ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: የተወካዮች ምክር ቤት ህወሓት ዳግም ህጋዊ ፓርቲ እንዲሆን ያስችለዋል የተባለውን አዋጅ አጸደቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27/2016 ዓ.ም፡-የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር ማሻሻያ አዋጅን በአብላጫ ድምፅ አጸደቀ።

የአዋጁ መሻሻል በትጥቅ ትግል ስልጣን መያዝ የሚፈልጉ ሃይሎች ህጋዊና ሰላማዊ አማራጭን እንዲከተሉ የሚያደርግ ነው ተብሏል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ግንቦት 23 ቀን 2016 ዓ.ም ከህጋዊ እና ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማዕቀፍ ውጪ የቆዩ እንደ ህወሓት ያሉ የፖለቲካ ቡድኖች መልሶ መመዝገብ የሚያስችል ረቂቅ የአዋጅ ለተወካዮች ምክር ቤት መላኩን መዘገባችን ይታወሳል።

በምክር ቤቱ የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ የማሻሻያ አዋጁን አስፈላጊነት በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፤ በማብራሪያቸውም በኢትዮጵያ ሰላምን ለማፅናት የተጀመረውን ጥረት የሚያግዝ አስፈላጊ የሆነ ማሻሻያ የተደረገበት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በሃይልና በጠመንጃ ችግሮችን ለመፍታት መሞከር ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ የለውጡ መንግስት የፖለቲካ ባህልን ለማሳደግ የህግ ማዕቀፎችን ማሻሻልና በትጥቅ ትግል የሚሳተፉ ቡድኖች ወደ ህጋዊ መንገድ እንዲመጡ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠርም አንዱ ትኩረት መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም በተለያየ ምክንያት ወደ ትጥቅ ትግል የገቡ ቡድኖች ህጋዊና ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንዲያደርጉ አዋጁን ማሻሻል አስፈልጓል ብለዋል።

የትጥቅ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያን ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈላት መሆኑን ያነሱት የምክር ቤቱ አባላት የማሻሻያ አዋጁ በአገሪቷ ሰላምን ለማፅናት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑን መግለጻቸውን ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የካቲት 5 ቀን 2016 ቀን ለክልሉ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የህወሓትን ተመልሶ በምርጫ ቦርድ እውቅና ስለማግኘት ተጠይቀው በሰጡት ምላሻቸው የፌደራል መንግስት የምርጫ ቦርድን ውሳኔ እንደማይደግፈው መግለጻቸው ይታወሳል።

በአዲስ አበባ ከፌደራል መንግስቱ ጋር በነበራቸው ውይይት “ህወሓት እያሉ መግለጫ እያወጡ ህወሓት የሚባል አናውቅም የሚል ንግግር ሊኖር አይችልም” መባሉን በወቅቱ አስታውቀዋል።

“ያሉትን የህግ እንቅፋቶች ቶሎ በማሰቀረት ህወሓት ህጋዊ ህልውናው የሚረጋገጥበት ሁኔታ መፈጠር እንዳለበት ተረዳድተናል፤ የፍትህ ሚኒስቴር ጉዳዩን እንዲከታተለው እና ፈጣን ምላሽ እንዲሰጥ ሃላፊነቱ ተሰጥቶታል” ማለታቸውን መዘገባችን ይታወሳል። በአጭር ግዜ ውስጥ ይፈጸማል ማለታቸውም በዘገባው ተካቷል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button