ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: ምርጫ ቦርድ “ህወሓት በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ እንዲመዘገብ” መወሰኑን አስታወቀ፣ “ሕጋዊ ሰውነቱ ወደ ነበረበት አልተመለሰም” ብሏል

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 3/2016 ዓ.ም፡- የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ “በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ” መመዝገቡ ተገለጸ። ቦርዱ “በድጋሚ የቀረበለትን ሕጋዊ ሰውነት ወደ’ነበረበት እንዲመለስ የሚለውን ጥያቄ አልተቀበልኩም ብሏል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ ነሃሴ 3 ቀን 2016 ዓ.ም ይፋ ባደረገው ደብዳቤ መሰረት ህወሓት የቀደመ ህጋዊ ሰውነቱ ወደነበረበት ሳይመለስ በልዩ ሁኔታ መመዝገቡን ለፓርቲው አስታውቆታል።

“በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ስለመመዝገቡ የተሰጠው የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ለህ.ወ.ሓ.ት እንዲደርሰው ተደርጓል” ብሏል።

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ሐምሌ 19 ቀን 2016 ዓ.ም. በተጻፈ ደብዳቤ የፓርቲው ሕጋዊ ሰውነት ወደነበረበት እንዲመለስ ጥያቄ አቅርቧል ያለው የምርጫ ቦርድ መግለጫ የተሻሻለው ዐዋጅ “በዓመፅ ተግባር ተሠማርቶ ለተሠረዘ ፓርቲ የቀድሞውን ኅልውና መልሶ የሚሰጥ የሕግ ድንጋጌ ያልያዘ በመሆኑ” ቦርዱ በድጋሚ የቀረበለትን ሕጋዊ ሰውነት ወደ ነበረበት እንዲመለስ የሚለውን ጥያቄ አልተቀበለውም” ብሏል።

በሌላ በኩል የፍትሕ ሚኒስቴር ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በጻፈው ደብዳቤ ህ.ወ.ሓ.ት ኃይልን መሠረት ያደረገ የዐመፅ ተግባሩን በማቆም ሕገ-መንግሥታዊ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን አክብሮ ለመንቀሳቀስ የተስማማ መሆኑን በመጥቀስ በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር ማሻሻያ ዐዋጅ መሠረት በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ እንዲመዘገብ ማረጋገጫ ለቦርዱ በመስጠቱ፣ በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ እንዲመዘገብ መወሰኑን አስታውቋል።

ቦርዱም በልዩ ሁኔታ የመመዝገብ ውሣኔን የያዘው ደብዳቤ ለፓርቲው ከደረሰው ቀን ጀምሮ ባሉት ስድስት ወራቶች ውስጥ ፓርቲው የቦርዱ ታዛቢዎች በተገኙበት ጠቅላላ ጉባዔ እንዲያደርግ ሲል ገልጿል።

በዚህ ጉባዔም መተዳደሪያ ደንቡን እንዲያፀድቅ፣ አመራሮቹን እንዲያስመርጥ ቦርዱ መወሰኑን አመላክቷል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የቅድመ ጉባዔ ዝግጅት የተመለከቱ ሥራዎችን ቦርዱ መከታተል እንዲችል ፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ ከማድረጉ 21 ቀናት በፊት የጠቅላላ ጉባዔ የሚያደርግበትን ቀን ለቦርዱ ማሳወቅ አለበት ሲል አሳስቧል።

የትግራይ ክልል ግዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት እና የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ረዳ ፓርቲያቸው በሚያካሂደው ጉባኤ እንደማይሳተፉ ነሃሴ 2 ቀን 2016 ዓ.ም ለፓርቲው ሊቀመንበር በጻፉት ደብዳቤ ማስታወቃቸውን የተመለከተ ዘገባ ማስነበበቻን ይታወቃል።

አቶ ጌታቸው ረዳ ለፓርቲው ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል በጻፉት ደብዳቤ ሊያካሄድ የታሰበው ጉባኤ ፓርቲውን እና የክልሉን ህዝብ አደጋ ላይ የሚከት ነው ሲሉም ማስታወቃቸውም በዘገባው ተካቷል።

ፓርቲው ህጋዊ እውቅና እንዲያገኝ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተጻፈው ደብዳቤም ይሁን በህወሓት ስም የሚደረጉ የጉባኤ እንቅስቃሴዎች ፓርቲውን የማይወክሉ እና የአንድ ቡድን ህገወጥ እንቅስቃሴ በመሆናቸው እንደማልቀበለው ላሳውቅ እወዳለሁ ማለታቸውም በዘገባው ተካቷል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button