/ር ፍስሃ በማብራሪያቸው “በትግራይ በጊዜያዊነት ስልጣን የተቆጣጠረው አካል ለትግራይ ዘላቂ ጥቅም የሚሆን በዲሞክራሲያዊ ፉክክር ህዝባዊ መንግስት ለማቋቋም ነበር መታገል የሚገባው” ሲሉ ገልጸው “አሁን እያየነው ያለነው ግን መቸ የስልጣን እድሜው እንደሚያበቃ አይታወቅም፣ አትጠይቁን የሚል ነው” ሲሉ ተችተዋል፤ “ህወሓትን የሚያክል ፖለቲካ ፓርቲ አያገባውም እያሉ ነው” ብለዋል።

“በዚህ አይነት አካሄድ መጓዝ አይቻልም” ያሉት ስራ አስፈጻሚው “የህወሓት ዋነኛ ትኩረት የፕሪቶርያውን የሰላም ስምምነት አስፈጽሞ ህዝቡን የዲሞክራሲ እና የልማት ተጠቃሚ ማድረግ ነው” ሲሉ አስታውቀዋል።

“የጊዜያዊ አስተዳደሩ ሰራው ተብሎ በሚነገረው ስራ ውስጥ ህወሓት አለ፤ በተፈጠረው ልዩነት እና ብልሽት ላይም ህወሓት አለ” ሲሉ ገልጸዋል።

“ህወሓት ከሻዕብያ ጋር ግንኙነት አለው በሚል የሚገለጸው ፍጹም ሀሰት ነው” ያሉት ፍስሃ ሃፍተፅዮን (ዶ/ር) “በውስጣችን ያሉት ግን መሬታችን ወረው የያዙት ሀይሎች ደጋፊዎች ናቸው” ሲሉ አስታውቀዋል።

በክልሉ ሊደረግ ስለታሰበው ሪፎርም አስመልክተው አስተያየታቸውን የሰጡት ስራ አስፈጻሚው “ “ሪፎርሙን ለመተግበር በተንቀሳቀስንበት ወቅት ነው ሁከቱ/ግርግሩ የገጠመን” ሲሉ ገልጸዋል። “ሪፎርም ከመካሄዱ በፊት የተወረረው መሬታችን እና የፈተናቀለው ወገናችን መመለስ አለበት” ሲሉ አስታውቀዋል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ የትግራይን ግማሽ መሬት ይዞ ነው ሪፎርም አካሂዳለሁ በሚል እየተንቀሳቀሰ ያለው ሲሉ የገለጹት ፍስሃ ይህ አካሄድ ደግሞ ህወሓትን የሚያፈርስ ነው ብለዋል።

አሁን በውስጣችን ያለው ልዩነት የሰላም ስምምነት ከተፈራረምናቸው አካላት ጋር በመነጋገር በህግ ወይንም ደግሞ በውስጣችን በምናደርገው ውይይት እልባት እንዲያገኝ እናደርጋለን ሲሉ አስታውቀዋል።

በምንም መንገድ ወደ ጦርነት ሊያስገባን የሚችል ነገር የለንም ሲሉ አረጋግጠዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button