ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: በሱዳን በመካሄድ ላይ ያለው ጦርነት ወደ ስደተኞች መጠለያ ጣቢያ እየተቃረበ በመምጣቱ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ስደተኞች ላይ ስጋት ፈጥሯል - ሂዩማን ራይት ዎች

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3/2016 ዓ.ም፡-በምስራቅ ሱዳን የሚገኙ ስደተኞች ህይወታቸው አደጋ ላይ ወድቋል ሲል ሂዩማን ራይት ዎች ገለጸ፤ ጦርነቱ የሱዳን አጎራባች ከሆኑት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የተሰደዱ ሰዎች ወደሚኖሩበት መጠለያ ጣቢያ እየተቃረበ በመሆኑ ስደተኞቹ ላይ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሮባቸዋል ብሏል።

የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር በምስራቅ ሱዳን አከባቢዎች ወደሚገኙ ግዛቶች እየገፋ መምጣቱን ተከትሎ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ስደተኞች ወደ ተጠለሉበት የገዳሪፍ እና ከሰላ ግዛቶች እየተቃረበ መሆኑን ዘገባዎች አመላክተዋል።

በፈጥኖ ደራሹ ሃይል እና በሱዳን ወታደራዊ ሀይል መካከል በአሁኑ ሰአት ጦርነት እየተካሄደ ያለው የገዳሪፍ እና ከሰላ ግዛቶችን በሚያጎራብተው ሴናር ግዛት ላይ መሆኑን ዘገባዎቹ ጠቁመዋል።

በገዳሪፍ ግዛት ውስጥ በሚገኝ የመጠለያ ጣቢያ ውስጥ 40ሺ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እንደሚኖሩ ሁዩማን ራይት ዎች አስታውቋል።

“የሱዳን ተፋላሚ ሀይሎች የሚያደርጉት ጦርነት ወደ ገዳሪፍ እና ከሰላ ግዛቶች ከደረሰ፣ ለአደጋ እንጋለጣለን” ሲሉ በመጠለያዎቹ ካምፕ ውስጥ የሚኖሩ ስደተኞች ከአንድ ወር በፊት ገልጸውልኝ ነበር ሲሉ ያወሱት የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቱ የአፍሪካ ዳይሬክተሯ ለተሺያ ባድር “አሁን ላይ ስጋታቸው ይበልጥ ግልጽ እየሆነ መጥቷል” ብለዋል።

በሱዳን የሚገኙ ከአንድ ሚሊየን በላይ ስደተኞች ህይወት አሳሳቢ ነው ያለው አለማቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ በአፋጣኝ ደህንነታቸው ሊያስጠብቅላቸው ወደሚችል ቦታ ሊዛወሩ ይገባል ሲል አሳስቧል።

የስደተኞቹን ደህንነት ማስጠበቅ የሚያስችል ስትራቴጂ ወይንም ወደ ሌላ ቦታ ለማዛወር የሚያስችል እቅድ አለመነደፉ በመጠለያ ካምፑ የሚኖሩ ስደተኞችን ህይወት አደጋ ላይ የሚጥል ነው ሲል ተቋሙ ስጋቱን ገልጿል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በተለይም የፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ የትግራይ ሀይሎች ከሱዳን ጦር ጎን ተሰልፈው እየተዋጉ ነው ሲል መኮነኑን ተከትሎ በገዳሪፍ የሚገኙ ከትግራይ የተፈናቀሉ ሰዎች ህይዎች አደጋና ስጋት ከፍተኛ ነው ሲል ገልጿል።

ስደተኞቹ ለጅምላ እስርም እየተጋለጡ ነው ሲል የጠቆመው ተቋሙ በገዳሪፍ ግዛት የሚገኙ ከተሞች ላይ በርካታ ኢትዮጵያውያን በከተማዎቹ ባለስለጣናት የጅምላ እስር እየተፈጸመባቸው እንደሚገኝ አስታውቋል።

በዋናነት በርካታ የትግራይ ስደተኞች የተጠለሉባቸው በገዳሪፍ በሚገኙ ሁለት ካምፖች እና በተወሰነ ደረጃ በሚገኙባቸው የከሰላ መጠለያ ካምፖች ውስጥ የሚገኙት የትግራይ ተወላጆች ወደ ቀያቸው ለመመለስ አሁንም ስጋት እንዳለባቸው ጠቁሟል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኤጀንሲዎች ከኢትዮጵያ እና ሱዳን ባለስልጣናት ጋር በመተባበር ወደ ሀገራቸው መመለስ የሚፈልጉ ስደተኞችን ለመመለስ ሁኔታዎችን እንዲያመቻቹ እና ትብብር እንዲያደርጉ ጠይቋል።

በሱዳን ተጠልለው የሚገኙ የኢትዮጵያ እና ሱዳን ስደተኞች በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ለበርካታ ግዜያት ተረስተዋል ያለው ሂዩማን ራይት ዎች አሁን ግድ ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል ሲል አሳስቧል።

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button