ዜናፖለቲካ

ዜና: “በጊዜያዊ አስተዳደሩ የሚፈጸም ሹመትም ይሁን ተሿሚዎችን መሻር ከተቋማዊ አሰራር ውጭ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም” - ህወሓት

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 20/2016 ዓ.ም፡- በእነ ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በጊዜያዊ አስተዳደሩ የሚፈጸም ሹመትም ይሁን ተሿሚዎችን መሻር ከተቋማዊ አሰራር ውጭ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም ሲል ገለጸ።

በቅርቡ በሐወልቲ አዳራሽ በተካሄደው ጉባኤ ስራ አስፈጻሚ ሁነው በተመረጡት እና የፓርቲው ዋና ጸሐፊ ሁነው የተሾሙት ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሔር ተጽፎ ለፓርቲው የዞን እና ወረዳ ጽ/ቤቶች በተሰራጨው ደብዳቤ እንዳመላከተው “ከተቋማዊ አሰራር እና ህግ ውጭ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ተሿሚዎችን የማውረድ እና አዲስ ሹመቶችን የመስጠት ስራ አጠናክሮ ቀጥሏል” ሲል ኮንኗል።

በቅርቡ ጉባኤውን ያካሄደው በሊቀመንበሩ ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራው ህወሓት በስራ አስፈጻሚነት የመረጣቸው የዞን አመራሮቹ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ከዞን አስተዳደር ሃላፊነታቸው በመነሳት ላይ ይገኛሉ።

 የቀድሞ የክልሉ የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ ሊያ ካሳ ከደቡባዊ ምስራቅ ዞን አስተዳዳሪ ነታቸው በጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ተነስተው በምትካቸው ጸጋይ ገብረተኽለ ገ/ክርስቶስ ተሹመዋል።

በፓርቲው ዋና ጸሐፊ ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሔር ተጽፎ ለፓርቲው የዞን እና ወረዳ ጽ/ቤቶች በተሰራጨው ደብዳቤ “በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ ያሉ ውስነ አመራሮች የድርጅቱን ውክልና ይዘው በስልጣን ላይ የተቀመጡ ሁነው እያለ ያለ ድርጅቱ ተቋማዊ አሰራር እና ህግ ውጭ ተሿሚዎችን በማውረድ እና አዲስ ሹመቶችን አጠናክረው መስጠት ቀጥለዋል” ሲል ተችቷል።

“በ14ኛው የፓርቲው ጉባኤ ላይ በህወሓት ስም ምንም ስራ እንዳይሰሩ የተወሰነባቸው አካላት በክልሉ ዕለታዊ አዋኪ አጀንዳ በመፍጠር እና በማናፈስ በስልጣን ላይ ለመቆየት እና ህወሓትን ለማፍረስ ያለመ ሃላፊነት የጎደለው አካሄድ አጠናክረው በመቀጠል አሁንም በተለያዩ ዞኖች በግል ተሿሚዎችን ማንሳት እና አዲስ መሾም ቀጥለውበታል” ሲል ገልጿል።

“ህወሓትን ወክሎ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ሃለፊነት ይዞ የቆየው አካል በግሉ የሚያካሂደው ምደባ እና ከሃላፊነት አመራሮችን የማንሳት ተግባር ህወሓትን ከስሩ ለመንቀል እና ለማፍረስ ያለመ የተደራጀ ሴራ ነው” ሲል አመላክቷል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በመሆኑም “በሆነ ቦታ ላይ ያለን ተሿሚ በግል ውሳኔ የማንሳት እና የመመደብ አካሄድ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ማሳወቅ እንወዳለን” ሲል አሳስቧል።

“ከተቋማዊ አሰራር ውጭ በመሄድ በዞን ይሁን በወረዳ ደረጃ ተሿሚ መመደብም ይሁን ማንሳት ህገወጥ ተግባር በመሆኑ ከዚህ ውጭ በተቋሙ አሰራር ባላለፈ ሁኔታ የሚመደብ/የተመደበ አካል መምራትም ይሁን መስራት እንደማይችል ልናሳውቅ እንወዳለን” ሲልም አስታውቋል።

“በተደራጀ ሁኔታ ትግል እንዲደረግበትም” ሲል አሳስቧል።

በከፍተኛ አመራሮቹ ክፍፍል መካከል በተደረገው በ14ኛው የህወሓት ጉባኤ ያልተገኙ እና በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ያሉ “የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እና ስራ አስፈጻሚዎች ድርጅቱን እንደማይወክሉ” የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል ማስታወቃቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

ህወሓት ከ14ኛው ጠቅላላ ጉባኤው ራሳቸውን ያገለሉ የማዕከላዊ ኮሚቴ እንዲሁም የፓርቲው ማዕከላዊ የቁጥጥር ኮሚሽን አመራሮች በተራ አባልነት ከመቀጠል ውጪ ሌላ ኃላፊነት እንደሌላቸው ማስታወቁም በዘገባው ተካቷል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button