ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: መንግስት የታገቱ ተማሪዎች ተለቀዋል እያለ ሀሰተኛ መረጃ እያሰራጨብነው ሲሉ የታጋች ቤተሰቦቸ ማዘናቸውን አስታወቁ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4/2016 ዓ.ም፡- በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ገርበ ጉራቻ ከተማ አቅራቢያ ታፍነው የተወሰዱ ከ160 በላይ ተማሪዎች መለቀቃቸውን የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ቢሮ ቢያስታውቅም፣ የታጋች ተማሪዎች ቤተሰቦች ልጆቻቸው እንዳልተፈቱ በመግለጽ የመንግስት ሀሰተኛ መረጃ እያሰራጨ ነው ሲሉ ኮንነዋል፤ አሁንም እንደታገቱ ነው በማለት ስጋታቸውን አጋርተዋል።

የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ቢሮ ትላንት በሰጠው መግለጫ እንደገለጸው “ጽንፈኛ እና አሸባሪ ሃይል” ብሎ በጠራቸው ሃይሎች ታግተው ከነበሩት 167 ተማሪዎች መካከል 160 ያህሉ በ”ከባድ ኦፕሬሽን” መለቀቃቸውን አስታውቋል።

ተማሪዎቹ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ከእገታ እንዲለቀቁ ተደርገዋል ሲሉ የቢሮው ኃላፊ አቶ ሃይሉ አዱኛ ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።

አዲስ ስታንዳርድ ያነጋገራቸው የታጋቾች ቤተሰቦች በበኩላቸው የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ኮሚኒኬሽን የሰጠውን መግለጫ ሐሰት ነው ሲሉ አስተባብለዋል።

በደባርቅ ዩኒቨርስቲ የ3ኛ ዓመት የIT ተማሪ የሆነች ልጃቸው ከታገቱት መካከል እንደምትገኝ የገለፁ አንድ አባት “ከአጋቾቹ ጋር በየቀኑ እየተገናኘን ነው፣ አሁንም ገንዘቡን እንድንከፍል እየተጠየቅን ነው፣ ልመናችንንም እየሰሙ አይደለም” ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልፀዋል፤ አክለውም አጋቾቹ ልጃቸውን ለመልቀቅ አንድ ሚሊዮን ብር እየጠየቁ መሆኑን ተናግረዋል።

የታጋች አባት አክለውም ባለፈው ረቡዕ ሰኔ 25 ቀን 2016 ዓ.ም አፈናው በተፈጸመበት ወቅት ለባለሥልጣናት ሪፖርት ማድረጋቸውን ገልፀው ነገር ግን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከመንግሥት የሰሙት ነገር አለመኖሩን ተናግረዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በቅርቡ መንግስት በሰጠው መግለጫ የተሰማቸውን ቅሬታ በመግለጽ “እስከ ዛሬ አንድም ተማሪ በመንግስት ታጣቂዎች አልተፈታም፤ አጋቾቹ በየቀኑ ከልጆቻችን ጋር ያገናኙናል፤ የተመለከቱት የመንግስት ሃይል አለመኖሩንም ነግረውናል” ሲሉ ገልፀዋል።

ሌላ ልጃቸው የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የሶስተኛ አመት ተማሪ የሆነች እና ከታገቱት ተማሪዎች መካከል የምትገኝ መሆኗን የተናገሩ አባትም ይህንን ዘገባ አረጋግጠዋል። ሴት ልጃቸው እንዳልተፈታች እና ለማስለቀቂያ የሚሆን ገንዘብ እንዲከፍሉ እየተጠየቁ መሆኑን ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።

አርሶ አደር የሆኑት አባት “ይህን ያህል ገንዘብ መያዝ ይቅርና ሰምቼም አላውቅም” በማለት ተናግረዋል። አክለውም ልጄን እንዲፈቱልኝ ከለመንኳቸው በኋላ በእግዚአብሔር እጅ ተውኩት” ሲሉ ሁኔታውን አስረድተዋል::

እኚህ ወላጅ አክለውም በአጋቾቹ በተመቻቸላቸው የስልክ ውይይት ተማሪዎቹ ከመጀመሪያ ታግተው ከነበረበት ቦታ ወደ ሌላ አካባቢ እንደተወሰዱና በአሁኑ ወቅት ተከፋፍለው በተለያዩ ቦታዎች እንደሚገኙ ለማወቅ መቻላቸውን ተናግረዋል።

የሶስተኛ አመት የደባርቅ ዩኒቨርስቲ ተማሪ እሀቷ እንደታገተችባት ለአዲስ ስታንዳርድ ያስታወቀች የታጋች ቤተሰብ በበኩሏ “ተለቀቁ በሚል የሚነገረው መረጃ ፍጹም ሀሰት ነው” ስትል ገልጻ “አሁንም እንደታገቱ ናቸው ምንም አዲስ ነገር የለም ብላለች። “ለመጨረሻ ጊዜ ትላንት (ሐምሌ 3 ቀን 2016) ጠዋት ሁለት ሰዓት እህቴን ያገቷት ታጣቂዎች ደውለውልኝ አገናኝተውኝ አውርቻላሁ” ስትል ሁኔታውን አብራርታለች።

ከእህቷ በተጨማሪ አጋቾቹም እንዳዋሯት አስታውቃ “ ብር ነው የሚፈልጉት፤ ብር አሰባሰቡ ነው ያሉኝ” ስትል ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጻለች።

“እኛ የምናውቀው ዕውነት ሌላ ነው፣ ሚዲያ ላይ የሚዘገበው ሌላ ነው” ስትል በምሬት ሁኔታው በጣም እንዳሳዘናት በመግለጽ“ ተለቀዋል ሲባል ነው የምንሰማው፣ እኛ ግን እንዳልተለቀቁ ነው የምናውቀው” በዚህ ምክንያት ከመናገር መቆጠብ መርጠናል ስትል ትዝብቷን አጋርታናለች።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አፈናውን የፈጸመው “ሸኔ” በማለት የጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት እንደፈፀመው የገለጸ ሲሆን ታጣቂ ቡድኑ ለቀረበበት ክስ እስከ አሁን ምንም ምላሽ አልሰጠም።

“ከቅርብ ግዜያት ወዲህ በተደጋጋሚ በኦሮምያ እና አማራ ክልሎች እየተፈጸሙ ያሉ የንጹሃን እገታዎች፣ የተራዘመ ግጭት ወንጀለኞች እንዲበረታቱ እና የህግ የበላይነትን እንደሚሸረሽር እንደሚያደርግ ማሳያ ነው” ሲሉ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤሪቪን ማሲንጋ መግለጻቸውን በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ይፋ ማድረጉን መዘገባችን ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ሰኔ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው 3ኛ አመታዊ የሰብአዊ መብት ሁኔታ ሪፖርቱ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ላይ የሚደርሰው አፈና እየጨመረ መምጣቱን አመልክቷል።

ከዚህ ቀደም አዲስ ስታንዳርድ በጥቅምት 2023 ባቀረበው ዘገባ በኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ለገንዘብ ተብሎ የሚካሄደው አፈና እየጨመረ መምጣቱንና ለዚህም በመንግሥት ሃይሎች እና በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት መካከል የቀጠለው ግጭት መንሰኤ መሆኑን መገለጹ ያታወሳል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button