ዜናፖለቲካ

ዜና: የሱዳን ጦርነት ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ ማስገደዱ ተገለጸ የመንግስታቱ ድርጅት ጉዟቸውን “አደገኛ” ሲል ገልጿል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 9/2017 ዓ.ም፡- በሱዳን ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሃገሪቱ ጦር እና በፈጥኖ ደራሹ ሃይል መካከል በተፈጠረው የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ወደ ሀገራቸው ለመመለስ መገደዳቸውን የመንግስታቱ ድርጅት አስታወቀ።

ከሱዳን ወደ ሀገራቸው ሳይፈልጉ በሁኔታው አስገዳጅነት ከተመለሱ ስደተኞች መካከል የትግራይ ክልል ተወላጆች ይገኙበታል ተብሏል።

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ትላንት መስከረም 8 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መረጃ እንዳመላከተው በትግራይ በኩል ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ስደተኞች ጋር ባካሄድኩት ቃለ ምልልስ ጉዟቸው “ረጅም እና አደገኛ” እንደነበር ተገንዝቢያለሁ ብሏል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደገለጸው፣ ተመላሾቹ በአማራ እና ቤንሻንጉል ክልሎች በሚገኙ የሱዳን አዋሳኝ መግቢያ ቦታዎች ተነስተው፣ የግጭት ቀጠናዎችን በጥንቃቄ በማምለጥ ወደ ትግራይ የተለያዩ ቦታዎች መጓዛቸውን አመላክቷል።

የስደተኞች ኮሚሽኑ በቅርቡ አጠናቀርኩት ባለው መረጃ መሰረት እስከ ነሃሴ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ በድምሩ 57 ሺ 568 ኢትዮጵያውያን ድንበር አቋርጠው መግባታቸውን ጠቁሞ ከነዚህም ውስጥ 11 ሺ 771 የሚደርሱ ተመላሾች ከዚህ ቀደም ወደ ሱዳን ተሰደው ተጠልለው ይኖሩ ነበር ብሏል፤ አሁን ደግሞ ድንበር አቋርጠው ወደ ሀገራቸው በመግባታቸው በኮሚሽኑ ከስደት ተመላሽ ተብለው ተመዝግበዋል ሲል አስታውቋል።

ኮሚሽኑ በትግራይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መጠለያ፣ አልባሳት እና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ችግራቸውን እየፈታ መሆኑንም አመላክቷል።

በግንቦት ወር 2016 ዓ.ም አዲስ ስታንዳርድ እንደዘገበው በሱዳን እና በደቡብ ሱዳን አዋሳኝ ድንበር ላይ በሚገኘው አቢዬ ክልል ሰፍረው የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ የነበሩ የትግራይ ተወላጆች በአከባቢው እየተባባሰ በመጣው ግጭት ምክንያት ከፍተኛ የጸጥታ ስጋት እያጋጠማቸው ነው ሲል መዘገቡ ይታወሳል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ከሁለት አመት በፊት በትግራይ ጦርነት ምክንያት በሱዳን ጥገኝነት የጠየቁት እነዚህ የቀድሞ የሰላም አስከባሪ ሃይሎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሱዳን ጦር ሃይሎች እና በፈጥኖ ደራሹ ሃይል መካከል የሚደረጉ ግጭቶች መባባሳቸውን ተከትሎ ስጋት ላይ መውደቃቸው ተመላክቷል።

በሐምሌ 2016ዓ.ም. ሂዩማን ራይትስ ፈርስት ኢትዮጵያ የተሰኘ የሀገር ውስጥ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የትግራይ ተወላጆች እና በምስራቅ ሱዳን የሚገኙ የቀድሞ የተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ ወታደሮች እንዲጠበቁ እና ወደ ሌላ ቦታ እንዲዛወሩ አስቸኳይ ጥሪ አቅርቧል።

ይህ ጥሪ የቀረበው በሱዳን ወታደሮች መካከል የሚካሄደው ጦርነት በስደተኞች ካምፖች አቅራቢያ ወደሚገኝ አካባቢዎች መስፋፋቱን ተከትሎ ነው።

በተጨማሪም በአከባቢው በሱዳን ጦር እና  በፈጥኖ ደራሹ ሃይል መካከል ያለው ግጭት እየተባባሰ በመምጣቱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጅ ስደተኞች በከፍተኛ ጭንቀት እና ስጋት ውስጥ መሆናቸውን የመብት ቡድኑ አስጠንቅቋል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን እያስተናገደች ሲሆን  በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በሱዳን እና በኢትዮጵያ ድንበር መካከል በሚገኙት የመተማ እና ኩርሙክ ሁለት ዋና ዋና መግቢያዎች እየገቡ እንደሚገኙ ተጠቁሟል።

ይሁን እንጂ በአከባቢዎቹ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት ስደተኞቹ ኑሯቸውን በተደላደለ መልኩ እንዳይገፉ እንዳደረገው ተገልጿል::

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር በበኩሉ በፀጥታ ችግር ምክንያት ወደ 7,000 የሚጠጉ ስደተኞች ከኩመር እና አውላላ ቦታዎች ወደ አዲስ ስፍራ ማዛወር መጀመሩን አስታውቋል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ መሰረት በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በአሶሳ የሰፈሩትን 48,964 ስደተኞችን ጨምሮ በአሁኑ ጊዜ  ከ90,000 በላይ ሱዳናውያን ስደተኞች ይኖራሉ።

ኢትዮጵያ በዋናነት ከደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ እና ኤርትራ የመጡ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን በማስጠለል በአፍሪካ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች ተብሏል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button