ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: “በህወሓት አመራር መካከል የተፈጠረው ክፍፍል፣ ሙስና እና ብልሹ አሰራር የትግራይን ቀውስ እያባባሰው ነው” - አቶ ጌታቸው ረዳ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23/2016 ዓ.ም፡- የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት እና የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ረዳ በፓርቲያቸው አመራር ላይ የሰላ ትችት የሰነዘሩበት ገለጻ አድርገዋል፤ ለጊዜያዊ አስተዳደሩን ዕቅድ መበላሸት እና ለክልሉ ጸጥታ መደፍረስ የህወሓት አመራር ተጠያቂ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

አቶ ጌታቸው ረዳ ከድምጽ ወያነ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባካሄዱት የትግርኛ ቃለምልልስ ክልሉ እየተጋፈጠ ያለውን ዘርፈ ብዙ ችግር አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ክልሉ በቀውስ ውስጥ እየታመሰ ይገኛል ያሉት አቶ ጌታቸው ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱ የህወሓት አመራር ከህዝቡ ሰላም እና ደህንነት ይልቅ ለግላዊ ፍላጎቱ ቅድሚያ መስጠቱ ነው ሲሉ ተችተዋል።

ለትችታቸው ዋነኛ ማጠንጠኛም ወንጀለኞች በተደራጀ እና የውጭ ሀገራት ሰዎችን ባካተተ መልኩ ኔትዎርክ ዘርግተው የወርቅ እና ሌሎች ማዕድናት ስርቆት እና ዘረፋ እያካሄዱ መሆኑን አስቀምጠዋል።

እነዚህ ተግባራት “አከባቢው እንዲበከል አድርገዋል፣ ከብቶች እንዲመረዙ እና በክልሉ ግጭቶች እንዲስተዋሉ አድርገዋል” ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።

በክልሉ እየተባባሰ ላለው የጸጥታ ችግር ዋነኛ ምክንያቶቹ “በተዋረድ ያለው አስተዳደር አለመናበብ፣ በጊዜያዊ አስተዳደሩ፣ በጸጥታ ሀይሉ እና በፍትህ ተቋማት መካከል አለመናበብ” መሆኑን አመላክተዋል።

“በህወሓት አመራር ላይ እየተስተዋለ ያለው ክፍፍል ሁኔታው እንዲባባስ አድርጓል” ብለዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ዕቅዶቹን እንዳያሳካ ትልቅ ችግር የሆነበት የፓርቲው የፖለቲካ አመራር ድጋፍ አለማድረጉ መሆኑን አስታውቀዋል። የጊዜያዊ አስተዳደሩ በተሾመ በሳምነቱ በፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች “ባንዳ” በሚል የተቀናጀ የስም ማጥፋት ዘመቻ ተካሂዷል ሲሉ ከሰዋል።  

“የተሰራጨው የስም ማጥፋት ዘመቻ ሁሉም የጊዜያዊ አስተዳደሩ ሹሞች ጠላት እና ባንዳ ተደርገው” ነው ብለዋል።  

ፓርቲው ጉባኤ ማካሄድ እንዳለበት እምነታቸው መሆኑን የጠቆሙት አቶ ጌታቸው “አሁን በፓርቲው በአመራር ላይ ያለው አካል ግን ስልጣን ለመቀራመት እንጂ ፓርቲው እንዲሻሻል አይደለም” ሲሉ ተችተዋል፤ ዝግጅቱ ግልጽነት እና ይዘት የለውም ሲሉ ገልጸዋ።

በወርቅ ዘረፋው ላይ ከሴኔጋል፣ ናይጀሪያ እና ቻይና ዜጎች የተሳተፉበት፣ ወርቁን ለማውጣት መርዛማ ኬሚካልም ጭምር ጥቅም ላይ የዋለበት ነው ሲሉ ገልጸው በክልሉ በስፋት እየተካናወነ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

በሙስና ተግባር እጃቸው ያለበትን የየትኛውም የፖለቲካ ወገን ደጋፊ ቢሆኑም፣ ምንም አይነት የቀደመ አስተዋጽኦ ቢኖራቸውም ተጠያቂ እናደርጋል ሲሉ ቃል ገብተዋል።

ፓርቲው በመጻኢ ግዜው ከመወያየቱ በፊት ክልሉ ያሳለፈውን ግጭት ሊገመግም ይገባል ሲሉ ጠቁመዋል።

ፓርቲው ጉባኤውን ከማካሄዱ በፊት ከምርጫ ቦርድ እና ከፌደራል መንግስቱ ጋር መተባበር ህጋዊ እውቅና እንዲያገኝ ማድረግ ያስፈልገዋል ሲሉ አስታውቀዋል።

ጉባኤው ትኩረት ሊያደርግባቸው ይባል ብለው ካነሷቸው ነጥቦች መካከልም ክልሉ የተጋረጡበትን ፈተናዎች መፍታት የሚችልበት መፍትሔዎችን ማበጀት የሚለው ይገኝበታል።

ከቀናት በፊት ከፌደራል መንግስት ባለስልጣናት ጋር ውይይት አካሂደው መመለሳቸውን ያስታወቁት የፓርቲው ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል ፓርቲያቸው ህጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስለት ለምርጫ ቦርድ ደብዳቤ ማስገባቱን እና በሁለት ሳምንት ውስጥ ምላሽ እናገኛለን ብለን እንጠብቃለን ሲሉ መግለጻቸው ይታወሳል።

ዶ/ር ደብረጺዮን በመግለጫቸው ኃይልን መሠረት ባደረገ የአመጽ ተግባር ተሳትፎ የነበረ የፖለቲካ ቡድን በፓርቲነት እንዲመዘገቡ የሚፈቅደው በምርጫ ሕጉ ላይ የተደረገው ማሻሻያ የፓርቲያቸውን ፍላጎት እንደማያሟላ አስታውቀዋል።

እንደ ደ/ጺዮን አገላለጽ ህወሓት ህጋዊ ፓርቲ ሁኖ መመዝገብ ብቻ ሳይሆን የሚፈልገው ከጦርነቱ በፊት በነበረበት ህጋዊነት እንዲመለስለት ይፈልጋል፤” የተሻሻለው አዋጅ እንደ ፋኖ ላሉ ቀድመው ፓርቲ ሁነው ላልተመዘገቡ ቡድኖች ሊጠቅም ይችላል፣ እንደ ህወሓት ላሉት ጋን አይሰራም፣ ምክንያቱም እንደ አዲስ ፓርቲ በጭራሽ አንመዘገብም” ብለዋል።

“ከጦርነቱ በፊት ወደ ነበርንበት ህጋዊ ፓርቲነት መመለስ ነው የምንፈልገው” ሲሉ ገልጸዋል። በጉዳዩ ልዩነት ዙሪያ ጠ/ሚኒስትሩ በተገኙበት ለምርጫ ቦርድ እና ለፌደራሉ መንግስት ባለስልጣናት ፓርቲያቸው ዝርዝር መረጃ መስጠቱን ጠቁመዋል፤ ስምምነት ላይ ተደርሷል ሲሉ ገልጸዋል።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ግን ሀሰተኛ መረጃ ነው ሲሉ ተችተዋል፤ ፓርቲው  ለመመዝገብ ለምርጫ ቦርድ ያስገባው ደብዳቤ አዲሱን የተሻሻለውን አዋጅ ጠቅሶ ነው ብለዋል። የፓርቲውን አባላት እና ህዝቡን ማሳሳት ተገቢ አይደለም ሲሉ አስታውቀዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button