ዜናቢዝነስ

ዜና: የፌዴራል መንግስት በጀት 971 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ሆኖ ጸደቀ፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ እና የቀረጥ ማበረታቻ አዋጆችም ጸድቀዋል

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27/2016 ዓ.ም፡- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ2017 በጀት ዓመት የፌደራል መንግስት በጀትን 971 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር አድርጎ በሙሉ ድምጽ አፀደቀ።

በምክር ቤቱ የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ ለመደበኛ በጀት የዓመቱ ወጪ 451 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር፤ ለካፒታል በጀት ደግሞ 283 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የተመደበ መሆኑን ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡

የዘንድሮው በጀት ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃጸር የ21 ነጥብ 1 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ሰብሳቢው አስረድተዋል፡፡

ምክር ቤቱ በተጨማሪም የወጪ ንግድ የቀረጥ ማበረታቻ ሥርዓት አዋጅ ላይ የተወሰነ ማሻሻያ በማድረግ በሙሉ ድምጽ ማጽደቁን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡

የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ የማሻሻያ አዋጁ የአለም አቀፍ ገበያ በመቀዝቀዙ ምክንያት ያመረቱትን ምርት ለውጭ ገበያ ማቅረብ ያልቻሉ አምራቾችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን አብራርተዋል።

በተጨማሪም በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ ወደ ሀገር ባስገቡት ጥሬ እቃ ምርት ማምረት እና ወደ ውጪ መላክ ያልቻሉትን ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡

የማበረታቻ ሥርዓቱ ተጠቃሚዎች በጥሬ እቃው ምርት አምርተው ወደ ውጭ ሀገር ላለመላክ በቂ ምክንያት የሆነው ችግር እስከሚወገድ ድረስ በጉምሩክ ኮሚሽን አማካኝነት የጊዜ ገደቡ እንዲራዘምላቸው ለማድረግ የሚያስችል አዋጅ ስለመሆኑ በውሳኔ ሀሳቡ ተመላክቷል፡፡

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ሌላኛው ምክር ቤቱ ያጸደቀው አዋጅ ደግሞ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅን ነው። አዋጁ ቁጠባንና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት ትልቅ ሚና ያለውና የካፒታል ዕቃዎችን ሳይጨምር በዕቃ እና አገልግሎት ፍጆታ ላይ የተጣለ ስለመሆኑ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡

አዋጁ በታክስ ከፋዩ እና በታክስ ሰብሳቢው መስሪያ ቤት መካከል ሲፈጠር የነበረውን ያለመግባባት በማስወገድ ምቹ የሆነ የታክስ አስተዳደር እንዲኖር የሚያግዝ እንደሆነም ተመላክቷል፡፡

መንግስት ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሃብት ተገቢውን ድርሻ እንዲያገኝ የሚያስችልና ከታክስ ነፃ መብት ገደብ የሚያበጅ አዋጅ እንደሆ የተከበሩ አቶ ደሳለኝ ባቀረቡት የውሳኔ ሀሳብ አስረድተዋል፡፡

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button