ዜናፖለቲካ

ዜና: “የህወሓት አመራሮች ልዩነታቸውን የሚያባብሱ መግለጫዎች ከማውጣት እንዲቆጠቡና ችግሮቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ” ቤተክርስቲያኗ ጥሪ አቀረበች

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 23/2016 ዓ.ም፡- በትግራይ የሚገኙ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሊቃነ ጳጳሳት ጉባኤ እና የመንበራ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ስራ አስኪያጆች በክልሉ ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ባወጡት መግለጫ የህወሓት አመራሮች ልዩነታቸውን ከሚያባብሱ መግለጫዎች ከማውጣት እንዲቆጠቡና ችግሮቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ ሲሉ ጥሪ አቀረቡ።

የክልሉ ህዝብ በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ ባለበት በአሁኑ ወቅት በአመራሮቹ መካከል የተፈጠረው ልዩነት መፍጠር ያልነበረበት ነው ያለው የቤተክርስቲያኗ አባቶች መግለጫ በአመራሮቹ መካከል ክፍፍል በተፈጠረበት ማግስት ከሁለቱ ጎራ ካሉ አመራሮች ጋር ተወያይተናል ሲሉ ገልጸዋል።

በውይይታቸውም አመራሮቹ ሁሉም “ከአባቶቻችን ፈቃድ አንወጣም፣ ስጋት አይግባችሁ፣ ልዩነቶቻችን ወደ ግጭት አያመሩም፣ በውይይት እንፈታቸዋለን” ሲሉ ቃል እንደገቡላቸው ጠቁመው ቃላችሁን እንድትጠብቁ ሲሉ አሳስበዋል፤ በቃላችሁ መሰረትም ልዩነቶቻችሁን ከሚያባብሱ መግለጫዎች ከማውጣት እንድትቆጠቡ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

“በአመራር ላይ ያላችሁ ሁላችሁም አንድ ልብ ሁናችሁ ተባብራችሁ ከቤቱ ተፈናቅሎ በጎርፍ፣ በብርድ፣ በሙቀት፣ በጭቃና በረሃብ ለአራት ዓመታት በስቃይ በመጠለያ ዳሶች ውስጥ የሚኖረውን ህዝባችሁን ለቤቱ አብቁት” ሲሉ አሳስበዋል።

የፕሪቶርያው ስምምነት ከተፈረመ “ሁለት አመታት ቢጠጋውም ሙሉ በሙሉ አልተተገበረም” ሲሉ የገለጹት የሀይማኖቱ አባቶች በመግለጫቸው “ስምምነቱ ሳይሸራረፍ እንዲፈጸም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር እንድታስፈጽሙ” ብለዋል።

“የክልሉ የግዛት አንድነት ከጦርነቱ በፊት ወደ ነበረበት እንዲመለስ በጽናት እንድትሰሩ” ሲሉ አሳስበዋል።

የሀይማኖት አባቶቹ በመግለጫቸው “የትግራይ የጸጥታ ሃይሎች ከማንም ጋር ሳትሰለፉ የትግራይን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ላደረጋችሁት ጥረት እናደንቃለን” ያሉት የሀይማኖት አባቶቹ በመግለጫቸው “ለየትኛውም ወገን ሳትወግኑ ለህዝባችሁና ለትግራይ ጥቅም እንድትቆሙ ጥሪያችንን እናቀርባለን” ብለዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በተያያዘ ዜና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ባወጣው መግለጫ በክልሉ የተለያዩ የስልጣን እርከኖች የምመድባቸውን ሰዎች አንቀበልም በሚሉት ላይ ህጋዊ እርምጃ እወስዳለሁ ሲል አስጠንቅቋል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ ህግና ስርአትን መሰረት በማድረግ የሚያካሂዳቸውን ምደባዎች ተግባራዊ እንዳይሆኑ በቅርቡ ጉባኤውነ ያካሄደው ቡድን ቀደም ብሎ በመሰረተው የኔትዎርክ ትስስር እንቅፋት ሆኖ እያደናቀፈብኝ ነው ሲል ወንጅሏል።

ከዚህም በላይ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የሚመድባቸው አመራሮች ተቀባይነት የላቸውም፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ መንግስት መመደብ አይችልም፣ ህጋዊ ምደባ አይደለም የሚል መግለጫ እስከታችኛው የአስተዳደር እርከን በመውረድ የዞንና የወረዳ አመራሮችን በማሰባሰብ መንግስታዊ አሰራር እንዳይኖር እና ስርዓት አልበኝነት እንዲፈጠር እየሰሩ ነው ሲል ኮንኗል።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ለክልሉ ህዝብ ፈጣን የሆነ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ከላይኛው የስልጣን እርከን እስከታችኛው ድረስ የሚያደርገው ምደባ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።

ይህንን ውሳኔየን የሚያደናቅፉብኝን ማንኛውንም አካል ደግሞ ህጋዊ አሰራርን ተከትሎ ተጠያቂ አደርጋቸዋለሁ፣ ህጋዊ እርምጃም እወስድባቸዋለሁ ብሏል።

በእነ ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በጊዜያዊ አስተዳደሩ የሚፈጸም ሹመትም ይሁን ተሿሚዎችን መሻር ከተቋማዊ አሰራር ውጭ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም ሲሉ መግለጻቸውን መዘገባችን ይታወሳል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button