ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: በህወሓት ጉባኤ “የሚተላለፉ ውሳኔዎች ተቀባይነት የላቸውም” ሲል በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ቡድን ባወጣው የአቋም መግለጫ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 13/2016 ዓ.ም፡- በሐወልቲ ሰማእታት አደራሽ በመካሄድ ላይ ባለው የህወሓት ጉባኤ የሚተላለፉ ውሳኔዎች ተቀባይነት የላቸውም ሲል በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ቡድን ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የተጠራ “ህወሓትን የማዳን” በሚል በመቀለ ትላንት እሁድ ነሃሴ 12 ቀን 2016 ዓ.ም የተካሄደው ስብሰባ ተጠናቀቀ።

በስብሰባው መጠናቀቂያ ላይ ተሰብሳቢዎቹ ባለ 10 ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተዋል። በመግለጫቸውም በህወሓት ሊቀመንበር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) በሚመራው ቡድን፣ ባለፈው ማክሰኞ ነሃሴ 7 ቀን 2016 ዓ.ም መካሄድ የጀመረው ጉባኤ የሚያስተላልፋቸውም ማናቸውም ውሳኔዎች ተቀባይነት የላቸውም ሲል አስታውቋል።

“አንድን ቡድን ለመጥቀም ተብሎ በመካሄድ ላይ ያለው ጉባኤ በፓርቲያችን እና ህዝባችን አደጋ የሚያስከትል እንዲሁም ህገወጥ እና ተቀባይነት የሌለው ነው” ያለው መግለጫው “በመሆኑም በጉባኤው የሚተላለፉ ውሳኔዎች ተቀባይነት የላቸውም፣ በዚህም ይህ ህገወጥ እንቅስቃሴ ፓርቲያችንን እና ህዝባችንን አደጋ ውስጥ የሚከት በመሆኑ ሁሉም አጥብቆ ሊታገለው ይገባል” ሲል አሳስቧል።

“በህገወጡ ጉባኤ ሳቢያ ለሚመጡ አደጋዎች ሁሉ ተጠያቂው ይህ ቡድን ሀላፊነቱን ይወስዳል” ሲል አስጠንቅቋል።

በሌላ በኩል ጉባኤው በማካሄድ ላይ ያለው በሊቀመንበሩ የሚመራው የህወሓት ቡድን በበኩሉ ላለፉት 7 ቀናት ሲያካሂደው የነበረውን ጉባኤውን ዛሬ ነሃሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም ከሰአት በኋላ እነደሚያጠናቅቅ አስታውቋል።  

በይፋዊ የማህበራዊ ሚዲያ ፌስቡክ ገጹ ባጋራው መረጃ በቀረቡ አጀንዳዎች ዙሪያ ሰፊው ውይይት በማካሄድ ውሳኔዎችን አሳልፏል፣ እስከ ቀጣይ ጉባኤ ድረስ ፓርቲውን በማዕከላዊ ኮሚቴነት እና በቁጥጥር ኮሚሽንነት የሚመሩ አመራሮችን እየመረጥኩ ነው ሲል ገልጿል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ትላንት በመቐለ ከተማ በሚገኘው የትግራይ ምክር ቤት አደራሽ በተካሄደው ስብሰባ አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 16 የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እና የማዕከላዊ ቁጥጥር ኮሚሽን አባላት፣ እንዲሁም ከመቐለ ከተማ፣ ከዞንና ከወረዳዎች የተወከሉ የፓርቲው አመራሮች መሳተፋቸው ተጠቁሟል።

“የጊዜያዊ አስተዳደሩ በክልሉ በምርጫ የተመረጠ መንግስት እስኪመሰረት ድረስ ከፍተኛው የክልሉ አስፈጻሚ አካል ነው፣ በመሆኑም ከጎኑ በመቆም ሁሉንም ድጋፍ እናደርጋለን” ሲሉ ተሰብሳቢዎቹ ባወጡት የአቋም መግለጫ አመላክተዋል።

“መላ ህዝባችን፣ አባላችን እና ካድሬዎቻችን ፓርቲያችን ህወሓት ካጋጠመው የመሰንጠቅ፤ መጠፋፋት አደጋ በማውጣት ብቻውን ሳይሆን ከሌሎች በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ጋር በመተባበር እና በመቻቻል የሚሰራ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ እነዲሆን እንታገላለን” ሲሉ ተሰብሳቢዎች በአቋማቸው ገልጸዋል።

በተያያዘ ዜና የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት እና የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ረዳ ትላንት የተካሄደውን ስብሰባ በከፈቱበት ወቅት ባደረጉት ንግግር በህወሓት ከፍተኛ አመራር መካከል ጉባኤ ይደረግ አይደረግ የሚል ልዩነት አለመፈጠሩን ጠቁመው እንዴት ይደረግ በሚለው ላይ ገነ ሰፊ ልዩነት መስተናገዱን አውስተዋል።

ህወሓት ውስጥ የተፈጠረው ልዩነት አስጊ እና ‘ጠላቶች’ ብለው የገለጿቸው ኃይሎች ሊጠቀሙበት ይችላሉ ሲሉ ስጋታቸውነ በንግግራቸው ያጋሩት አቶ ጌታቸው “የህዝብ የሰላም ፍላጎት ወደጎን በመተው፣ ለግዜው ማን መሆኑ በግልፅ ከማይታወቅ እና እነሱ ደጀን ይሆነናል ያሉት የውጭ ኃይል ተማምነህ፥ ያለ ዝግጅት፣ የተወሰነ ግለሰቦች ጠባብ ፍላጎት ሲባል የትግራይ ህዝብን ዳግም ወደ አደጋ ለመዳረግ የሚደረግ እንቅሰቃሴ ነው እየተካሄደ ያለው” ሲሉ ተናግረዋል።

የህወሓት ህጋዊ ዕውቅና እንዲመለስ የተደረጃ ትግል እና ከፍተኛ የፖለቲካ ድርድር እናካሂዳለን ሲሉ አቶ ጌታቸው ረዳ መግለጻቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

“ከፓርቲው ህጋዊ እውቅና ጋር በተያያዘ አዲስ የተሻሻለው አዋጅ እንደገና እንደ አዲስ እንዲመዘገብ የሚያስገድድ፣ ወርቃማውን የትግራይ ትግል ታሪክ የሚያጎድፍ፣ በቀጣይ ቅርቃር ውስጥ እንድነገባ የሚያደርግ በመሆኑ ዘላቂ መፍትሔ ሊያመጣ የሚችለው ፖለቲካዊ ድርድር በማካሄድ መሆኑን ማዕከላዊ ኮሚቴው በሙሉ ድምጽ ወስኗል” ማለታቸውም በዘገባው ተካቷል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button