ፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: በኢትዮጵያ የሚፈጸሙ ግድያዎች እና የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች አሳሳቢነታቸው ጨምሯል - ኢሰመኮ

በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁም እንዲደረግ ጠይቋል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21/2016 ዓ.ም፡-የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን “በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በግጭት ዐውድ ውስጥና ውጭ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች አሳሳቢነትና ሥጋቶች” በተመለከተ ሪፖርት አውጥቷል።

በሪፖርቱም በግጭት ዐውድ ውስጥና ውጭ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችንና ሥጋቶችን በአስቸኳይ እንዲቆሙ ጠየቋል።

የአማራና ኦሮሚያ ክልሎችን ጨምሮ ሁሉንም የትጥቅ ግጭቶች በውይይት በመፍታት ዘላቂ ሰላምና የሰብአዊ መብቶች መከበርን ማረጋገጥ ይገባል ሲል አሳስቧል።

ኢሰመኮ በሪፖርቱ በተለያዩ ግዜያት በተለይም በአማራ እና በኦሮምያ ክልሎች በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና መንግስትን መሳሪያ አንግበው በመፋለም ላይ ባሉ ታጣቂዎች ተፈጸሙ ያላቸውን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በዝርዝር አስቀምጧል። ግድያዎች እና የሰብአዊ መብት ጥሰቶቹ መፈጸማቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል።

በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ከተራዘሙ የትጥቅ ግጭቶች ጋር በተያያዘና ከግጭት ዐውድ ውጭ የተፈጸሙ እንዲሁም በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች በተለይም በአፋር፣ በሶማሊ፣ በሲዳማ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ እና በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎችና በአዲስ አበባ ከተማ የቀጠሉና በቅርብ ጊዜያት የተከሰቱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችንና ሥጋቶችን በተመለከተ ኢሰመኮ ክትትልና ምርመራ ማድረጌን ቀጥያለሁ ሲል አስታውቋል።

የሚመለከታቸውን የመንግሥት አካላት፣ ተጎጂዎችን እና የተጎጂ ቤተሰቦችን፣ የዐይን ምስክሮችን እና ከአስገድዶ መሰወር የተለቀቁ ሰዎችን በማነጋገር መረጃዎችንና ማስረጃዎችን ሲያሰባስብ መቆየቱን ጠቁሟል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በሀገሪቱ አሁንም እጅግ አሳሳቢ ሆነው ከቀጠሉ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መካከል ከሕግ ውጭ ግድያ፣ የሲቪል ሰዎች ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመትና ዘረፋ፣ የዘፈቀደ፣ የጅምላና የተራዘመ እስራትና የተፋጠነ ፍትሕ እጦት፣ አስገድዶ መሰወር፣ እገታ፣ እና የሀገር ውስጥ መፈናቀል ይገኙበታል ብሏል።

ለአብነት በሪፖርቱ ከተጠቀሱ ከሕግ ውጭ ግድያ፣ የሲቪል ሰዎች ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመትና ዘረፋ መካከልም በአማራ ክልል ሰሜን ጎጃም ዞን 11 የአብነት ተማሪዎች ግድያ ይገኝበታል።

የካቲት 20 ቀን 2016 ዓ.ም. በአማራ ክልል ሰሜን ጎጃም ዞን ሜጫ ወረዳ ብራቃት ቀበሌ በሚገኘው የጋፊት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን የአብነት ተማሪዎች የዕለቱን ትምህርትና ጉባኤ ከምሽቱ 5፡00 ሰዓት አካባቢ አጠናቀው ወደ ማደሪያ ጎጇቸው ከገቡ በኋላ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች አባላት ከሌሊቱ 6፡30 ሰዓት ገደማ ወደ ቦታው ደርሰው ተማሪዎችን “ውጡ” እያሉ ተኩስ በመክፈት ቀድመው በወጡ 11 ተማሪዎች ላይ ግድያ እንደፈጸሙ፤ ሌሎች 8 ተማሪዎችን በቁጥጥር ሥር አውለው ካሳደሩ በኋላ በማግስቱ ምንም ጥፋት የለባችሁም ብለው እንደለቀቋቸው ጠቁሟል።

በሪፖርቱ ከተጠቀሱት መካከልም ታኀሣሥ 15 ቀን 2016 ዓ.ም. በግምት ከጠዋቱ 1፡30 ሰዓት አካባቢ በኦሮሚያ ክልል በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ጉዱሩ ወረዳ ውስጥ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት በየነ ጢቂ፣ ጉደታ ፊጤ፣ ሀብታሙ ንጋቱ፣ ታዴ መንገሻ፣ ዳመና ሊካሳ፣ ዱጋሳ ዋኬኔ፣ ሕፃን አብዲ ጥላሁን እና ሕፃን ኦብሳ ተሬሳ የተባሉ 8 ሰዎች መገደላቸውን ያስታወቀበት ይገኛል።

መጋቢት 1 ቀን 2016 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖ ወረዳ ስልካምባ ከተማ ላይ የኦሮሞ ነጸነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) ታጣቂዎች በከፈቱት ጥቃት የወረዳው አበዪ ሄቤን ቀበሌ ነዋሪ የነበሩ አቶ ሹመቴ ፋርስ እና ወ/ሮ ተቀባ አበጋዝ የተባሉ አረጋዊያን በመኖሪያ ቤቶቻቸው ፊት ለፊት ተገድለዋል ብሏል።

የዘፈቀደ፣ ሕገወጥ፣ የጅምላና የተራዘመ እስራትና የተፋጠነ ፍትሕ እጦት አስመልክቶ ሪፖርቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ በአዋሽ 40፣ በአዲስ አበባ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ፣ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በተለምዶ 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ፤ በአማራ ክልል በባሕር ዳር፣ ሸዋሮቢት፣ ኮምቦልቻና ጎንደር በሚገኙ የኮማንድ ፖስቱ ማቆያ ስፍራዎች እና በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች በርካቶች ለተራዘመና የዘፈቀደ እስራት መዳረጋቸውን ጠቁሟል።

ኢሰመኮ ካቀረባቸው ምክረ ሐሳቦች መካከል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ በተሰጠው ስልጣን መሰረት  ተጠያቂነት እንዲሰፍን ጠይቋል።

በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ግጭት ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁም በማድረግ ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሔ ለማፈላለግ በቁርጠኝነት እንዲሠሩም አሳስቧል።

መንግሥትበአማራና በኦሮሚያ ክልል በመካሄድ ላይ በሚገኘው የትጥቅ ግጭት፣ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊነት ሕጎች ጥሰት የፈጸሙ እና ያስፈጸሙ ኃላፊዎችን እና አባላትን እንዲሁም የታጣቂ ቡድኖች አባሎች ተጠያቂ እንዲያደርግ ጠይቋል።

ለማድረግ ተዓማኒ እና የሰብአዊ መብቶች ደረጃን የሚያሟላ የወንጀል ምርመራ እና የክስ ሂደት እንዲጀመር አሳስቧል።

ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም ጋር በተያያዘ ከተያዙት እጅግ ብዙ ታሳሪዎች ውስጥ አብዛኞቹ ቢለቀቁም አሁንም በርካቶች በእስር ላይ እንደሚገኙ በመጠቆም  በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥም ቢሆን ሰዎችን በቁጥጥር ሥር አውሎ ለተራዘመ ቅድመ ክስ እስር መዳረግ የሰብአዊ መብቶች መርሖችን የሚጥስ በመሆኑ ተዓማኒ ክስ ያልቀረበባቸው ታሳሪዎች እንዲሁም በማስገደድ የተሰወሩና ያሉበት ቦታ ሳይታወቅ የታሰሩ ሰዎች ሁሉ ከእስር እንዲለቀቁ ጠይቋል።

በጸጥታ መደፍረስ፣ ከመንግሥት አካላት ተገቢውን ምላሽና ትብብር በወቅቱ ባለማግኘትና በሌሎች ምክንያቶች ምርመራቸውና ክትትላቸው የዘገዩና የተጓተቱ በርካታ ጉዳዮችን በመርመርና ክትትል በማድረግ በተገቢው ጊዜ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button